Tidarfelagi.com

የማርች 8 የስልክ ጥሪዎች…

ማርች 8 መጣሁ መጣሁ ሲል ፤ መቶ እና ከመቶ ሰው በላይ የሚያውቃቸው ሴቶች ስልክ በጥሪ የሚጨናነቅበት ወቅት ነው። እኔም እዚህ ፌስቡክ ላይ መቶ ምናምን ሰው ያውቀኝ የለ? አንድ እሽግ ስሜንም እኔንም የማያውቁ ሰዎች የሚያውቁኝ ሰዎች ፈቃዴን እንኳን ሳይጠይቁ ቁጥሬን ስለሰጡዋቸው ብቻ በዚህ ሰሞን በጥሪ ያጣድፉኛል።

የዛሬ ጠዋቱ ግን ለየት ያለ እና ትንሽ ያሳፍር ነበር። ጠቅላላው ንግግራችን የሚከተለውን ይመስላል።

– ሄሎ
– ሄሎ…ወይዘሮ ሕይወት?
– አዎ ነኝ…
– እገሊት እባላለሁ…እገሌ ከሚባል ኢንተርናሽናል ኤንጂኦ ነው የምወደውልልሽ….
– እሺ…(ስሟን እና መስሪያ ቤቱን ለማስታውስ እንገላታለሁ)
– እኔን አታውቂኝም…እገሊት ናት ስልክሽን የሰጠችኝ…
– እሺ….(አንቺን አናግሬ ስጨርስ እገሊትን እገላታለሁ ብዬ አስባለሁ)
– ለማርች ኤት ቢሮ ዝግጅት ነበረን

ይሄ አስራ ምናምንኛ ጥሪዬ ነውና በመሰላቸት ዝም አልኩ።

– እና ስልክሽን የሰጠችን እገሊት መጥታ ስለ ጠንካራ ሴትነት እና አመራር ጉዳይ እንድትናገርልን ፈልገን ነበር
– እሺ…
– እሷ ቀድማ ዝግጅት አለኝ አለች…
– እሺ…
– ከዚያ እሺ ሌሎች የምተውቂያቸው ሴቶች ስንላት የ ‹‹ለ›› እና ‹‹ሐ›› እና ያንቺን ስም ሰጠችን…
– እሺ…
– ለ ‹‹ለ› ብንደውልላት ብንደውልላት አታነሳም…
– እሺ…
– ‹‹ሐ›› ቢዚ ነኝ አለች
– እሺ….
– እና ለዚያ ነው የደወልኩት…ባልኩሽ ርእስ ላይ አርብ መጥተሸ እንድታወሪልን ነበር….

(እገሊት አልቻለችም። የኔን እና የ‹‹ለ›› እና ‹‹ሐ›› ስልክ ሰጠች። ‹‹ለ›› አልተገኘችም። ‹‹ሐ›› ቢዚ ናት። እኔ ተገኘሁ። ስለዚህ በነገረችኝ እንኳን ይሄንን በሚያህል መስሪያ ቤት ውስጥ ብዙ ሰዎች በየቦታው እየወደሉ እንደሚጠይቁ ብንገምት፣ በአንድ ሰው የምሳደድ አራተኛ ምርጫ ነኝ ማለት ነው። ያሳፍራል። በዚህ ሰአት የተመረጥኩበት ብቸኛ ምክንያት ሴት መሆኔ ሊሆን ሁሉ ይችላል። )

– ወይዘሮ ሕይወት?
– አቤት?
– እና…አርብ ጠዋት 4 ሰአት ላይ መጥተሸ በርእሱ ላይ ማውራት ትችያለሽ?
– ይቅርታ…ስምሽን ማን ነበር ያልሽኝ የእኔ እመቤት?
– እገሊት…
– ይሄውልሸ እገሊት…ደስ ይለኝ ነበር ግን ርእሱ ሰፊ ነው…ከእኔም ሙያ ጋር አይገናኝም…የተሻለ ሰው…ወንድም ቢሆን ብትፈልጊ አይሻልም?
– ወንድ……?!

ደነገጠች።

‹‹ሄደሽ ብትሰቀይ አይሻልም?›› ያልኳት ያህል ደነገጠች

– አይ…ወንድማ አይሆንም…ማርች ኤይት እኮ ነው እንዴ…..! አክብደሽው ነው እንጂ ከባድ እኮ አይደለም…ሴቶችና አመራር…ብዙ.ልትናገሪበት ትችያለሽ..

ምን እንደምላት ግራ ገባኝ። ከአነጋገሯ ማን እንደሆንኩ ፣ ምን እንደምሰራ፣ ምን እንደማውቅና ምን እንደማላወቅ እንደማታውቅ ግልፅ ነው። ያላት ረጅም የ‹‹ትንሽ ታዋቂ ሴቶች›› ዝርዝር ነው። ዝርዝር እንጂ ከዚያ የዘለለ ነገር አይደለሁም።

– ይቅርታ…ሙያዬ ምን እንደሆነ አውቀሻል ግን? አልኳት ያበጠው እንዲፈነዳ….
– እ…አይ…አላውቅም…ይቅርታ…ስምሽ ሲሰጠኝ ኢንፊሎንሻል ናት ነው የተባልኩት..

ህእ! ኢንፍሎዌንዛ ይደቁስሽ።

– እሱ እኮ ሙያ አይደለም ታዲያ…
– ኢፍ ዩ ዶንት ማይንድ ሚ አስኪንግ….ምንድነው ስራሽ ወይዘሮ ሕይወት…?
– (በረጅሙ ተንፍሼ) ኮሙኒኬሽን ላይ ነው የምሰራው…በትርፍ ጊዜዬ ደግሞ ፀኃፊ ነኝ…
– ውይ! በጣም አሪፍ…እንደዛ ከሆነማ እንደውም ግጥሞችሽን ታነቢልናለሽ! ፐርፌክት!

ሰውነቴ ተኮማተረ። ፈጣሪዬ! ትእግስቱን ስጠኝ!

– እገሊት…
– አቤት…
– እኔ ገጣሚ አይደለሁም…ልቦለድ..ወግ… ምናምን ነው የምጽፈው…ሁለት መፅኃፍት አሳትሜያለሁ…
– ዋው…..ምን የሚባሉ መፃህፍት?
– አንደኛው ባርቾ

እየፃፈች እንደሆነ በሚያስታውቅ ሁኔታ ዝም አለችና፣

– ኦኬ…ባርች…
– ባርች አይደለም ባርቾ….
– እ….እሺ…ሁለተኛውስ?
– ፍቅፋቂ
– ፍቅ- ምን?
– ተይው እገሊት…አሁን ስብሰባ ልገባ ነው… (ከዚህ በላይ ራሴን በዚህ የማሸማቀቅ ሂደት ማሳለፍ አልፈቀድኩም)
– እና አትችይም ማለት ነው?

እ….እስካሁን ግልፅ አልነበርኩም?

– አልችልም…ለግብዣው ግን አመሰግናለሁ ቻው…
– ቆይ ወይዘሮ ሕይወት…ወይዘሮ ሕይወት!
– አቤት….(ትእግስቴ ሙጥጥ ብሎ እያለቀ)
– ሌላ በዚህ ርእስ ጉዳይ ሊያወሩ የሚችሉ ሴቶች ኮንታክት የለሽም?

አሁን ነው ለሴቶች መቆም ብዬ አሰብኩ።
አሁን ነው የኮታ መስፈርተን፣ የይድረስ ይድረስ፣ የለብለብ፣ የይስሙላ ማርች 8 ዝግጅትን ብትንትኑን ማውጣት ብዬ ወሰንኩ።

– ወይዘሮ ሕይወት?
– የለኝም። ቻው!

የግርጌ ማስታወሻ- እመኑኝ፤ በእውቀቱ ስዩም ሴት ቢሆን በማርች ኤይት ሰሞን ስልኩንም ጨርቁንም ጥሎ ያብድ ነበር።

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...