በነገራችን ላይ የላይኛው የምታውቁት የሚመስላችሁ ጥቅስ በሶስት ፖለቲከኞች በተለያዬ ጊዜ የተነገረ ቢሆንም መሰረቱ የእኔ ነው። በእርግጥ በመጀመሪያ ይህንን ነገር ያነበብኩት በካርል ማርክስ ዳስ ካፒታል መጽሃፍ (ቮሊዩም ሁለት ይመስለኛል) መግቢያ ላይ ፍሬዴሪክ ኤንግልስ ከጻፋት ማስታወሻ ላይ ነበር። ከዛም በህዋሃት ኢሃዴግ ዘመን ፕሮፌሰር መረራ በቴሌቪዝን ይሄን ነገር ሲናገሩ ሰምቻለሁ።
እኔ ደግሞ የላይኛው አባባል” የሚበላው ያጣ ህዝብ” ከሚለው ንግግር ላይ “የሚበላው ስጋ ያጣ ህዝብ” በሚል ንግግሬ በስፋት በውጪ ሚዲያዎች እታወቃለሁ። ወይም አልታወቅም። ከእኔ፡ ከኤንግልስ ፡ እና ከፕ/ር መረራ የሃሳቡ ኦርጅናል ባለቤት ማን እንደሆነ ብዙ ጭቅጭቅ የሚያስነሳ ስለሚሆን ፍርዱን ለአንባቢ ትቻለሁ።
እና ምንድነው…እ…እእ.እ…እ…እ
በቃ ስጋ ግን አይናችን እያየ ኪሎ ስምንት መቶ ብር መግባቱ ነው ወይ ! ?
እኔ በተለምዶ ጥሬ ስጋ የምበላባቸው ቦታዎች ኪሎው ስጋ ከስድስት መቶ እስከ ስምንት መቶ ብር የገባ ሲሆን ወዳጄ አሳዬ ደርቤ የሚበላበት ቦታ በኪሎ 200 ብር እንደጨመሩባቸው ጥዋት ከጻፈው ፖስት ተረድቻለሁ….እንዲህ ከሆነማ እነ አሴ ሰፈርም ስጋ 250 ገባ ማለት ነው! ?
ይሄ የጭማሪ ነገር በሁሉም ምርቶች ላይ እንደሆነም መገመት ችያለሁ። ሚስቴ ዛሬ ጥዋት አስቤዛ አድርጋ ስትመጣ ከገበያ ሳይሆን ከትኩስ መርዶ የመጣች መስላ አይቻታለሁ።በደጉ ጊዜ በትላልቅ ዘንቢልና ፔስታል አስቤዛዋን ጠቅጥቃ እቤት ስትደርስ ትደውልልኝና “አንዲ እስቲ ና ወጣ በልና አግዘኝ ሰራተኛዋንም ነይ በላት….” ትለኝ ነበር።.. ዛሬ ግን ፊቷን ክስክስ አድርጋ ሁለት ትናንሽ ፔስታል ይዛ ስትገባ ሳያት የምር ከገበያ እየተመለሰች ሳይሆን ገና ወደ ገበያ ልትሄድ ባዶ ፔስታል ይዛ እየወጣች ነበር የመሰለኝ። ደግነቱ ባለፈው እንደነገርኳችሁ የቤታችንን የበጀት ወጪ ስንከፋፈል አስቤዛ የሷ ወጪ ሲሆን እኔ የቤት ኪራይ ፡ የጤና እና የመከላከያ ወጪዎች ናቸው የደረሱኝ።ጤነኛ ልጆች የሰጠኝ እና ቤቴን መሃል አዲስአበባ ላይ ያደረገ አምላክ ይመስገን .. ሃሳብ የለብኝም…በዚህ ክፍፍል ጎጃሜዋን ሚስቴን ይዤ ከኢዲስአአባ ውጪ የሆነ ክልል ኗሪ ብሆን…የመከላከያ ወጪዬ ከሃማስ ያንስ ነበር?ሎል
ለማንኛውም የብልጽግና ነኝ የሚለው መንግስት ያስብበት
ድሮ እኔ እና የተወሰኑ ጓደኞቼ የቆየ ልማድ ነበረን። በወያኔ ዘመን ቅዳሜ ረፋዱ ላይ እንገናኝና ሶስት ከሆንን አንድ አራት ኪሎ ጥሬ አዘን ከድራፍት ጋር ስናወራርደው እንውል ነበር። በጠ/ሚ ሃይለማርያም ዘመን (ያው በወያኔ ዘመን ) መቶ ምናምን ብር እናሻምደው የነበረ ስጋ ኋላ ላይ እየተወደደ ሲመጣ ልምዳችንን አሻሻልንና ለሶስት ሁለት ኪሎ ከዛም ኪሎው 380 ብር ሲገባ ለሶስት አንድ ኪሎ ፡ከዛም “ለውጡ” ሊመጣ ሲል ኪሎው ወደ አራት መቶ ብር ሲገባ ግማሽ ለሶስት እየበላን …ድሮ በቀላሉ የምናስተናግደው ” ጥብስ ይጨመር እንዴ?” የሚለውን ጥያቄ ህገመንግስት ከማሻሻል የማያንስ ክርክር የሚያስነሳ ሲሆንብን …እኔ እንደውም ቅዳሜ ቅዳሜ እንዲህ እየተሰበሰቡ ከመሳቀቅ ወዳጆቼን ማሳቅ ይሻላል ብዬ መጣጥፎችን እጽፍ ነበር..የድሮ ጓደኞቼ ትዝ ይላችኋል መቼም….
አሁንስ! ?
ጭራሽ አንድ ኪሎ ስጋ 800 ብር! ?
እዚህ ሀገር ከለውጡ በኋላ በተጋነነ ሁኔተ የጨመሩ ነገሮች ስጋትና ስጋ ናቸው።
ዛሬ የድሮ ጓደኞቼ ደወሉልኝ።
አንዲ ለምን የድሮዋ ቦታ አንገናኝም አሉኝ።
“ስጋ ቤት እንሂድ?!” በግርምት ጥያቄውን ደገምኩ። ድምጼ ውስጥ ያለው ግነት” ና አሁኑኑ ጋዛ እንሂድ” የተባልኩ ነው የሚመስለው።
“ብዙ ነን አንድ ኪሎ ብናዝ አይጎዳንም!” አለኝ ጓደኛዬ
ቁጥራችንን ሲነግረኝ አንድ አንድ አሚኖ አሲድ እንኳን አይደርሰንም።
ታዲያ እኔስ ወደ ድሮ መጣጥፌ ብለመስ አይሻለኝምን!?
ምናልባት እዚህ ጋር እኔ ያነሳሁት ቅንጦት ተብሎ ሊተው ስለሚችለው ስጋ ብቻ ይሆናል።እስቲ በሌሎች አስፈላጊ ሸቀጦች ላይ ያለውን የዋጋ ንረት አንሱትና እንወያይ።…በዋዛም በቁምነገርም(ያው ሰሚ እንኳን ባይኖርም) ስለ ምሬታችን ብንወያይ ምን ይለናል?..
ብልጽግና ሆይ አስብበት።
የኑሮ ዋጋ እንዲህ ሲወደድ የመጨረሻው መጀመሪያ ለመሆኑ ምልክት ነው።
መልካም ቀን
ይመቻችሁ