Tidarfelagi.com

የሚቀጥለው ፋሲካ

(የሚያስተክዝ ትዝታ)

ያኔ ልጅ እያለሁ ፤ የፍልሰታ ጦምን እስከዘጠኝ ሰአት እፆም ነበር። የፆም አላማ ፤ወደ እግዚያብሄር ለመቅረብ፤ በረከት ለማግኘት እና ሀጢአትን ለማስተረይ እንደሆነ ይታወቃል ። እኔ ግን የምጦመው በፆም ወቅት ቤት ውስጥ ምግብ ስለማይሰራ ነው፤ ጦሙ ሊገባ ሁለት ቀን ሲቀረው እናታችን፤ ያንን ትልቁን ብረትድስት ፤ ለሁለት ወራት ስለማትፈልገው፤ ለእትየ ፋጤ ታከራያቸዋለች፤ እትየ ፋጤ በመላው ዳሞት ብቸኛ የሙስሊም ምግብ ቤት ያላቸው ሴትዮ ነበሩ፤

በፍስክ ወቅት፤ትምርት ቤት ከምንዘምራቸው መዝሙሮች ውስጥ፤

“ሳይንስ ሳይንስ መዳኒቴ
አስታወሰኝ ጤንነቴ ( ምን ለማለት ተፈልጎ ነው ግን?)

ፊቴን ታጥቤ ፤ቁርሴን ስበላ
ሳይንስ ትዝ አለኝ፤ ከጤና ጋራ”

የሚለው አይዘነጋኝም፤በፆም ወቅት ግን ፤መዝሙሩን ትንሽ አስተካክለን እንደሚከተለው እንዘምረዋለን፤

ሳይንስ ሳይንስ መዳኒቴ
……
ፊቴን ታጥቤ ቁርሴን ባልበላም
እናት አገሬ ሁኝልኝ ሰላም
በፆም ወቅት፤ አያሌ ምእመናን ጊዝያቸውን፤ በፆሎትና በስግደት ያሳልፉታል። እኔ ግን በፆም ወቅት ቀኑን የማሳልፈው ፤ አላፊ አግዳሚውን እያስቆምኩ ፤ ሰአት በመጠየቅ ነው። (ዘጠኝ ሰአት ካልሞላ እህል ወደኛቤት አይደርስም፤)

ለምሳሌ ጋሽ በለው በቤታችን በር በኩል ሲያልፉ ጠብቄ፤

“ጋሼ ስንት ሰአት ነው?”

ጋሽ በለው ፤ የእጅ ሰአት ለማሰር ከታደሉት ጥቂት የማንኩሳ ነዋሪዎች አንዱ ነበሩ። ከሴኮ ሰአታቸው የሚመነጨው ኩራታቸው ወሰን አልነበረውም፤ ሰአትን የፈለሰፈው ሰውየ እንኩዋ የሳቸውን ያህል አይንጠባረርም !! የእጅ ሰአቱን ፤የዳሞትን አውራጃ በመወከል ፤በውሃ ዋና ውድድር አሸንፈው፤ ከጃንሆይ የተሸለሙት ነው ይባላል። የዋና ችሎታቸውን ለማጋነን በየጠላ ቤቱ እሚወራው ብዙ ነው፤ አንዳንዴ ጋሽ በለው፤ ሲደብራቸው፤ ጣና ላይ ዳይቭ ገብተው ፤ ቀይ ባህር ላይ ብቅ ይሉና የባህር ሃይላችንን ሰራተኞች “ጉዋዶች በርቱ!” ብለው፤ ይመለሳሉ ይባላል።

በነገራችን ላይ “አሳ በለው በለው” የተባለው ዘፈን ለሳቸው ነው የተዘፈነው ለእሳቸው መሆኑን ስንቶቻችን እናውቃለን?፤ እና ሰአት ስጠይቃቸው፤ በኩራት ፈገግግግ ብለው፤ እስክስታ እንደሚመታ ሰው ግራ እጃቸውን ትንሽ ርግፍ ርግፍ አድርገው፤ በክርናቸው ነፋሱን ጎስመው፤ አይበሉባቸውን ወደ ፊታቸው ያመጡና ግንባራቸውን ቁዋጠር ፈታ ሲያረጉ ቆይተው፤

” ሰባት ሰአት ነው” ይሉኛል።

“ትንሽ አጠገባቸው ቆሜ ኦና ሆዴን ሳክ ከቆየሁ በሁዋላ “አሁንስ?”

“ሰባት ካምስት”

“አሁንስ?”

“ወግድ ከዚ”

እኔም ከዚ እወግድና ሌላ ሰአት አስሮ የሚያልፍ ሰው እጠብቃለሁ። ዘጠኝ ሰአት የሚባለው ነገር እየተንቀራፈፈ፤ እሪህ ያለበት ኤሊ እየጋለበ ፤ እስኪመጣ ድረስ እጠብቃለሁ፤

ጦም ሲታሰብ ፍስክ ትዝ ይለኛል፤ ፍስክን ሳስብ ትንሽ ወንድሜ ሞሴ ይመጣብኛል ፤ ሞሴ እንቁላል አጥብቆ ይወዳል ፤ ሞሴ እንቁላል ከመውደዱ የተነሳ የሰጎን እንቁላል ከቤተክስያን ጉልላት ላይ አውርዶ ቢቀቅል አይጠላም፤ ያኔ እንቁላል የሚባል ነገር መኖሩ ትዝ የሚለን በሁለት አጋጣሚዎች ነው፤ በሳይንስ ክፍለጊዜ ስለገንቢ ምግብ ስንማር እና የፋሲካ ሌሊት ፤ የፋሲካ ሌሊት እናታችን በትልቁ ሰታቴ ብስል ያጋም ፍሬ የመሰ ዶሮ ወጥ ሰርታ አስራሁለት ቅቅል እንቁላል ትጥልበታለች ፤

ያገራችን ዶሮዎች፤ ከላይ ጆፌ አሞራ እያንጃበባቸው፤ ከታች ጎረቤት በቅዝምዝም እያባረራቸው ፤ ተሳቀው ጭረው፤ የሚጥሉት እንቁላል ከውሃ ብይ አይበልጥም፤ እንድያውም አንዳንዳንዴ ፤ከዶሮይቱ እንቁላል ፤የዶሮይቱ አይን ይተልቃል፤

ባንዱ ፋሲካ ዶሮ ወጥ ከብበን ስንበላ፤ እናታችን በየፊታችን እንቁላሎችን አስቀመጠችልን፤ ሞሴ ድርሻውን አንስቶ፤ በትንሽ በትንሹ እየቆረሰ፤እየቆጠበ በልቶ ጨረሰ፤በጉንጩ ገበር ላይ ተለክኮ የቀረውን የንቁላል ቅሪት በምላሱ ጠርጎ አጣጣመ፤ከዚያ ፤

“እማየ”

“አቤት ልጄ ”

“የሚቀጥለው ፋሲካ ስንት ቀን ቀረው?”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • solomon215mekonnen@gmail.com'
    ሠለሞን መኮንን commented on August 9, 2019 Reply

    ኑርልን!!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...