Tidarfelagi.com

የመጀመሪያዋ ግብዣ

ምድርም ሰማይም ባዶ እንደነበሩ ነው ድሮ ! …እና ባዶው ምድር ላይ …እግዚአብሔር ሳር ነሽ ቅጠል ነሽ ውሃ ነሽ ፀሃይ ነሽ እንደጉድ ፈጠረው …. በግ ነሽ ዶሮ ነሽ በሬ ነሽ ዳይኖሰር ነሽ …..ፈጠረ ፈጠረና ከዳር እስከዳር አየት አድርጎ ሲያበቃ ‹‹ፓ መልካም ነው ›› አለ ! ከዙፋኑ በታላቅ ግርማ ሞገስ ተነስቶ ወደፈጠረው ምድር እጁን ዘረጋ …..እናም ትኩሱን አፈር ቆንጠር አድርጎ ትንፋሹን እፍ ቢልበት ሰው ሁኖ እርፍ ! ያውም አዳምን የመሰለ ጎምላላ ትካሻ ከባድ ሰው !

‹‹ ያውልህ በተዘጋጀ ምድር ላይ ዘና ብለህ ኑር ….›› አለው አዳምን
ምን ዋጋ አለው አዳም ነጭናጫ ነበር ….እግዜር ብቅ ብሎ ‹‹ እንዴት ነው ኑሮ›› ሲለው
አዳም ይነጫነጫል ‹‹ ምን ኑሮ ……… ሳር ቅጠል ውሃ …ተራራ ሸንተረር ጫካ ዝሆን ዳይኖሰር ወፍ ወንዝ ዥረት ይሄ ሁሉ ኮተት ገና በፈጠርከኝ በሳምንቱ ደበረኝ ›› …..
‹‹ ጥሩ ! ምን ልፍጠርልህ ታዲያ ›› አለ እግዚአብሔር የሆዱን በሆዱ ይዞ ….መቸስ የሚጠቅመንን ነገር ቢያውቀውም ሰወችን መጠየቅ ልማዱ ነው መሻታችን በፈቃዳችን ይሆን ዘንድ ይፈልጋልና
‹‹ እኔ ምን አውቄ ብትችል እንደገና ወደአፈር ብትመልሰኝ ›› ሲል አዳም ተነጫነጨ ተማረረ ….የአዳም መነጫነጭ መነሻው የእናት ፍቅር አለማውቁ የእናት ጡት ወተትም ሳይጠባ ማደጉ እደሆነ ይጠረጠራል …

እና እግዚአብሔር ሂዋንን አሰበ …አሰበ ማለት ያው ፈጠረ ነው ….ሒዋን ሁለት ተልእኮ ነበራት አንድም እናት ለሌለው የቲም ወንድ የእናት ፍቅር መስጠት …ሁለትም ሚስት ሁና አዳምን በስጋም በነፍስም ሙሉ ማድረግ ….ለዛ እኮ ነው በእያንዳንዷ ባፈቀርናት ሴት ውስጥ ትንሽ እናትነት ትንሽ እህትነት ብዙ ሚስትነት ተቀላቅሎ የሚገኘው ….ለዛ እኮ ነው የሴቶች እቅፍ የሴቶች ጠረን የሴቶች ድምፅ እና አብሮነት ከባድ ምቾት ውስጥ የሚሞጅረን !

ፍቅረኛችን ፍቅረኛ ብቻ ስትሆንኮ ትደብረናለች …እናት ብቻም ስትሆን ምቾት ነው የሚነሳን ….ቅመማ ቅመሙ እናትነት እህትነትና ሚስትነት አብሮ ሲቀመም ነው ደገፍ የምንላት ምቹ የነፍስ አጋር በነብሳችን ራስጌ ትራስ መከዳ ሁና በምቾት ቀና የምታደርገን …. ወንዶች ብዙ ጊዜ በፍቅር ትንታ የሚሞቱት ይህን ትራሳቸውን እያጡ እኮ ነው …. ይችን ያልተቀመመች ሴት እየተደገፉ ….አቤት ስትጎረባብጥ ….ከማይመች ፍቅር በኋላ ማጅራትህን ነው ስትራፖ የሚጨመድድህ …. ለምን መሰል ታዲያ ወንዶች ሴት ባዩ ቁጥር ወዳኋላ ወደጎን አንገታቸውን የሚያዞሩት …..ያሉበት ትራስ አልመች ቢላቸው ነው ወይም የተሸለ ትራስ ፍለጋ ……(ሴቶች የሚያሙን ሌላ ነው የአይን አመል ምናምን ነው ይላሉ ) እንግዲህ ሴትን ከአዳም ጎን አጥንት ሰራና ሲቀምማት ትንሽ እናትነት ትንሽ እህትነት በዛ ያለ ሚስትነት ለከለር ደግሞ ትንሽ ጓደኝነት ነስነስ አደረገባት ….በቃ ሴት ሆነች ኬክ የሆነች ሴት …!!

ሰነባብቶ እግዜር አዳምን ጠራና ‹‹ እህ እንዴት ነው ሂወት ? ›› ሲለው
‹‹ ኧረ ተወኝ ! አሁን ገና ገነትን ሙሉ አደረካት ›› ብሎ እግዜርን በሳቅ ሊገለው (ያው ድሮ አዳምና እግዚአብሄር እንዲህ ነበር በወዳጅነት የሚያወሩት ) እንግዲህ ሂዋን አዳም ጋር ወዲያ ወዲህ እያለች ስለወደፊቱ ብቻ እያወሩ(ያው ኑሮን ከመሃል ስለጀመሩት ትዝታ አልነበራቸውም ) በደስታ ፍንክንክ ብላ ስትኖር አንድ ቀን እንዲሁ ብቻዋን ወደጫካው ጎራ አለች … እባብ እያፏጨ ቁሞ ነበር …ሂዋንን ሲያያት እንዲህ አላት

‹‹ ሃይ ቆንጅት እዚህ ሰፈር ነሽ እንዴ ? ››
‹‹ አዎ አንተስ ?››
‹‹ እኔም እዚሁ ነኝ …አንችን የመሰልሽ ቆንጆ ግን እንዴት እዚህ ጫካ ውስጥ ያስቀምጥሻል ….. ? እኔ እንዳንች አማላይና ውብ እግሮች ቢኖረኝ ኖሮ የት በደረስኩ››
ሂዋን ለመጀመሪያ ጊዜ አካባቢዋን ቃኘችው የተሸለ ሰፈር ይኖር ይሆን እንዴ ብላ ነፍሷን አባነነችው …..በዛ ላይ አዳም ራሱ ‹‹ቆንጆ›› አያውቅም ‹‹ውብ እግሮች እንዳላት›› ዛሬ ገና መስማቷ ነው …. እግሮቿን አየቻቸው ሂጅ ሂጅ አላት …. አድናቆቱ ጣማት ! በዛ ላይ አክብሮቱ ….መፅሃፉ ‹‹እባብ እግዜር ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ ተንኮለኛው ነበር ›› ሲል ሂዋን ‹‹ ግን ምናይነት ፀዳ ያለ ለሴት ልጅ አክብሮት ያለው ፍጥረት ነው ›› ስትል አሰበች!

‹‹ እስኪ ሳር ቅጠል እንበል የኔ ቆንጆ ›› አላት እባብ …ያኔ ሳር ቅጠል እንበል ማለት በአሁኑ ቋንቋ ‹‹ሻይ ቡና እንበል›› እንደማለት ነው…እናም ሴት ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብዣ የተጋበዘችው የዛን ጊዜ ነው ….(ከዛ ጊዜ ጀምሮ ሴቶች ሻይ ቡና እንበል በሚል ግብዣ ከሻይ ቡና አልፈው ሌላ ታሪክ ውስጥ መግባት እንደጀመሩ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ)

እንግዲህ ሂዋን በእባብ ተጋብዛ ግብዣው መዘዝ መዘዘና አዳምንም ይዞት ዘጭ አለ ‹‹ አዱሻ የማውቃት ዛፍ አለች አሪፍ ነገር ልጋብዝህ ›› አለችው ተከትሎ ሂዶ እጣ ፋንታውን ገመጠ ! በሰውኛ ሂሳብ ስናየው በሰው ልጅ ታሪክ ወንድን ለመጀመሪያ ጊዜ የጋበዘችው ደግሞ ሂዋን ናት(ግብዣ ድሮ ቀረ… የዛሬ ሴቶች በናታቸው አልወጡም ግብዣ ላይ ሂሂሂ )

አዳም ፍሬውን ሲበላ መብላትን መሰረት ያደረጉ ሁለት ርግማኖችን ተረገመ
‹‹አዳም›› አለው እግዜር
‹‹ አቤት ›› አለ እየፈራ
‹‹ግረህ ጥረህ ብላ …(ሂዋንን ግን በምግብ ጉዳይ አረገማትም ምናልባት በግብዣ እንድትኖር ሳይሆን አይቀርም የሚሉ አሉ)
ሁለተኛው እርግማንም ያው መብላት ጋር የተያያዘ ነው ……
‹‹ አዳም ቅድም ግረህ ጥረህ ብላ ብየሃለሁ አይደል ….?.››
‹‹አዎ ›› አለ ምን ሊለኝ ነው ብሎ በጉት
‹‹ አሁን ደግሞ እለሃለሁ …… አፈር ብላ ›› በቃ ትሞታለህ እንደማለት !

አዳም ግሮ ጥሮ ሲበላ ሂዋንን ግሮ ጥሮ ሲጋብዝ ይሄው እስካሁንም ሴትን መጋበዝ የአዳም ‹‹ሆቢ ›› ሁኖ ቀረ አፈር እስኪበላ ይጋብዛል ….በነገራችን ላይ ፊትህ የቆመ የተራበ ሚስኪን ሽ ጊዜ እጁን እየዘረጋ ምፅዋት ሲለምንህ እንዳላየህ አልፈህ ….. አንዷን ሴት ለምነህ ‹‹አፈር ስሆን›› ብለህ የምትጋብዘው ለምን ይመስለሃል ….እንደውም ግብዣ የተጀመረው ሴት ልጅ ከተቀመመችበት ቅመሞች አንዱን እናትነትን ከጣለችው በኋላ ነው …. አንተ የጎደለ ሆድ ፒዛ በርገር ቦንቦሊኖ ትጋብዛለህ የጎደለ መንፈስ ዘላለም ያዛጋል ! ለዛ እኮ ነው እናትነት የሚባለው ቅመም በተለይ ከተሜው ሴት ላይ ድራሹ የጠፋው ….እናት ሁልጊዜም ምን አንደምታደርግልህ እንጅ ምን እንደምታደርግላት አታስብም …ብታደርግላትም ፍቅሯ አይጨምርም ባታደርግላትም ፍቅሯ አይቀንስም … ዋናው ቅመም ሲከሽፍ ከቦንቦሊኖ ጋባዥ አንተ ፒዛ ጋባዥ እሱ የፍቅር ሃዋሪያ ተደርጎ በሚስትህ አይን ሲቀማጠል ብታይ እንዳይገርምህ !

እና በ ‹‹ግረህ ጥረህ ብላ›› እና ‹‹ በአፈር ብላ›› መሃል ….ኑሮ የሚባል ሂደት ተዘረጋ …..አዳም ሆድ እንዳይብሰው የተቀማትን ዘላለም ያስታውሳት ዘንድ በቀናት መካከል …በልፋቶች መሃል አንዲት አጭር ዘላለም….. አንዲት ቅልብጭ ያለች ረፍት አስቀመጠለት
….አዳም ታዲያ ለውዱ እንዲህ ይላታል
‹‹ ውዴ ነይ ልጋብዝሽ ….የእናትነት …የእህትነት የሚስትነት ቅመሞችሽን ይዘሽልኝ ነይ …………ነይ ››





ነ………………ውና
ነ……..ይ ውዴ በአጭር ዘላለማችን አጭር ገነትን በነፍሳችን ጊዮን ዳርቻ ላይ እንመስርት …. !!

2 Comments

  • yiteyenatulij@gmial.com'
    ይታያል commented on April 18, 2017 Reply

    የ21ኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ ሰው!!!

  • danielshawul7@gmail.com'
    daniel commented on January 18, 2018 Reply

    አሌከሶ አንዴት አባቱ ኧንደምወድህ……..

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...