Tidarfelagi.com

የሕዝብ ችኩል ምን ይነክሳል?

…… ወሩን ሳስበው ፆም ነው፡፡ፆም ስለሆነ፣ አንድ ሆቴል ገብቼ ቅቅል በላሁ፡፡ …..ቅቅል የበላሁት ስላማረኝ ብቻ አይደለም የበላሁት፣ ፆም ስለሆነም ነው፡፡ ብዙዎች ከሚያደርጉት በተቃራኒ ማድረግ ደስ ስለሚለኝ ነው፡፡

ለነገሩ እውነቱን እናውራ ከተባለ፣ ቅቅል አልበላሁም፡፡ በዚህ ቅቅል ኑሮ፣ ቅቅል መብላት እራስን መቀቀል ነው ብዬ ስላመንኩ ትቼዋለሁ፡፡ ግን ቃሉ “…. ያየ በልቡም የተመኘ እንዳመነዘረ ነው” ስለሚል፣ እኔም `በልቤ ስለተመኘሁ፣ በሃሳቤም ስለበላሁ` እንደበላሁ ይቆተራል፡፡ ከሆቴሉ ስወጣ( መጀመሪያዉኑስ ግን መች ገባሁ? ) ያ ቅድም ሲጣደፍ የነበረው ህዝብ አሁንም ይጣደፋል፡፡ ተፍ…ተፍ…ተፍ…….ደፍ……ደፍ….ደፍ……ክው….ክው….ክው….ጡል… ጡል…. ጡል….

ለምን እንደሚጣደፍ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ መጣደፍ ልማድ ሆኗል፡፡ በዕውቀቱ “ሲመላለስ እንጂ ሲደርስ አይታይም” ያለው እዚህ እውነት ነው፡፡ የሆነ ከፍታ ላይ ወጥቼ፣ `ህዝቤ ሆይ ተረጋጋ!` ማለት አሰኘኝ፤ “ምን ያጣድፍሀል? ደህና ህዝብ አልነበርክ እንዴ? መሮጥ ብቻ እኮ የህይወት ግብ አይደለም፤ የምትሮጥለትን ነገር ማወቅ አለብህ፡፡ ዝም ብለህ ሲሮጡ አይተህ፣ ባለመድከው እሩጫ፣ በአፍ-ጢምህ ልትተከል ነው? ኸረ ተው የድሮ አንተነትህ ይሻልሀል…” ልለው አማረኝ፡፡ ‘
‘‘ይሄ ሕዝብ በዚህ ሰዓት እግር እንጂ፣ ጆሮ የለውም’’ ብዬ ስላመንኩ ተውኩት…

…. የምር ግን ይሄ ህዝብ አማካሪ ያስፈልገዋል፡፡ ሕዝብን የሚያማክር ሳያካተሪስት ይኖር ይሆን? ቢኖርስ ሕዝብ እንዴት ተደርጎ ይመከራል፡፡ ህፃን ልጅ አይደለ፣ ጉልበትህ ላይ አስቀምጠህ፣ ፀጉሩን እየደባበስክ አትመክረው፡፡ትልቅ ሰው አይደል፣ `እስቲ እዛች ወንበር ላይ ቁጭ በል` ብለህ አትመክረው…. ወይ ሕዝብ! ለአያያዝ የማየመች ሆነብን እኮ… የጅብ ችኩልስ ቀንድ ይነክሳል እንበል፤ የሕዝብ ችኩል ምን ለመንከስ ነው እንዲህ የሚጣደፈው? አጓጉል በሆነ ችኮላ ውስጥስ ማንከስ እንጂ፣ መንከስ ይኖራል?

ብዙዎቹ ጥድፍ ጥድፍ ሲሉ ይቆዩና፣ ደክሟቸው ይሁን ትንሽ “አረፍ ብሎ ለመጣደፍ” እንጃ፣ ባቅራቢያቸው ካለ ካፌ ገብተው ቁጭ ይላሉ፡፡ አይናቸው ውስጥ ግን ያልተረጋጋ ጥድፊያ አለ…. ተነሱ እንጣደፍ እያለ የሚጎተጉት!! ቁጭ ቢሉም አላረፉም፡፡ ደሞ፣ ማኪያቶ፣ ቡና፣ ኮካ…. ነገር ነው የሚያዙት…. ይበልጥ ለመጣደፍ ይመስል፡፡ እሷን ጠጥተው ተነስተው ቱር ይላሉ፡፡ …… ኸረ ተው አንተ ሕዝብ!

ለዚህ ሕዝብ፣ ሁሉ ነገር ጥድፊያ ሆኗል፡፡ ወሬው እንኳን ጥድፊያ ነው፡፡ ፌዴሬሽንን…ፌዴሬሽን…. ቤቲ ቤቲ….ግብፅ…. ግብፅ… ሹመት …ሹመት…. ሽረት… ሽረት…. ሁሉ ነገር ጥድፊያ ነው( ጥድፊያ እንጂ፣ ጥልቀት የለም)…. “ሴቶች እራቁታቸውን ይሂዱ አትከልክሏቸው“ የተባለ ይመስል፣ ብዙዎቹ ራቁታቸውን ናቸው፡፡ ብዙ ከርፋፋ ወንዶች፣ ከርፋፋ ልብስ ለብሰው፣ በተቻለቸው አቅም፣ ከጥድፊው እኩል ለመጣደፍ ይሞክራሉ፡፡
…. ከፊት ለፊቴ ረዥም የታክሲ ሰልፍ አለ፡፡ ከታክሲው ሰልፍ ዳር የሚጮህ ሰባኪ!… እንዲህ ይላል፤ “…ጆሮ ያለህ ስማ…. አዳኛችንና መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ፣ `መምጫዬ ቀርባለች እና ንስሃ ግባ ሲል ጥሪውን ያስተላልፋል!….“ … ሳቅኩ፡፡ “ጥሪውን ያስተላልፋል” የምትለዋ ቃል የምር አሳቀችኝ፡፡….. እንደሰባኪው አባባል፣ የክርስቶስ መምጫ በቅርብ ነው፡፡ ያ ማለት፣ የእኛ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ክርስቶስም ተጣድፏል፡፡ ነው የተጣደፈው፣ የሕዝብ አካል የሆነው `የተጣደፈው ሰባኪ` ነው፣ አጣድፎ ሊያመጣው የሚሞክረው፡፡

ሰባኪው ቀጥሏል፡፡ “ የንስሃ ጊዜዬ ቀርባለችና………….ሲል ጥሪውን ያስተላልፋል!” … ሁሉም የውስጡን ጥድፊያ እንጂ ሰባኪውን የሚያዳምጠው አይመስልም፡፡ ፡፡ ግን የክርስቶስን መምጣት የሚያስንቅ ምን የሚያጣድፍ ነገር ተገኘ፡፡ እውነት በሰባኪው በኩል ጥሪ አስተላልፎ ከሆነስ( እሱ እንደው የተናቁትን ነው የሚመርጠው)…. ለንሰሃም የባከነ ሰዓት ጭማሪ ይኖረዋል ብሎ ተስፋ አድርጎ ይሆን? ….አይ እግዜር ግን! እራሱ ፁሙ፣ ፀልዩ ብሎ፣ ቢዚ ሲያደርገን ከርሞ፣ አሁን ደግሞ፣ በድንገት ሊመጣ ነው……..! ….ለተወሰኑ ደቂቃዎች ዝም ብዬ ቆምኩ- በጥድፊያው መሃል፡፡ …….. ሰዓቴን አየሁ፡፡ እቺን ይወዳል! ወደ ታክሲ መያዣዬ ተጣደፍኩ(ሃሃሃ ሕዝቡ ተጋባብኝ ወይስ አጋባብኝ ነው ሕዝቡ ላይ እኔ እራሴ ተጋባሁ?)… ታክሲዬን ይዤ ወደ ሰፈሬ፡፡ …. እቤቴ ገባሁ፡፡

ስገባ፣ እህቴ `Z` ነው `X` የምትባል አረብ ሀገር ያለች ጓደኛዋ የላከችላትን ደብዳቤ ቁጭ ብላ ታነባለች፡፡ እህቴ፣ `አታነብም!` ተብላ እንዳትታማ የሚያደርጋት አንድ ነገር ቢኖር፣ እቺ ጓደኛዋ ደብዳቤ ስትልክላት ማንበቧ ነው፡፡ ልብሴን ቀያይሬ ወደ አልጋዬ አመራሁ፡፡

“እራት ላቅርብ” አለች እህቴ፡፡

“በላሁ” አልኳት፡፡

“የት?!”
“ሆቴል”
“ምን በላህ?”
“ቅቅል!”…….. ዝም አለች፡፡ ዝም አልኩ፡፡

ከጎረቤት የአከራዮቼ ጭቅጭቅ ተነሳ፡፡ ትዳር ውሸት! ጥድፊያ ውሸት! ሕዝብ ውሸት! ቡድን ውሸት!…. ውሸት እራሱ ውሸት! ሁሉም ውሸት! አልኩ ለራሴ፡፡ ጥቅልል ብዬ ተኛሁ፡፡ ከአንድ እንቅልፍ በኋላ፣ ሕዝቡን ሆኜ እነቃለሁ፡፡ ከአንድ እንቅልፍ በኋላ ጥድፊያውን፣ ውሸቱን፣ የቡድን አስተሳሰቡን፣ ፈሊጡን እቀላቀላለሁ!…… ሽፍንፍን! ለጥ!!!! ……. አውቄ ተኛሁ፤ ሲቀሰቅሱኝ ላለመስማት……

የራስ ናቸው፡፡ የማንንም ሃሳብ ለመፃፍ አልተከፈተም! የሚያስማሙንን ሃሳቦች እዚህ ካገኛችሁ እሰየው፡፡ ለመስማማት አንፅፍም፣ ለመፃፍ አንስማማም፡፡ ወዘተ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...