ክፍል ሶስት፡ የአዲስ ግንባር ምሥረታ
ጆርጅ ሐበሽ እና ዋዲ ሀዳድ ሶሪያን እንደ ዋነኛ ቤዝ በመጠቀም ትግላቸውን በማካሄድ ላይ ሳሉ በ1962 የባዝ ፓርቲ አፍቃሪ የሆኑ መኮንኖች በሳላህ አል-ቢጣር መሪነት የሀገሪቱን መንግሥት ገለበጡ። ይህም የሶሪያ መንግስት ይከተለው በነበረው ፖሊሲ ላይ ትልቅ ለውጥ አመጣ። አዲሱ መንግስት የፍልስጥኤም ታጋዮችን በባላንጣነት ማየት ጀመረ። በተለይም ጆርጅ ሐበሽና ጓዶቹ በ1959 የተሳካ የሶሻሊስት አብዮት ያካሄዱትን ፊደል ካስትሮንና ቼ ጉቬራን የሚያደንቁ ጽሑፎችን በተከታታይ ማሰራጨታቸው በኮሚኒስትነት አስጠረጠራቸው። በመሆኑም የሶሪያ የጸጥታ ኃይሎች ዶ/ር ጆርጅ ሐበሽን አሰሩት።
ታዲያ በዚያን ጊዜም የድርጅቱን መሪ የታደገው ዶ/ር ዋዲ ሀዳድ ያካሄደው ኦፕሬሽን ነበር። ዋዲ ሀዳድ ኦፕሬሽኑን ወጥኖ ለመተግበር የወሰደበት ጊዜ ሁለት ሳምንት ብቻ ነው። ጆርጅ ሐበሽ በዚህ ዘዴ ካመለጠ በኋላ ወደ ሊባኖስ ነበር የገባው። ይህንን ተከትሎም ድርጅቱ ጠቅላይ መምሪያውን ወደ ሊባኖስ በማዞር ትግሉን ማካሄዱን ቀጥሏል።
—–
በ1967 የተካሄደው የዐረብ-እስራኤል ግጭት ፍልስጥኤማዊያን በሚከተሉት ርዕዮተ ዓለምና የትግል ስልት ላይ ትልቅ ለውጥ ነው ያመጣው። በተለይም ዶ/ር ጆርጅ ሐበሽ “ፍልስጥኤም ነፃ የምትወጣው በሁሉም ዐረቦች ትብብርና ተሳትፎ ነው” የሚለው ርዕዮት ብዙ እንደማያራምድ የተገነዘበው በዚያን ጊዜ ነበር። በመሆኑም ጆርጅ ሐበሽ የቀድሞ አመለካከቱን እርግፍ አድርጎ ተወው። በምትኩም “ፍልስጥኤም ነፃ የምትወጣው በፍልስጥኤማዊያን ቁርጠኝነትና ሁሉን አቀፍ በሆነ አብዮታዊ ትግል ነው” የሚል አዲስ እይታ ማቀንቀን ጀመረ። “ፍልስጥኤማዊያን ታጋዮች የሀገራቸውን ነፃነት እውን ለማድረግ የሚችሉት የካርል ማርክስን የአብዮታዊ ፍልስፍና ከተከተሉ ብቻ ነው” በማለትም አሰመረበት።
ጆርጅ ሐበሽ ተመሳሳይ ርእዮት ያላቸው ቡድኖች ሁሉ ተቀራርበው የጋራ ግንባር መመሥረት እንዳለባቸውም አስታወቀ። በዚህም መሠረት እነ ጆርጅ ሐበሽ ከመሠረቱት “ሐረካት አል-ቀውሚይን አል-ዐረብ” (ሐረካ) በተጨማሪ “የፍልስጥኤም ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ” እና “የፍልስጥኤም ነፃነት ግንባር” (በአሕመድ ጂብሪል የሚመራ) የተሰኙ ቡድኖች በአዲሱ ግንባር ስር ለመሰባሰብ ጠየቁ። በተናጥል የሚንቀሳቀሱት እንደ ያሲር ዐብድ-ረቦ እና ናይፍ ሃዋትማን የመሳሰሉ ታዋቂ ፍልስጥኤማዊያንም ከጆርጅ ሐበሽ ጋር ለመታገል ወሰኑ። በታሕሳስ 11/1967 በፍልስጥኤማዊያን ትግል ላይ ትልቅ አሻራ ለማሳረፍ የቻለ አንድ ታላቅ አብዮታዊ ድርጅት ተመሠረተ።
ከጆርጅ ሐበሽ ጋር ተያይዞ ዘወትር የሚጠቀሰው ይህ አብዮታዊ ድርጅት “የፍልስጥኤም ህዝባዊ የነፃነት ግንባር” ተብሎ ይጠራል። በዐረብኛ ስሙ ደግሞ “ጀብሀት አል-ሻዕቢያ ሊታሕሪረል ፈለስጢን” ይባላል። ብዙዎች እርሱን የሚያውቁት ግን Popular Front for the Liberation of Palestine በተሰኘው የእንግሊዝኛ ስሙ ነው። ግንባሩ በመጻሕፍትና በሚዲያ በስፋት የሚጠቀሰው ደግሞ “PFLP” በተሰኘው ምህጻረ ቃል ሲሆን እኛም በጽሑፋችን “PFLP” እያልን እንጠራዋለን።
——-
በዶ/ር ጆርጅ ሐበሽ የትግል ፈር ቀያሽነት የተመሠረተው PFLP ለእስራኤል መንግሥት እውቅና እንደማይሰጥ አስታወቀ። ዓላማውና ግቡ “በኢምፔሪያሊስቶችና በአውሮጳ-በቀል ጽዮናዊያን አሻጥር የፈረሰችውን ፍልስጥኤምን ነፃ ማውጣት” እንደሆነ ገለጸ። አዲሲቷ ፍልስጥኤም ለሀይማኖት ያልወገነች፣ በዓለማዊ ህግ የምትዳደር (Secular የሆነች) እና ዜጎቿን በሙሉ በእኩልነት የምትመለከት ሶሻሊስት ሀገር እንደምትሆንም አወጀ። የአይሁድ፣ የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮችም በአዲሲቷ ፍልስጥኤም ስር በጋራ እንደሚኖሩም ተገለጸ። ግንባሩ ዓላማዉን ከግቡ ለማድረስ የሚያስችሉትን በርካታ የትግል ስልቶች እንደሚጠቀምም ይፋ ተደረገ።
ዶ/ር ጆርጅ ሐበሽ የግንባሩ ዋና ጸሐፊ ሆኖ ተመረጠ። አቡ ዐሊ ሙስጠፋ ምክትል ዋና ጸሐፊ ሆነ። ዶ/ር ዋዲ ሐዳድ ደግሞ የግንባሩ የወታደራዊ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ሆኖ ተመደበ። በሳም አቡ ሸሪፍ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነ። አሕመድ ሰዓዳት፣ ያሲር ዐብድረቦ፣ ናይፍ ሀዋቲም፣ አቡሃኒ አል-ሂንዲ፣ አሕመድ ጂብሪል፣ ገሳን ከነፋኒ እና ሌሎች ታዋቂ ታጋዮች የግንባሩ የፖሊት ቢሮ አባላት ሆነው ተመረጡ።
ከቀድሞው ሐረካ የተሻለ አቅም ይዞ የመጣው አዲሱ PFLP በያሲር አረፋት ከሚመራው “ፋታሕ” ቀጥሎ በፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ድርጅት (PLO) ውስጥ ሁለተኛ ስፍራ ያለው ድርጅት ለመሆን ችሏል። አምስት የግንባሩ መስራቾች የPLO ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሆነው ተመርጠዋል። ፍልስጥኤማዊያን በስደት ባቋቋሙት የፍልስጥኤም ብሄራዊ ሸንጎ (Palestinian National Council) ውስጥም ግንባሩ ብዙ አባላቱን አስመርጧል።
አዲሱ ፍልስጥኤማዊ ግንባር የማርክሳዊ ርዕዮት አቀንቃኝ ሆኖ በመመሥረቱ ሶቪየት ህብረትና ቻይና ተደስተው ነበር። በመሆኑም ግንባሩ በሶቪየት ህብረት፣ በቻይና፣ በምሥራቅ ጀመርን፣ በቪየትናም፣ በኩባ እና በሌሎች የሶሻሊስት ሀገራት ቢሮዎቹን ለመክፈት ችሏል። ቻይና፣ ሶቪየት፣ ምሥራቅ ጀርመንና ኩባም ለድርጅቱ መጠነኛ የፋይናንስና የማቴሪያል ድጋፍ አድርገዋል።
ይሁን እንጂ የግንባሩ የግራ ፖለቲካ አቀንቃኝ መሆን በብዙ የዐረብ ሀገራት ዘንድ በበጎ መንገድ አልታየም። በቀዳሚ ዓመታት ግንባሩን እንደ ፍልስጥኤማዊ ታጋይ ቡድን ያወቁት የዐረብ ሀገራት አልጄሪያ እና ኢራቅ ብቻ ነበሩ። በ1967 በተደረገው የዐረብ-እስራኤል ጦርነት የተሸነፉት ሶሪያና ዮርዳኖስ ግን ማርክሲዝምን ባይወዱትም እንኳ እስራኤልን ለመበቀል ሲሉ የፍልስጥኤማዊያንን ትግል ለመደገፍ ወስነው ነበር። በመሆኑም ግንባሩ ሊያካሂዳቸው ላቀዳቸው ጥቃቶች ግዛታቸውን እንደ መንደርደሪያ እንዲጠቀም ፈቅደውለታል። ሙአመር አል-ጋዳፊ በ1969 ስልጣን ሲይዙ ደግሞ ከየትኛውም የዐረብ ሀገር መሪ በበለጠ ሁኔታ የግንባሩ ደጋፊ ሆኑ። ጋዳፊ ከስልጣን እስኪባረሩ ድረስ ለግንባሩ የሚሰጡትን ድጋፍ ያላቋረጡ ብቸኛው የዐረብ መሪ ሆነው ዘልቀዋል።
(ይቀጥላል)
—–
ታሕሳስ 4/2010
በሸገር ተጻፈ።