Tidarfelagi.com

የሁለት ዶክተሮች ወግ (ክፍል አራት)

ክፍል አራት፡ ትግሉን ለዓለም ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ 

በጆርጅ ሐበሽ የሚመራው PFLP እስራኤልን በትጥቅ ትግል ብቻ ለመፋለም የወሰነ ድርጅት ነበር። በመሆኑም በወቅቱ ከስድስት መቶ ያልበለጡ ተዋጊዎቹን በማሰማራት በፍልስጥኤም ግዛቶች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ያደርግ ጀመር። በሊባኖስ፣ በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ እና በሌሎች የዐረብ ሀገራት የተበተኑት ፍልስጥኤማዊያን እንዲቀላቀሉትም ጥሪ አቀረበ። በርካታ ወጣቶችም ለጥሪው ምላሽ ሰጡ። በአጭር ጊዜ ውስጥም ከአምስት ሺህ ያላነሱ ሽምቅ ተዋጊዎችን አሰልጥኖም ለትጥቅ ትግሉ አሰማራ። እነዚህ ተዋጊዎችም በጋዛ ሰርጥ፣ በምዕራባዊ ዳርቻ እና በሌሎች የፍልስጥኤም ግዛቶች የእስራኤል ወታደሮችን መፋለም ጀመሩ።

በፕሮፓጋንዳው ረገድ ደግሞ ግንባሩ ራሱን የቻለ ቢሮ አደራጀ። “ገሳን ከነፋኒ” የተባለው ታዋቂ ፍልስጥኤማዊ ደራሲና ገጣሚ የፕሮፓጋንዳ ዘርፉን እንዲመራ ተመደበ። በርሱ የሚመራው ቢሮ የግንባሩን ሬድዮ ጣቢያ በቤይሩት ከተማ በማቋቋም ህዝቡን ወደ ትግሉ የማንቀሳቀስ ጥረቱን ቀጠለ። በዐረብኛ የሚዘጋጅ አል-ሀደፍ (“ግባችን”) የተሰኘ መጽሔትና በእንግሊዝኛ የሚዘጋጅ “Revolution” የሚባል መጽሔት እያሳተመ ማሰራጨትም ጀመረ።
——
ከላይ የተጠቀሱት የግንባሩ እንቅስቃሴዎች ፍልስጥኤማዊያንን ወደ ትግሉ በማንቀሳቀስ ረገድ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል። ግንባሩ በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ መነጋገሪያ ለመሆን የበቃው ግን ከ1968 የክረምት ወራት ጀምሮ በተከታታይ ሲያካሄዳቸው በነበሩትና በቀድሞው ዘመን በፍልስጥኤማዊያን ድርጅቶች ዘንድ ብዙም ባልተለመዱት እንቅስቃሴዎቹ አማካኝነት ነው።

ግንባሩ እነዚህን እንቅስቃሴዎች ያካሄደው በዘመኑ የትግል ቋንቋ “እስራኤልን በሁሉም ስፍራና ጊዜ ማጥቃት” የሚል ስም የሰጠውን አዲስ የትግል ስትራቴጂ በስራ ላይ ካዋለ በኋላ ነበር። ይህ የግንባሩ የትግል ስትራቴጂ ፍልስጥኤማዊያን ድርጅቶች በቀድሞ ዘመናት ይከተሉት የነበረውን እስራኤልን በፍልስጥኤም ግዛት ብቻ የማጥቃት አካሄድን በማስፋት በየትኛውም ስፍራ ባሉት የወራሪዎቹ ይዞታዎችና ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸምንም ያካትታል።

አዲሱ የትግል ስትራቴጂ በግንባሩ ላይ ከፍተኛ ነቀፋና ትችት አስከትሎ ነበር። የግንባሩ የአመራር አባላት ግን የሚከተሉትን የአብዮታዊ መስመር መርሆዎች እየጠቀሱ ስለስትራቴጂው ህጋዊነት ተከራክረዋል። ጆርጅር ሐበሽ ግንባሩ ይህንን ስር ነቀል የሆነ የትግል ስትራቴጂ በስራ ላይ ያዋለበትን ምክንያት ሲገልጽ “ወራሪዎች የህግና የሞራል ገደቦችን ጥሰው ሀገራችንን ይዘውታል፤ ህዝባችንን እንዳሻቸው እየገደሉትና እያፈናቀሉት ነው፤ ጽዮናዊያን ወራሪዎች ፍልስጥኤምን ቀስ በቀስ ከዓለም ካርታ እያጠፏት ነው። ስለዚህ እነርሱን በየትኛውም ስፍራና የመፋለም መብት አለን” በማለት አስረድቶ ነበር።

PFLP አዲሱን የትግል ስትራቴጂውን መተግበር ሲጀምር በፍልስጥኤም ግዛት ውስጥ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በጣም ቀንሷል። በምትኩም ከፍልስጥኤም ግዛት ውጭ የሚገኙትን የእስራኤል የፖለቲካ፣ የንግድና ወታደራዊ ተቋማትን የጥቃቱ ዒላማዎች አድርጓል። በዚህም መሠረት ግንባሩ ታጋዮቹን በተለያዩ የዓለም ሀገራት በማሰራማት በርካታ ጥቃቶችን ፈጽሞአል።

ከነዚያ ጥቃቶች በላይ የዓለምን ህብረተሰብ ቀልብ ለመሳብ የቻሉት ግን የግንባሩ አባላትና ተባባሪዎች ያካሄዷቸው በርካታ የአውሮፕላን ጠለፋዎች ናቸው። የአውሮፕላን ጠለፋን እንደ ትግል ስልት የመጠቀምን ሐሳብ ያመነጨው ዶ/ር ዋዲ ሀዳድ ሲሆን ጆርጅ ሐበሽ እና ሌሎች የግንባሩ መሪዎች ስልቱን በመቀበል አጽድቀውታል። ግንባሩ በወሰነው የስራ ክፍፍል መሠረት ዋዲ ሀዳድ ጠለፋዎችን ሲያስፈጽም ሌሎች የግንባሩ መሪዎች አጋጣሚውን በመጠቀም በፕሬስና በሚዲያ የትግሉን ዓላማ ለዓለም ህብረተሰብ ያስተዋውቃሉ። የጠለፋ ገቢሮቹን በድርድር ለማብቃት ከሚመጡ የመንግሥታት ተወካዮችም ጋር ይነጋገራሉ።
——
በዶ/ር ዋዲ ሀዳድ አመራር ሰጪነት የተሰማሩት የPFLP አባላት የመጀመሪውያን የተሳካ የአውሮፕላን ጠለፋ ያከናወኑት በ1968 ነበር። በዚህ እርምጃም አምስት የግንባሩ ኮማንዶዎች ከሮም ወደ ቴል አቪቭ ይበር የነበረውን አንድ የእስራኤል አየር መንገድ አውሮፕላን በመጥለፍ ወደ አልጄሪያ ወሰዱት። የጠለፋው ክንውን ወዲያውኑ በዓለም የዜና ማሰራጫዎች ተዘገበ። ጠላፊዎቹ የፍልስጥኤም ህዝባዊ ነፃነት ግንባር አባላት እንደሆኑ ተገለጸ። የግንባሩ ስም እና የፍልስጥኤም ህዝብ ትግልም በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኑ።

ጠላፊዎቹ አውሮፕላኑን በአልጄርስ ከተማ ካሳረፉት በኋላ በርካታ ሀገራት ከጠላፊዎቹ ጋር ለመደራደር ጠየቁ። የግንባሩ ታጋዮች የእስራኤል ደጋፊ ከሚሏቸው ሀገራት ጋር ለመደራደር እንደማይፈልጉ ገለጹ። የጠለፋው ድራማ ያበቃው ፍልስጥኤማዊያን እንደ ጠላት የማይመለከቷት ኢጣሊያ ነገሩን በሽምግልና ከጨረሰች በኋላ ነበር። በድርድሩ መጨረሻ ላይ በተደረሰበት ስምምነት መሠረት እስራኤል በእስር ቤቶቿ የነበሩ ሰማኒያ ያህል ፍልስጥኤማዊያንን ፈታች። ጠላፊዎቹም አውሮፕላኑን ከተሳፋሪዎቹ ጋር ለቀቁ። በማስከተልም በአልጄሪያ ጦር አጃቢነት ወደ ዮርዳኖስ ተወስደው ከጓዶቻቸው ጋር ተቀላቀሉ።

የPFLP ታጋዮች ጥቃት በአውሮፕላን ጠለፋ ብቻ የተገደበ አልነበረም። ጥቃታቸው ከጠለፋ በተጨማሪ አውሮፕላኖች በአየር ማረፊያ ላይ እንደቆሙ በቦምብ ማጋየትንና ለትራንዚት በሚያርፉበት ወቅት አመቺ ሁኔታ ጠብቆ ከርቀት ማውደምንም ይጨምራል። በዚህም መንገድ በአንድ ዓመት ውስጥ (በ1968) አራት የእስራኤል አውሮፕላኖችን በተለያዩ የአውሮጳ ከተሞች አውድመዋል። በሌላ በኩል ሰዓት ጠብቀው የሚፈነዱ ፈንጂዎችን እያጠመዱ ተሳፋሪዎች ሲወርዱ አውሮፕላኖቹን ማውደምም የPFLP ታጋዮች ይጠቀሙበት የነበረ አንዱ ዘዴ ነበር።

በዓመቱ ውስጥ በPFLP ታጋዮች የወደሙት ፍልስጥኤማዊያን “ነፃነታችንን የገፈፈች ወራሪ ናት” የሚሏት የእስራኤል አውሮፕላኖችና “የዓለም አቀፋዊ ኢምፔሪያሊዝም አቀንቃኝ ናት” በማለት የሚጠሯት የአሜሪካ አውሮፕላኖች ብቻ ነበሩ። ሆኖም በጠለፋ በተያዙ ተሳፋሪዎችና በአውሮፕላኖቹ ላይ እንዲያገለገሉ በተመደቡ ሰራተኞች ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም የPFLP አመራር ለታጋዮቹ ጥብቅ መመሪያ ይሰጥ እንደነበር በጠለፋዎቹ የተሳተፉ የግንባሩ አባላት ይናገራሉ።

ታዲያ PFLP እና የፍልስጥኤም ጥያቄ እጅግ በሚገርም ሁኔታ በዓለም ዙሪያ በስፋት የተደመጡት በቀጣዩ ዓመት ዓመት ተመሳሳይ የአውሮፕላን ጠለፋ በተካሄደበት ወቅት ነበር። በዚያ ዓመት ምን ተፈጠረ? በቀጣዩ ክፍል ታገኙታላችሁ።
(ይቀጥላል)
—-
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 6/2010
በሸገር ተጻፈ።

የሁለት ዶክተሮች ወግ (ክፍል አምስት)

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...