Tidarfelagi.com

የሁለት ዶክተሮች ወግ

ክፍል አንድ፡ የትግል ጅማሮ

ይህ ተከታታይ ትረካ የሁለት ግለሰቦችን የትግል ጉዞ በአጭሩ ለማስተዋወቅ ታስቦ የተሰናዳ ነው። እነዚህ ግለሰቦች ፍልስጥኤማዊያን ናቸው። ሁለቱም ክርስቲያን ዐረቦች ነበሩ። ሁለቱም ከሀብታም ቤተሰቦች ነበር የተገኙት። ሁለቱም በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ አጥንተው በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል። ሁለቱም በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው ቆይታ ጎበዝ ተማሪዎች እንደነበሩ ተመስክሮላቸዋል።

ይሁንና ሁለቱ ዶክተሮች በዓለም ታሪክ የሚታወቁት በተመረቁበት የህክምና ሳይንስ በሰጡት አገልግሎት አይደለም። ታሪክ እነርሱን የሚያነሳው እናት ሀገራቸውን ነፃ ለማውጣት ባካሄዱት ትግል ነው። ሁለቱ ዶክተሮች በትግላቸው ላይ ሳሉ በርካታ ወዳጆችን አፍርተዋል። ብዙዎችም በጠላትነት ተነስተውባቸዋል። አሜሪካና እስራኤልን የመሳሰሉት ሀገራት ሁለቱንም “አሸባሪዎች” ይሏቸዋል። ዶክተሮቹ ግን “እኛ የነፃነት ታጋዮች እንጂ አሸባሪዎች አይደለንም” በማለት ለክሱ ምላሽ ይሰጡ ነበር። አብዛኛው የዓለም ህዝብም የነርሱን አባባል በመደገፍ እንደ ነፃነት ታጋዮች ይመለከታቸዋል።

ሁለቱ ዶክተሮች በዘመናችን በሕይወት የሉም። ይሁንና ዛሬም ድረስ የውይይትና ክርክር መነሾዎች ሆነው ማነጋገራቸውን ቀጥለዋል። እኛ የነርሱን የትግል ጉዞ ለመተረክ የተነሳሳነው ግን ከዚህ ቀደም እንደገለጽነው በሁለቱ ዶክተሮች ፊታውራሪነት የተመሠረተውና እስከ ዛሬዋ ቀን ለነፃነት በመታገል ላይ የሚገኘው ፍልስጥኤማዊ ግንባር ትግል የጀመረበትን ሃምሳኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ነው።
——
ሁለቱ ዶክተሮች በተጸውኦ ስማቸው “ጆርጅ ሐበሽ” እና “ዋዲ ሀዳድ” ይባላሉ። ጆርጅ ሐበሽ በፍልስጥኤማዊቷ የሊዲያ ከተማ በ1926 ነበር የተወለደው። ዋዲ ሀዳድ ደግሞ በሰፊድ ከተማ በ1927 የተወለደ ሳተና ነበር። ሁለቱ ፍልስጥኤማዊያን የተወለዱባቸው ከተሞች በቅርብ ርቀት ነው የሚገኙት። ይሁንና በትውልድ ሀገራቸው ሳሉ ትውውቅ አልነበራቸውም። የነርሱ ትውውቅ የሚጀምረው በ1940ዎቹ በሊባኖስ ዋና ከተማ የሚገኘው “የቤይሩት የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ” (American University of Beirut) ተማሪዎች በነበሩበት ዘመን ነው።

ሁለቱ ፍልስጥኤማዊያን በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ሳሉ በ1948 የመጀመሪያው የዐረብ-እስራኤል ጦርነት ተቀሰቀሰ። በእንግሊዝና በፈረንሳይ ትልቅ ድጋፍ የተደረገላት እስራኤል በጦርነቱ ድል ቀናት። በማስከተልም ነፃነቷን ለማወጅ ከጫፍ ላይ የነበረችውን ፍልስጥኤምን ወርራ በርካታ ህዝብ ገደለች። ከሟቾቹ መካከል አንዷ የጆርጅ ሐበሽ እህት ነበረች። እስራኤል ከግድያው ባሻገር የዶክተሮቹን ቤተሰቦች ጨምሮ በትውልዱ ፍልስጥኤማዊ የሆነውን ሰው በሙሉ ከሀገሩ አፈናቀለች። በተለይም በሀይፋ፣ ሊዲያ፣ ናዝሬትና ጃፋ ከተሞች የሚኖሩ ፍልስጥኤማዊያንን ቤት እያፈራረሰች ህዝቡን አባረረች። በታሪክ ምእራፎች “ነከባ” ተብሎ በሚጠራው በዚህ ትእይነት ከአንድ ሚሊዮን የማያንሱ ፍልስጥኤማዊያን ከሀገራቸው ተሰደው ስደተኛ ሆኑ።

ሁለቱ ዶክተሮቹ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ለመመለስ ሲሞክሩ የሀገሪቱ ዜጋ እንዳልሆኑና መሬቱንም እንዲረግጡ እንደማይፈቀድላቸው ተነገራቸው። በዚህም የተነሳ ለትምህርት የወጡት ፍልስጥኤማዊ ወጣቶች “ሀገር የለሽ ስደተኞች” ሆኑ። ሀገራቸውን በሙያቸው ለማገልገል የሰነቁት ራእይም በእስራኤል ወረራ ጨነገፈ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የህይወት መንገዳቸው እነርሱ ባልገመቱት አቅጣጫ መጓዝ ጀመረ።
——-
ዶ/ር ጆርጅ ሐበሽ እና ዋዲ ሀዳድ የፖለቲካ ጉዞአቸውን የጀመሩት በዩኒቨርሲው ውስጥ ሳሉ “የዐረብ ወጣቶች ለንቃት” የተባለ ቡድን በመመሥረት ነው። በዚህ ቡድን አማካኝነትም ኃያላኑ መንግሥታት እውቅና ነፍገዋት ለወረራ የዳረጓት ፍልስጥኤም ነፃ በምትወጣበት ሁኔታ ዙሪያ ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እና ከፍልስጥኤም ወዳጆች ጋር ይወያዩ ነበር። በሊባኖስ ለሰፈሩት የፍልስጥኤም ስደተኞች አፋጣኝ እርዳታ ለመስጠት የተሰማሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንም በተለያየ መልኩ አግዘዋል።

ጆርጅ ሐበሽ በ1951 ከዩኒቨርሲቲው በከፍተኛ ማዕረግ እንደተመረቀ በዮርዳኖስ ምድር በተቋቋሙ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች የሚኖሩትን ፍልስጥኤማዊያን ለማገልገል ወሰነ። ውሳኔውንም በተግባር ላይ በማዋል ለሶስት ዓመታት ወገኖቹን በሙሉ ልብ ሲያገለግል ቆየ። ዋዲ ሀዳድ ደግሞ በ1953 የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ ከጆርጅ ሐበሽ ጋር ተገናኘ። ሁለቱ ዶክተሮች በ1954 በአማን (የዮርዳኖስ ዋና ከተማ) አንድ የግል ክሊኒክ ከፈቱ።

ዶክተሮቹ በክሊኒካቸው በመስራት ላይ እያሉ ሙሕሲን ኢብራሂም፣ አሕመድ ሰዓዳት፣ አቡ ዓሊ ሙስጠፋ እና በሳም አቡሸሪፍን ከመሳሰሉት ፍልስጥኤማዊያን ጋር ተዋወቁ። ከነርሱም ጋር ሆነው ትግሉን በተግባር በሚቀላቀሉበት ሁኔታ ላይ መወያየት ጀመሩ። ውይይቱ እያደገ ሄደና አዲስ ድርጅት የሚመሠርተበትን ጥናት ማካሄድ ያዙ። “የድርጅቱ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም እንዴት መምሰል አለበት?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ በሰፊው ተከራከሩ። ከብዙ ውይይት በኋላም “ፍልስጥኤም ዐረባዊት ናት፣ ነፃነቷ ሊረጋገጥ የሚችለው በሁሉም ዐረቦች ትብብርና ተሳትፎ ነው” በሚል ሃሳብ ላይ ተግባቡ።

በዚህም መሠረት ሁለቱ ዶክተሮችና ጓዶቻቸው የግብጹ ፕሬዚዳንት ጀማል ዐብዱናሲር የሚያቀነቅኑትን “የዐረብ ሁለንተናዊነት” (Pan-Arabism) ጽንሰ ሐሳብ ተቀበሉ። በ1956 መግቢያ ላይ በዐረብኛ ስሙ “ሐረካት አል-ቀውሚይን አል-ዐረብ” (“የዐረብ ብሄራዊ ንቅናቄ”/Arab National Movement) ወይንም በአጭሩ “ሐረካ” እየተባለ የሚጠራ ድርጅት መሠረቱ። በዚህ ድርጅት አማካኝነትም ፍልስጥኤምን ነፃ ለማውጣት የሚደረገውን ትግል በራሳቸው መንገድ ያስኬዱት ጀመር። በርካታ ፍልስጥኤማዊያንም ድርጅቱን ተቀላቀሉ። ጆርጅ ሐበሽም የሐረካ ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጠ። ሙሕሲን ኢብራሂም ምክትል ሊቀመንበር ሆነ። ዶ/ር ዋዲ ሀዳድ ደግሞ የወታደራዊና የደህንነት ጉዳዮች ኃላፊ ሆነ።
(ይቀጥላል)
——–
አፈንዲ ሙተቂ
ታሕሳስ 4/2010
በሸገር ተጻፈ።

የሁለት ዶክተሮች ወግ (ክፍል ሁለት)

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

One Comment

  • እኔ ነኝ ባላገር commented on May 29, 2019 Reply

    አመሰግናለሁ እውቀት ማካፈል ከገንዘብ ይበልጣል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...