የዛሬ ወር ተኩል ገደማ ለሳምንታት ቆይታ ወደ አሜሪካ ሄጄ ነበር፡፡ የጉዞ ሃሳቤን የሰሙ እዚህም አዚያም ያሉ ዘመድና ወዳጆቼ እኔ ‹‹ልዋጭ ልዋጭ›› የምለውን የእቃ ውሰጂና አምጪልን ጥያቄያቸውን ጀመሩ፡፡
በርበሬና ሽሮን በጋላክሲ ስልክና በሌቫይስ ጅንስ የመለወጥ ጥያቄ፡፡
ቡላና ኮሰረትን በናይኪ ስኒከርና በሬይባን መነፀር የመለወጥ ጥያቄ፡፡
ከዚህም ከዚያም ከደወሉት ብዙ ሰዎች መሃከል አንዷ የአጎቴ ልጅ ሜሮን ነበረች፡፡ ቦስተን የምትኖረው ታላቅ እህቷ ጋር የምትልከውን ሽሮና በርበሬ መጠን ከነገረችኝ በኋላ ስንገናኝ በፅሁፍ የምትሰጠኝንና ይዤ መምጣት ያብኝን እቃ ዝርዝር ሳልጠይቃት ታንበለብለው ጀመር፡፡
‹‹ ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ ፋይቭ ስልክ…››
‹‹ ኮች ቦርሳ- ሰማያዊ ወይ አረንጓዴ..ጥቁር ምናምን እንዳትልክልኝ በናትሽ…!እሷ እዛ ከሄደች ስታይል ጠፍቶባታል…››
‹‹ቶፖች! የሰመር ቶፖች…ደማማቅ››
‹‹ኦቨር ኦል ጅንስ ሱሪዎች…››
‹‹ሄድ ባንዶች..››
‹‹ፈንዲ መነፀር- ባለ ሌፐርድ ፐሪንት››
‹‹ጄውለሪዎች…ሃብል፣ የእጅ፣ የጆሮ…;;
‹‹ወፋርራም ታይቶች…ባለዚፕ..ባለ ፐሪንት››
‹‹ደህና ቡትስ…በጣም ሳይረዝም…››
መቼም ቴሌ ደህና ወሬን እንጂ እንዲህ አይነቱን የልብ ካውያ ወሬ አይቆርጥምና አቋረጥኳት፡፡
‹‹ሜሪዬ የምትፅፊው ከሆነ ለኔ መንገሩ ምን አስፈለገ?››
‹‹አንቺ ስታይለኛ ስለሆንሽ አብረሻት ሾፕ እንድታረጊ ብዬ ነው ሂዊ..?!እሷ እኮ አሮጊቶች ቤት ነው መሰለኝ የምትገዛው የምትልከው ነገር ሁሉ ሁሌ ለሰራተኛችን አንደተሰጠ ነው…!በናትሽ ደህና ቦታ ውሰጃት….››
‹‹እ…ሺ…በቃ ፃፊውና አነበዋለሁ…አንድ ሁለት ቀን እዛ ማደሬ አይቀርም››
ስልኩ ተዘጋ፡፡
ከሶስት ቀናት በኋላ ከሰላሳ ምናምን ኪሎ በላይ ባልትና ተሸክሜ ቦስተን ገባሁ፡፡
የተላኩትን ሁሉ ለራሄልም ለሌሎም አከፋፍዬ ጨርሼ ሰነበትኩ፡፡
በሶስት ሳምንት ቆይታዬ ፤ እንኳን ከእኔ ጋር ገበያ ለገበያ ለመዞር ለአፍታ እንኳን፣ስታር ባክስ›› ቁጭ ብላ በወጉ ቡና ልታጣጣኝ ጊዜ ያልነበራት ራሄል ወደ አዲስ አበባ ልመለስ ሶስት ቀናት ሲቀሩኝ ፤ ሜሮን የላከችላትን ዝርዝር አውጥታ እያየች ስትጨነቅ በቀጠሮዬ ቤቷ ደረስኩ፡፡
‹‹መጣሽ…!?ጎሽ…ነይ!›› አለችኝና ወደ መኝታ ቤቷ እጄን ይዛ እያንደረደረች አስገባችኝ፡፡
‹‹ምንድነው?›› አልኩ አልጋዋ ጫፍ ላይ እየተቀመጥኩ::
‹‹ሂዊ፤ ምን መአት ነው ይዘሽብኝ የመጣሽው…?ሽሮና በርበሬው ቢቀርብኝ ይሻል ነበር›› ፊቷ ላይ ያለው ደም ደፍርሷል፡፡
‹‹ምን ሆነሻል ራሄል?›› አልኳት
‹‹ሜሮን እዚህ ያለው ኑሮ አይገባትም፡፡ ይሄው መቼም አንቺ የኔን ኑሮ አይተሸዋል፡፡ አረፍት የለኝም፡፡ አሁን ደግሞ ይቺን ሰመር ደህና ስራ እሰራለሁ ብዬ ባስብም የምሰራበት ሬስቶራንት ብዙም ስራ ስለሌለው ሺፍቴን በግማሽ ቀንሶታል…ቤት ኪራይ ራሱ እንዴት እንደምከፍል አላውቅም…..››
ደነገጥኩ፡፡
ዝም ብዬ ሳያት ቆየሁና፤
‹‹ራሄልዬ፤ በቃ ንገሪያታ! እህትሽ ናት ይገባታል…እኔም ሁኔታውን እነግራታለሁ…›› አልኩ ተነስቼ እጇን ይዤ፡፡
‹‹አሄሄ! አንቺ የኔን ቤተሰቦች አታውቂያቸውም፡፡ ዛሬም ድረስ ስቱኮ የአሜሪካ ጭቃ የሚመስላቸው ናቸው…አሜሪካ ዶላር ከበረዶ ጋር የሚዘንብበት ሀገር እንጂ ሰው የሚቸገርበት ሀገር አይመስላቸውም፡፡››
‹‹ ቢሆንም ሁኔታውን ብነግራቸው ይገባቸዋል›› አልኳት በአሜሪካ ጭቃ የምንጫወተው ትዝ ብለኝ ሳቄ እየመጣ፡፡
‹‹ አይ መግባት! … አሁን የዛሬ ሁለት ወር በየወሩ ከምልከው ብር በአሁኑ ስላልተሳካልኝ ብዬ መቶ ዶላር ቀንሼ ብልክ ›‹አንቺ በሚያብረቀርቅ ባቡር እየሄድሽ ቤተሰብሽን በችግር ትጠብሻለሽ›› ብላ አንዷ እክስቴ ፃፈችልኝ፡፡ እማምላክን!›› አለች እየሳቀች፡፡
መሳቋ ደስ አለኝና፤
‹‹አንቺ ነሻ! ማን የሚያብረቀርቅ ባቡር አጠገብ ፎቶ ተነስተሸ ፌስቡክ ለጥፊ አለሽ…?በመንግስት ባቡር አንቺ ምን አስደገፈሽ…?ሄድሽበት እንጂ አልገዛሽው!››
‹‹እውነት እኮ ይገርማል…የከተማ ደሃ እየተጋፋ በሚሄድበት ባቡር አጠገብ ፎቶ ተነስቼ ብለጥፍ ኢትዮጵያ የደላኝ ይመስላል…!›› ብላ ሳቀችና ቁምሳጥኗን ከፈተች፡፡
‹‹በይ አሁን ከዚህ ውስጥ እንመራርጥና ለዚያች ሞልቃቃ ይዘሽልኝ ትሄጃለሽ›› አለችና ልብስና ቦርሳዎች፣ ከዚያ ደግሞ ጫማዎች እያወጣች አልጋ ላይ መከመር ጀምረች፡፡
‹‹ያንቺን ልብስ?››
‹‹ምናባቴ ላድርግ ታዲያ! ካልላኩላት ምላሷን አልችለውም!›› ባለፈው አንድ ሱሪ ልኬላት ጠልታው ‹‹አሁን እኔም አሜሪካ እህት አለኝ ይባላል!›› አትለኝ መሰለሽ!?
ለሚቀጥሉት ሁለት ሰአታት ለሜሮን የሚላኩ የራሄልን አዳዲስና ‹‹ተቀባይነት›› ያላቸውን ልብሶች ስንመርጥ ቆየን፡፡
ራሄል በየመሃሉ በመጨነቅ ፊቷን እየቋጠረች
‹‹ይሄ ይደብራት ይሆን?››
‹‹ይሄ አሁን አዲሳባ ፋሽን ነው አይደል?››
‹‹ይሄ ውድ ነው አይደል ኢትዮጵያ?››
‹‹ይሄንን ቦይፍሬንዴ ነው ለልደቴ የሰጠኝ..ገና አላደረግኩትም…ብራንድ ጫማ ነው››
ስትል ቆይታ የምንችለውን ከመረጥን በኋላ ወደ ተላከላት ዝርዝር ስትመለስ ‹‹ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ ፋይቭ ስልክ›› የሚለውን አይታው ኩምትር ስትል አየኋት፡፡
‹‹ራሄል አታብዢው…በዚህ ሁኔታሽ ሰባት መቶ ስምንት መቶ ዶላር አውጥተሸ ስልክ መግዛት አትችይም፡፡ የያዘችው ስልክ እኮ ደህና ነው…!አይ ፎን አይደል?›› አልኳት እቃዎቹን እያስተካከልኩ፡፡
‹‹እህህ….ከጓደኞቿ እየተፎካከረች እኮ ነው…ሁሉም ጓደኞቿ ወንደምና እህት ውጪ አላቸው፡፡ የማይልኩላቸው ነገር የለም…!ስራቸው ውድ ካፌ ተቀምጦ በውድ ስልክ ፎቶ እየተነሱ ፌስቡክ ላይ መለጠፍ እኮ ነው….እንደው እግዜር አሳክቶልኝ እዚህ አምጥቼያት የአሜሪካ ኑሮ ደህና አድርጎ በቀጣልኝ!››
‹‹አሜሪካ መጥተሸ ተቀጪ ብትያት አሁን ታምናለች እሷ…?!›› አልኳት እዚህ ከመጣሁ ከብዙ ሰው በተደጋጋሚ የሰማሁትን ‹‹ሰውን አሜሪካ አምጥቶ የመቅጣት›› ወይም ‹‹መጥቶ ባየው›› ፅንሰ ሃሳብን ለመረዳት እየሞከርኩ፡፡
‹‹እዛ ሆና አይገባትም፡፡ እዚህ በገባች ማግስት ግን ይገባታል…አሁን ምን አሰብኩ መሰለሽ ይልቅ…››
‹‹እ….?››
‹‹ቦይፍሬንዴ ባለፈው ስልክ ሲቀይር ለማንኛውም ይቀመጥ ብሎ የተወው ኤልጂ ስልከ አለ፡፡ እሱን ልላክላት…›› አለችና ፌት ለፊት ካለው ኮመዲኖ መሳቢያ አንድ ሰፊና ረጅም ስልክ ይዛ መጣቸ፡፡
‹‹ያምራል አይደል?›› አለችኝ አንዴ ስልኩን አንዴ እኔን እያየች
‹‹ያምራል›› አልኩ ቶሎ ብዬ፡፡
እቃዎቹን ከሸካከፍን በኋላ መቶ ዶላር አብሬ እንድሰጣት ሰጥታኝ ወደ ቤቴ ሸኘችኝ፡፡
ከቀናት በኃላ አዲስ አበባ ስመለስ ኦጎቴ ቤት ሄድኩና ለሜሮን የተላኩትን እቃ አንድ በአንድ እያወጣሁ ሰጠኋት፡፡
መጀመሪያ ከእህቷ የተዘረፉትን ልብሶች ስታይ የሚከተሉትን ነገሮቸ አለች፤
‹‹ይሄ ቦርቃቃ ነው! እሱን ለማሰራት የማወጣው ገንዘብ ከልብሱ ዋጋ ይበልጣል››
‹‹ይሄ አልፎበታል››
‹‹ይሄ ደግሞ ምን ይመስላል…?ለኔ ከለር እንደማይሆን እያወቀች ምን አስላካት?!››
‹‹ታይቱ ደግሞ መሳሳቱ…ወፍራም አላልኳትም…?››
‹‹ይሄኛው ጅንስ ደግሞ ተቀዷል እንዴ! እንዴ…እዛም ሰልቫጅ ተራ አለ እንዴ! …ከሰልቫጅ ተራ ነው እንዴ የገዛችልኝ…?!››
ቀጥላ የራሄል ቦይፍሬንድ ለልደቷ ሰጥቷት ገና ያላደረገችውን ጫማ አየችና፤
‹‹ይሄ እንኳን ደህና እቃ ይመስላል ግን ኦልድ ስታይል ነው፡፡ በተለይ ከለሩ…ኡፍ…..እንቅልፍ ነው የሚስመጣው…!ጎደኛዬ ሰብሊ ይሄን ከለር ምን እንደምትለው ታውቂያለሽ ሂዊ?”
‹‹አላውቅም››
‹‹ቮሚት ከለር…! ለእናቷ እንሸጥላቸዋለን…በቻይና ጫማ ሲማረሩ ነበር››
ዝም ብዬ አያታለሁ፡፡
‹‹ሀብሎቹ ደግሞ በሙሉ አንድ አይነት! ምናለ የተለያየ ነገር ብትልክልኝ! ?>›
‹‹እኔ ይሄን የጆሮ አድርጌ ከቤት አልወጣም…!….ኡፍ በቃ ስልኩን ስጪኝ!›› አለችኝ
ሲሰርቅ እጅ ከፍንጅ እንደተያዘ ሰው ስቅቅ እያልኩ ስልኩን ከቦርሳዬ አውጥቼ ሰጠኋት፡፡
‹‹ምንድነው ይሄ?››
‹‹ስልኩ…››
‹‹ተሳስተሸ እንዳይሆን…የሌላ ሰው መሰለኝ?››
‹‹አይደለም ያንቺ ነው››
‹‹እኔ እኮ ጋላክሲ ነው ያልኳት››
‹‹እንጃ የሰጠችኝ ይሄን ነው››
‹‹ይሄማ ዩዝድ ነው!…ይሄን እዚህ ማስከፈቱ ራሱ መከራ ነው….!ምን አይነት ናት በማምላክ!;››
ልወጣ ስል ራሄል የቤት ኪራይ መክፍል ካለመቻሏ ጋር እየተገዳደረች የላከቻትን መቶ ዶላር አወጣሁና ‹‹ይሄም ላንቺ ነው›› ብዬ ሰጠኋት፡፡
እንደ ዋዛ አየቻትና ‹‹ብትተወው ይሻላት ነበር፡፡ ስም ነው የሚሆንብኝ፡፡ እኔ ለሷ በርበሬና ሽሮ ከዚህ በላይ አላወጣሁም እንዴ?! ›› አለች፡፡