ቀምጣላ ስድስተኛ ቤቷን በአዲስ አበባ የገዛችው ዘመን ያገነነናት ሙሰኛ የድሮ የትምህርት ቤት ጓደኛዬን ካገኘሁ ወዲህ የአርባ-ስልሳ ነገር ያነደኝ፣ የኮንዶሚኒየም ኪራይ ያንጨረጭረኝ ጀምሯል።
ልጅቱ አንድ ኮንዶሚኒየም፣ አንድ የሰንሻይን ሪል ሰቴት አፓርትማ፣ አንድ የፍሊንትስቶን ሆምስ ታወን ሃውስ፣ አንድ የማህበር ቤት፣ አንድ ሰበታ የሚገኝ የትየሌሌ ግቢ ያለው ሰርቪስ ቤት እና አሁን የምትኖርበት ጂ ፕላስ ምናምን ቤት አላት።
የተዛባ ነገር አለ። የተፋለሰ ነገር አለ። ልክ ያልሆነ ብዙ አለ።
ምክንያቱም ፤ የእሷ ስድስት ቤት የስልሳ ስድስት ቤት ኪራይ መገፍገፍ የመረራቸው ምስኪኖች ድርሻ ነው።
ከነሱ ተቀምቶ የተሰጣት ነው።
ከሃቀኛ፣ ከሠራተኛ ጎስቋሎች ተነጥቆ ‹‹እንካችሁ›› የተባለችው ነው።
ይሄን ባሰብኩ ጊዜ፤
‹‹የእኛስ ተራ መቼ ነው?››
‹‹ እሷ እና እነሱ ደጋግመው ሲበሉ እኛስ እጣ የሚወጣልን መቼ ነው?›› የሚሉ ጥያቄዎች ይሞግቱኝ ይዘዋል።
ከዚህ ተያይዞ ድሮ የሰማኋት ታሪክ ትዝ አለችኝ።
(የት ተገናኝተው እንደሆን እንጃ እንጂ) ጃንሆይና አንድ ተርታ ሰው የሳንቲም ቁማር (ድብ ድብ) እየተጫወቱ ነው።
ተርታው ሰው ሳንቲሟን ያጦዟትና ቀልበው፣ በመዳፋቸው ውስጥ ቀበሩና፣ ጃንሆይን “ጥሩ!…” ይሏቸዋል።
ጃንሆይ … “እኛ” ይላሉ።
ሳንቲሙ ሲገለበጥ… አንበሳ ይሆናል። ይሄኔ ጃንሆይ ፈጠን ብለው… “ታዲያስ! እኛ አንበሳ አይደለን?” ይመልሳሉ።
ተርታው ሰውዬ ተናድደው እንደገና ሳንቲሟን አጎኑና ቀልበው በመዳፋቸው ሸፍነው… “እሺ?! ጃንሆይ እንደገና ይጥሩ?…” ይሏቸዋል…
ጃንሆይ … አሁንም “እኛ” ይላሉ።
ሳንቲሙ ሲገለበጥ… ዘውድ ይሆናል። አሁንም ጃንሆይ ቀልጠፍ ብለው… “ዘውዱስ ቢሆን የኛ አይደል!?”ማለት።
ይሄን ጊዜ ሰውየው ብግን ይሉና…፤ “እንዴ! እኔ መቼ ነው የምበላው?” ሲሉ…
ጃንሆይ…
“በጠርዙ ሲቆም!” ብለው መለሱላቸው አሉ።
…ይህች ታሪክ ስጠይቅ ለነበረው ጊዜ የማያልፍበት ጥያቁ ወሽመጥ በጣሽ መልስ ትሰጥ ይመስለኛል።
አሁን ባለው ሁኔታ፤ የእኛ ተራ የሚደርሰው፣ እጣው የሚወጣልን፣ የምንበላው፤
የስበት ህግ ተሽሮ ሳንቲሙ በጠርዙ ሲቆም ብቻ ነው።
One Comment
“የአንባቢ ፀሐፊ “ጽሑፍ ያስደስተኛል ብሪቮ