በቀደም እኔና አዩ እራት ለመብላት አበሻ ምግብ ቤት ቁጭ ብለናል፤ አዩ ባልንጀራየ ናት ፤ ለስድስት ወራት ያክል ብንተዋወቅም ሙሉ ስሟን አልነገረችኝም፤ ሙሉ ስሟ “ አያልነሸ” ወይም “ አያንቱ” ሊሆን ይችላል።
ቅርብ ማዶ ካለው ጠረጴዛ ፊተለፊት ሁለት ፍቅረኛሞች ተቀምጠዋል፤ ሴቲቱ በሰውየው ትከሻ ላይ ዘንበል ብላ ታለቅሳለች ፤ ሰውየው በፈርጣማ ክንዱ አቅፎ እያባበላት ነው፤
“ልጂቱዋ ምን ሆና ነው እምትነፋረቀው?’ አልኳት አስናጋጂቱን።
“እጮኛዋ ነገ ወደ ኢትዮጵያ ሊሄድ ነው፤ ዘመቻ” አለች አስተናጋጄ ጠረጴዛውን እያስተካከለችኝልኝ ።
“ይገርማል! ሸገር ፤ መሀል ቦሌ ላይ የሚኖሩ ቤተሰቦችን ማየት የሚፈራ መአት ዲያስፖራ ባለበት አገር እንዲህ አይነት ቆራጥ ማየት ልብ ያሞቃል“ አለች አዩ።
“የጠረጴዛው ልብስ በጣም ነው የሚያምረው “ አልኩ ጨዋታ ለማስቀየስ ።
“አንተ መች ነው እምትዘምተው?”
<ምነው፥ የእዝን ቆሎየን ለመብላት ቸኮልሽ> ልላት ፈልጌ ተውኩት ።
“እኔኮ ባገሬ ድርሻየን ዘምቻለሁ”
“መቸ?” ፥ አፋጠጠችኝ
“ትንሽ ቆየት አለ”
“ባድሜ?”
“አይ! የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ”
“የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ላይ ደርሰህበታል ?’ አለች አይኖቿን በግርምት አፍጥጣ ።
“ሰባተኛው ዙር ደርሶብኛል ”
“በሕይወትህ ተደባድበህ ታውቃለህ?”
“ተደብድቤ አውቃለሁ፤ አጻፋውን ለመመለስ ግን ጊዜና አጋጣሚው አልፈቀደልኝም ”
“unbelievable !”
“ቤተሰቦቼ ባንድ ወገን ደብተራ ባንድ በኩል ቃልቻ ናቸው፤ ለማውጋት እንጂ ለመዋጋት የሚሆን ጂን ያልወረስኩት ለዚያ ይሆናል! ተረጂኝ”
ዝም አለች፤ በፊቷ ሞገስ ለማግኘት አንድ ነገር ለማድረግ ወሰንኩ፤ አስተናጋጂቱን ጠርቼ “ ዘማቹ ሰውየና ሚስቱ ያዘዙት ሂሳብ በኔ ነው “አልኩዋት፤
“አንድ ጎድን ጥብስ፤ አንድ ክትፎ፤ እና አንድ ሩዝ ባትክልት”
ሰውየው ከራቱ ጋር ደርቦ ስንቁን እንዳዘዘ ገባኝ።
ትንሽ ቆይቶ ፤ ወደ ተቀመጥንበት መጥቶ አመሰገነኝ ፥
“አንተ መሰዋእት እየከፈልህል እኛ ራት መከፈል አይበዛብንም” አልኩት፤ በውነት ግን ለራት የከፈልኩት ወደ ኢትዮጵያ ቢመነዘር ቆንጆ ቅጥቅጥ ባጃጅ ያስገዛል፤
“አየ! በእንባ ብዛት ሀሳቤን አስቀየረችኝ እኔማ ልዘምት ወስኘ ነበር” ሲለኝ ምን ልበል፤
በንባ ብዛት ማስቀየር የማልችለውን የጋብዝኩበትን ደረሰኝ እያየሁ ተከዝኩ፤
One Comment
አጅሬ በዉቄ በአሁን ሰዓት ብቸኛዉ የምታስቀኝ አንተ ብቻ ነህ
እጆችህ ይባረኩ