ምን ዓይነት ዘመን ነው፣ የዘመን ጉንድሽድሽ
ባንዳ እያከበረ፣ ጀግናን የሚያንቋሽሽ?
ኸረ መን ዘመን ነው፣ የዘመን ቅራሪ
ኮብል የሚያስጠርብ የጊዜያችን ዲግሪ
ምን ዓይነት ዘመን ነው፣ የዘመን እግረኛ
ስደት የሆነበት ብቸኛው መዳኛ
ምን ዓይነት፣
ምን ዓይነት
ምን ዓይነት ዘመን ነው፣
ዘመንን ለመስደብ የሚቃጣ አዋጅ የሚታወጅበት
የብሶት ግብስብስ የሚታጀልበት፤
ገጣሚ ነኝ በሚል የሚገጥመው ባጣ የተሰደረበት…
ብዬ ጠይቃለሁ፣ መላሽ በሌለበት!
ምን ዓይነት ዘመን ነው፣
ጠያቂው እንዳሸን አጉል በፈላበት
መላሽ እየጠፋ፣ መልስ የጎደለበት
ጥያቄው ነው ከባድ?
መላሹ አቅመ ቢስ?
ዘመኑ ነው መልስ አጥ?
ወይስ ለአድማጩ ነው ምላሹ ’ማይዋጥ
ምን ዓይነት ዘመን ነው፤
በእንዲህ ዓይነት ጥያቄ መልስ አጥቶ የሚናጥ?
ለምን ዓይነት ዘመን?…
መልሱ አይታወቅም ጥያቄው ይልቃል፣
ዘመኑ ያፈራው፣ ዘመናይ ጠያቂ ዘመን ይጠይቃል።
ኸረ ምን ዘመን ነው፣
የዘመን ምንነት የሚጠየቅበት?
አልፎ ሂያጅነቱ፣ ነግ የማይደገም-
መሆኑ ተረስቶ የሚፈተንበት?
ምን ዓይነት ዘመን ነው፣
የዘመን መፈተን አይነኬ ሆኖ
ሳያስቡ መኖር ያገኙትን ዘግኖ
እየጣሉ ማለፍ፣ አለመውደቅ ብቻ እውነት ነው ተብሎ
የሚታመንበት የዘመን ደበሎ?!
ምን ዓይነት?…… ምን ዓይነት?
ምን፣ ምን ዓይነት ዘመን፣
ዘመን ምላሽ አጥቶ
ጥያቄው ያለመልስ፤
ባክኖ ተንከራቶ
መልስ አልባው ጥያቄ፣ መልስ ሆኖ ተቆጥሮ
ተስፋ ቆጥሮ የሚያቆም የስንኝ ቋጠሮ!!