የእናንተን አላወቅም፤ እኔ ግን በቤቴ እና በቢሮዬ እጅግ መራራቅ…ብሎም በመንገዱ መጨናነቅ የተነሳ ከቤት ወደ ስራ፣ ከስራ ወደ ቤት ስሄድ የማጠፋው ጊዜ ቢደመር በአመት ውስጥ አንድ ሶስት ወሩን መንገድ ላይ ሳልሆን አልቀርም።
ለዚህ ነው አሁን አሁን መኖሪያዬ መንገድ ላይ እና ቢሮዬ ውስጥ የሆነ፣ ቤቴ ደግሞ ሲቀናኝ ሲቀናኝ የምውልበት አልጋዬን ብቻ የያዘ ማደሪያዬ መስሎ የሚሰማኝ…
የዛሬን አያድርገውና፣ እኛም እንዲህ ሳንባዛ፣ መኪናውም መሄጃ እስኪያጣ ሳይባዛ በፊት….የመንግስት ሰራተኛ የነበሩት እናት እና አባቴ ለምሳ ቤት መጥተው፣ በልተው ፣ ቡና አስፈልተው ጠጥተው…የቡና ቁርስ ቀማምሰው፣ ከልጆቻቸው ጋር አውርተው ቢሮ ይመለሱ ነበር። ከዚያ ደግሞ ማምሻውን ከስራ መልስ ከአስራ አንድ ሰአት በፊ ቤታቸወ ገብተው ፣ መክሰስ ቀማምሰው፣ ልጆቻቸውን ‹‹የቤት ስራ ስሩ…አጥኑ…›› ብለው ገስፀው፣ ጎረቤት ለቅሶ ወይ ሌላ ጉዳይ ካለ ጎራ ብለው ወይ ደግሞ ከወዳጅ ዘመዳቸው ጋር ሻይ ቡና ብለው በጣም ሳይመሽ ወደ ቤት ይመለሱ ነበር።
የብዙዎቻችን ወላጆች የሚያንደላቅቅ ቁሳዊ ሃብት አልነበራቸውም። በሕይወት ውስጥ ፋይዳ ላለውና ለዋናው ዋናው ነገር ግን ጊዜ ግን ነበራቸው።
የእኛ ጊዜ ይሄን ሁሉ ማህበራዊ እና ቤተሰባዊ ጊዜ ቀምቶናል። ሕይወታችን ስራ ላይ በመዋል እና ቤት ገብቶ በመተኛት ብቻ የተከፈለ ነው።
እናትና አባቶቻችን የነበራቸው ጊዜ የለንም።
የዛሬዎቹ ሰራተኞች….ደም ተፍተን የገዛነው ቤት ውስጥ የምናሳልፈው ጊዜ ጥቂት ነው።
የገቢያችንን ሁለት ሶስተኛ የሚሞጨልፈውን የቤት ኪራይ የምንገብርበት ቤታችን የምንሄደው ለመተኛት ነው።
አጠራቅመን የምንገዛው ሶፋ ላይ ከስራ መልስ ለመንደባለል …የደከመ ጎናችንን ለማሳረፍ ጊዜ የለንም።
ከስራ መልስ የቲቪ ፕሮግራሞችን አማርጦ በመመልከት ለመደሰት ጊዜ የለንም።
ከቢሮ መልስ ለማንበብ ከመንገድ የተረፈ ጊዘም፣ ጉልበትም የለንም። ከጎረቤት አንገናኝም። ከዘመድ ወዳጅ ቶሎ ቶሎ አንተያይም።
የእኛ ‹‹ዘመናዊ ኑሮ›› ይህንን ሁሉ ማህበራዊ እና ቤተሰባዊ ጊዜ ቀምቶናል።
የዛሬ ሰዎች ሰራተኞች ከሆንን ኑሯችንን በእነዚህ ምርጫዎች ብቻ ተገድቦብናል፤ ወይ ስራ ነን…ወይ ቤታችን ለመድረስ መንገድ ላይ ነን…ወይ በስንት እንግልት ቤት ደርሰን መኝታ ላይ ነን….