መነሻ ሃሳብ – “ዘ ሚድል” ተከታታይ ፊልም
“ፍ…ቅ…ር…ተ!”
ስሜ በሴት ሲጠራ ሰማሁና እጆቼን አጎንብሼ ከሰል ከምጎለጉልበት ማዳበሪያ ሳላወጣ ቀና አልኩ።
ሴት ናት።
ለሰፈራችን ከልክ በላይ የለበሰች፣ ለተቦዳደሰ ኬር መንገዳችን ከሚመጥነው በላይ ሸላይ ጫማ ያደረገች፣ …ቂቅ ያለች ሴት ናት።
ከመስታወት የተሰራ የሚመስለው ባለ ረጅም ስፒል ጫማዋ በሚፈቅድላት ፍጥነት፣ ሚዛኗን ላለመሳት አንዴ መሬቱን፣ አንዴ እኔን፣ አንዴ ሰፈሩን እያየች አጠገቤ ደረሰች።
አላምንም።
በጭራሽ አላምንም።
እስከዳር ናት።
የልጅነት ጓደኛዬ እስከዳር። ለአስራ ስምንት አመት ያላየኋት አብሮ አደጌ፣ አሜሪካ ከሄደች ወሬዋን ሰምቼ የማላውቀው የአሁኗ ዲያስፖራ፣ የጥንቷ ባልንጀራዬ እስከዳር ናት።
የአሜሪካ ኑሮ እንደ እጅ ስራ ፎቶ ሞላት፣ አቀላት፣ አሰለከካት እንጂ መሰረቱን በሳተ መልኩ አልተለወጠችም።
እስከዳር ናት!
በዚህ አኳሃኗ ልታቅፈኝ አጠገቤ ስትደረስ እጆቼ ከሰል ሲቦረቡሩ እንደነበር ታወሰኝ።
የለበስኩት ልጄ ያቀረሸበት ‹‹ቲቢን በጋራ እንከላከል›› የሚለው ቀበሌ የሰጠኝ ካኔተራዬ ትዝ አለኝ።
ጭኔ ላይ የተቦተረፈው ቱታዬ ተከሰተልኝ።
በምን አይነት ቀን ተያዝኩ..?.በምን አይነት አሳቻ ሰአት ላይ ተገኘሁ?
እግዜሩ ምን በደልኩት ! አስራ ስምንት አመት ጠብቆ ጡቶቻችን ቶሎ እንዲወጡልን የውሃ እናት ካጣባችኝ የልጅነት ጓደኛዬ፣ የዛሬ ዲያስፖራ-ዘናጭ-ቆንጆ–ብራም-ደስተኛ-ያለፈላት ሴት ….ፊት በዚህ ሁኔታ ያገናኘኛል?
ለእንዲህ ያለ ክፉ አጋጣሚ አሳልፎ ይሰጠኛል?
ሃሳቤ ሳያልቅ ደረሰችብኝ።
‹‹ወይኔ…ጥላሸት በጥላሸት…ምንድነው የምታቦኪው ፍቅርዬ?…ነይ ቀስ ብለሽ እቀፊኝ….›› አለችኝ።
እያፈርኩ መዳፎቼ ቢጫ እና ነጭ ሸሚዟን እንዳይነኩ አንጨፍርሬ ለወጉ አቀፍኳት።የባርኮንን ቅርሻት እያሰብኩ፣ የመንጎዳጎድ ጠረኔን እየገመትኩ ተሰቅቄ አቀፍኳት።
‹‹ ኦህ ማይ ጉድነስ…ፍቅርዬ…ደህና ነሽ…ምንድነው እንዲህ የተጎሳቆልሽው….ኑሮው ነው?…እኔማ አገኝሻለሁም አላልኩ….ምንድነው ይሄ ሁሉ? …ሰፈራችን የት ደረሰ…ምን ሆኖ ነው ሁሉ ነገር ብትንትኑ የወጣው…ሰዉስ የት ሄደ…›?›
የጥያቄ ጎርፍ።
‹‹የቱን ልመልስልሽ….ብዙ ጥያቄ ነው….ደህና ነሽ ግን…?መቼ መጣሽ?›› …አልኩ የተቦተረፈውን ቱታ ሱሪዬን በረጅም አሮጌ እና ቆሻሻ ካኔተራዬ ለመሸፈን እየሞከርኩ…ጎላ ድስትን በሚጢጢ ድስት ክዳን እንደመክደን እየሆነብኝ…
‹‹ሶስት ሳምንቴ…ዋው…እኔማ…››አለችኝ በአይኖቿ እያጠናችኝ። ሰው እንዴት በአስራ ስምንት አመት ውስጥ አይኑ በአንድ መስመር እንኳን አይከበብም…?የኔን አይኖች አስራ ስምንት መስመሮች ያጅቧቸዋል።
ቲሸርቴን ይበልጥ ወደ ታች ጎተትኩ።
‹‹ፍቅርዬ ምንድነው እንዲህ ውድቅድቅ ያልሽው?…እንዳገባሽ …እንደወለድሽ ሰምቼ ነበር…ምንድነው ግን በጣም እኮ ነው የተጎሳቆልሽው..ኑሮሽ ጥሩ አይደለም? .›› አለች ዙሪያ ገባውን እያየች።
ያላረጀ አይኗ ማየት ቢችል ኑሮዬ ጥሩ እንዳልሆነ መልስ አትፈልግም ነበር።
ቡና እና ሻይ ፊት ለፊት ቀልጦ አገር ያቀልጥ በነበረው መንደር ውስጥ በፍርስራሽ በተከበበ እና በግማሹ የፈረሰ ቤት ውስጥ ነው የምኖረው። ቤቴ በልማት ተገምጧል። ነገ ደግሞ ስልቅጥ ተደርጎ ይበላል።
ፈገግ ብዬ ዝም አልኳት፡፤
‹‹ እንግባ አይባልም ታዲያ እንግዳ?›› ስትለኝ በከሰል -ንክር እጄ እየመራሁ ቤት ወደምለው የግድግዳ እና የጣሪያ ድምር ወሰድኳት።
ገባን።
እፈረሰው ቤቴ ገባን።
ሳሎን ብለን የምናጋንናት ሶሰት በሶስት ክፍላችን ውስጥ ከሞቱት አባት እና እናቴ ከወረስኳቸው ፎቴዎች ሁለቱ አሉ። ሌላው ለወሬ አይበቃም እና ይቅርባችሁ።
እኔና ባሌ በርሄ…ቤሪዬ… ከስድስት ወር ልጃችን ጋር በንፅፅር ሳሎኑን ፈረስ ያስጋልባል በምታሰኝ በቅርፅ ለቱቦ በምትቀርብ ክፍል እንተኛለን።
ትልልቆቹ ልጆቻችን ሰላምሃል እና ዳንኤል ሳሎን ይተኛሉ።
ይሄው ነው።
‹‹አይ ካንት ብሊቭ እስከዛሬ እዚህ ቤት እንደምትኖሪ…!ልጆች ሆነን እዚህ ሳሎን ጋሽ አባይ እጅ በጆሮ ያስያዙን ትዝ ይልሻል?›› አለችኝ።
‹‹እህ…አዎ… ዛሬ ደግሞ እኛን ኑሮ እጅ በጆሮ አሲዞናል።…
ያው የቀበሌ ቤት አይደል…አዲሳባ ዛሬ ለእኛ አይነቱ ቦታ የላትም…ስለዚህ የቤተሰብ ቀበሌ ቤት ወርሰን እንኖራለን…እንኖር ነበር…አሁን እንደምታይው ነው…ሰፈሩ ሁሉ ፈርሶ…ሰዉ ሁላ…››
‹‹አይ ኖው! ዋር ዞን እኮ ነው ሚመስለው! ያልደወልኩልት ሰው የለም እኮ…ግን ሁሉም ሰው ከዚህ ሰፈር እንደወጣ ሰማሁ። ለምሳሌ ሃውልት ቦሌ ምን የመሰለ ቤት ሰርታለች አሉኝ። ሰመረ እና ቢኒ ሁለቱም አግብተው ገርጂ መሆናቸው ሰምቻለሁ። ..ፈተለ አሜሪካ ናት… ራሄል ስዊድን ነው ምትኖረው…ሌላ…ሌላ…ኦ…ታሪኳ እንኳን ከዛ መቃብር ከሚመስል ቤት ወጥታ ሰሚት ምን የመሰለ ፓላስ ውስጥ መሰለሽ ምትኖረው….››
ወደ ላይ ሊለኝ ፈለገ።
እሷ አንድ ቦታ ላይ ሩጫ ጀምረን ጥለውኝ የሄዱትን፣ ደርበውኝ የሮጡትን የሰፈራችንን ልጆች የዛሬ ኑሮ ስትነገረኝ ወደ ላይ ሊለኝ ፈለገ።
እሷ አንድ ቦታ ላይ ሩጫ ጀምረን ጥለውኝ የሄዱትን፣ ደርበውኝ የሮጡትን የሰፈራችንን ልጆች የዛሬ ኑሮ ስትነገረኝ ወደ ላይ ሊለኝ ፈለገ።
ስሜቴ የገባት አልመሰለኝም። ይሄ አሜሪካ የስሜት ማንበቢያን በቀዶ ጥገና ያስወጣል እንዴ!
ቀጠለች።
‹‹..ግን ፍቅር…ምን ሆነሽ ነው ያ ሁሉ ሰው ሲወጣ አንቺ ብቻ እኮ የቀረሽው…ማለቴ…ኦልሞስት ትዌንቲ ይርስ…ዛት ኢዝ ኤ ሎንግ ታይም ኖት ቱ ቼንጅ…መቼም ህልምሽ ይሄ አይመስለኝም…ምን ሆንሽ…?››
‹‹ለስላሳ ነገር ላምጣልሽሽ› አልኳት ፍንጥር ብዬ ተነስቼ።
‹‹እ..?.››
‹‹ለስላሳ ላምጣልሽ…ምን ይሁንልሽ…?››
‹‹ኦ ኖ…ለስላሳ አልጠጣም…ዳይት ላይ ነኝ…አታይኝም ተዝረጥርጬ…›› አለችኝ። ልብሷ ብቻ ሳይሆን ቆዳዋ እንደጠበባት ያስተዋልኩት ገና አሁን ነው።
‹‹አሜሪካ ያወፍራል መሰለኝ…››
‹‹አዎ…ምግቡ…ዝም ብለን በመኪና ስለምንዞር በዚያ ላይ…በነገርሽ ላይ…መኪና ያቆምኩት በፊት ጠጅ ቤት የነበረበት ቦታ ነው…ሴፍ ነው አይደል….?የሆኑ ልጆች እንደ ጉድ ሲያዩኝ ነበር…››
ሳቅ አልኩና ‹‹ሰላም ነው…ምንም አይሆንም…እና ምንም አትበይም…?ባዶ ቤት አጉል ሰአት መጣሽ….›› አልኳት።
‹‹ኖ ዛት ኢዝ ሶ ኦኬ! ይልቅ…ማታ እንውጣ…አንቺም ፈታ በይ…ቀና ቀና ብሏል ዘፋኙ…›› አለች ብድግ ብላ::
‹ማነው እሱ ደግሞ?››
‹‹አብርሃም ወልዴ ነው ማነው?…አይ ላቭ ዛት ሶንግ!››
‹‹እሺ…ግን ባሌን ልንገረው መጀመሪያ…›› አልኩ እያቅማማሁ። የማስበው ልለብሰው ስለምችለው ልብስ ነው። የማስበው ስለተንጨበረረው ፀጉሬ ነው። ታኮዋ ስለላላችው ብቸኛዋ ‹‹የውጪ›› ጫማዬ ነው።
‹‹ኦ ማይ ጋድ! ዋት ኢዝ ዚስ…ናይንቲን ሰርቲስ…?የሱን ፈቃድ መጠየቅ አለብሽ እንዴ…?››
‹‹ እንዴ እስኩ…ትዳር እኮ ነው…በዛ ላይ ህፃን ልጅ አለኝ…መያዝ አለበት››
‹‹ቢሆንም…ኤኒ ዌይ…እስካሁን አለመጠየቄ ይገርማል…ማነው ስሙ ባልሽ?…››
‹‹በርሄ …በርሄ ይባላል››
ልክ እንዲህ ስላት፤ እጆቿን እያማታች፣ በሹል ጫማዋ የተቦረበረ ሊሾ መሬቴን እየደቃቸች ‹‹ኖ ዌይ!…›. አለች ።
‹‹ምነው…አታውቂም ነበር…?ቢሪን እንዳገባሁ…››አልኳት ፊቷን እየሰለልኩ። የዋሸችኝ መሰለኝ፡፤
‹‹ በጭራሽ….!ታዲያ የሰፈር ልጅ…ያውም የእቃ እቃ ባልሽን አግብተሸ ነዋ እዚህ ተቀብረሽ የቀረሽው…ወይኔ በጣም ይገርማል…በጣም….››
ሳትጨርስ ልጄ አለቀሰ።
በሕይወቴ ‹‹ እሰይ ልጄ አለቀሰ›› የሚያስብለኝ አጋጣሚ ይፈጠራል ብዬ አስቤም አላውቅ ግን ተፈጠረ።
በቆመችበት ትችያት አንስቼ ላባብለው ወደ መኝታ ‹‹ክፍሌ›› ሮጥኩ።