Tidarfelagi.com

የዋለልኝ መኰንን አጭር የትግል ታሪክ

ዋለልኝ መኰንን በድሮው አጠራር በወሎ ጠቅላይ ግዛት በደብረሲና ወረዳ ከአባቱ ከአቶ መኰንን ካሣና ከእናቱ ከወይዘሮ ዘነበች ግዛው መጋቢት 11 ቀን 1938 ዓመተ ምህረት ተወለደ። ዋለልኝ መኰንንም በደሴ ከተማ በሚገኘው የንጉሥ ሚካኤል ተምህርት ቤት አንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ከዚህም በመቀጠል መስከረም 1954 ዓመተ ምህረት ደሴ ወይዘሮ ስሕን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ተምህርት ቤት ትምህርቱን ቀጠለ። በዚህ አጋጣሚ በ 1950 ዎቹ ውስጥ ሎተሪ ለዋለልኝ መኰንን አሥር ሽህ የኢትዮጵያ ብር ደርሶት ነበር ገንዘቡን ግን የተቸገሩ ስዎችን በመርዳት ተጠቅሞበታል። ዋለልኝ የ12ኛ ደረጃ ትምሕርቱን ያጠናቀቀው በ 1958 በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ስር ይተዳደር በነበርው በልዑል በዕደማርያም ቅድመ ዝግጅት ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። በዚህ ትምህርት ቤት ቆይታው በሥነ ፅሁፍ ዝግጅት የላቀ ሚና ተጫውቷል። የክርክር ክበብ ምክትልና ዋና ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግሏል። በዚሁ ክበብ አማካኝነት በተለይም የሥነ አመክኗዊ /Logic / ውይይት አካሄድን ልቅም አድርጐ እንደተማረ ይነገርለታል። ትምህርት ቤቱ ዋለልኝን ተከራካሪ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ፀሃፊም እንዲሆን ረድቶታል። በሁለት ዓመት ቆይታው የትምህርት ቤቱ የጋዜጣ ረዳት አዘጋጅ በመሆን አገልገሏል። ጥሩ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ችሎታ ያለው ፀሃፊ እንደነበረ ጹሁፎቹ ምስክር ናቸው። የአጻጻፉ ሥልት ከእነ ኃይሉ ገበረዮሐንስና ፀጋዬ ገብረ መድህን ሰልፍ ላይ እንደ ነበር ጓደኞቹ ይናገራሉ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከተቀላቀለ በኋላ፣ በ ሕዳር 18, 1961 ዓመተ ምሕረት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በተደረገው የሥነ ጽሁፍ ውድድር “የአዚናራው እሥረኛ” በሚል አርእስት ኢትዮጵያውያንን ከጣሊያን ወታደር ጋር ያደረጉትን ተጋድሎ፣ መስዋዕትነት፣ ጀግንነት፣ ለአገር ታማኝነትና ፍቅርን የሚያሳይ ሰነ ጽሁፍ ጽፎ ከተወዳዳሪዎቹ ውስጥ የአንደኝነት ማዕረግ በመጐናጽፉ ሽልማት አግኝቷል። በየዓመቱ በሚከበረው የዩኒቨርሲቲው ቀን ላይ በመወዳደር ካሸነፉት ስመጥር ገጣሚዎችና ባለቅኔዎች አንዱ ዋለልኝ መኰንን ነበር። በዚህ ጽሁፍ ምክንያት አገርና ሕዝብን ለመበጥበጥ በሚል ክስ ዋለልኝ መኰንን፣ ሄኖክ ክፍሌ፣ ታምራት ከበደ፣ ጌታቸው ሻረው፣ ፋንታሁን ጥሩነህ፣ አያሌው አክሎግና ገዘኸኝ መኰንን የተባሉት የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች አምስት ዓመት ተፈርዶባቸው አዲስ አበባ ከርቸሌ ከቆዩ በኋላ ተለቀዋል።

ዋለልኝ መኰንን በዚሁ የኢትዮጵያን አርሶ አድሮችና ላበ አድሮች ነፃ ለማውጣት በ60ዎቹ ውስጥ በተደረገው የኢትዮጵያ ወጣቶች ትግል ውስጥ ዓብይ ሚና የተጫወተ ወጣት ነው። ጥላሁን ግዛው የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ፕሬዝዳንት ሆኖ ከተመረጠ በኋላ ባደረገው ከፍተኛ የትግል ተሳትፎ ከባድ ክትትል ይደረግበት ነበር። አፍንጮ በር አካባቢ ታህሳስ 19, 1961 ዓ.ም ጥላሁን ግዛው በጥይት ይመታል። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ሲፈጠር ዋለልኝ መኰንን አምስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ቤቱ ከጓደኞቹ ጋር ነበር። አንድ ወጣት ወደ ቤት ይመጣና ስለ ጥላሁን ግዛው በጥይት መመታት ይነግራቸዋል። እነሱም በድንጋጤ ተያይዘው ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ይሄዳሉ። ሐኪሞቹ ሕይወቱን ለማትረፍ ሞክረው እንዳልተሳካላቸው ይነግሯቸዋል።በዚህ ወቅት ዋለልኝና ጓደኞቹ የጥላሁንን አስከሬን ከሆስፒታሉ በመውሰድ ዩኒቨርስቲው ውስጥ ቅጥር ግቢ Morgue ውስጥ በስርዓት ያስቀምጡታል። ከዚህ በኋላ የተቃውሞ ትዕይንትና የቀብሩን ሥርዓት ዝግጅት ያደርጋሉ። ለኮሌጅና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መልዕክቶችን ያስተላልፋሉ። የጥላሁን ሞት ትግላቸውን እንደማይገታው፣ ጥላሁን ቢሞት ሽህ ጥላሁኖች እንደሚፈጥሩ በመግለጽ ጽሁፎችን በሕዝብ መሃል ያሰራጫሉ። በዩኒቨርስቲው ውስጥ ያለውን የጥላሁንን አስከሬን ለመውሰድ ወታደሮች በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ይገባሉ። በዚህ አጋጣሚ ዋለልኝ ከፎቅ ላይ ሆኖ በድምፅ ማጉያ ጥላሁንን የሚቀብሩት የትግል ጓዶቹና ሕይዎቱን የከፈለለት ሕዝብ እንጂ ገዳዮቹ መቅበር እንደማይችሉ ይናገራል። የክብር ዘበኛ ወታደሮች በተማሪዎቹ ላይ ተኩስ ከፍተው አበበ በርሔ፣ ስብሃቱ ውብነህ፣ ጀማል ያሲን የተባሉ ተማሪዎችን ይገላሉ። በዚያን በሽብር ወቅት ዋለልኝ መኰንን ይተርፋል ያለ ሰው አልነበረም። ነገር ግን ዋለልኝና ጓደኞቹ ወደ ኮልፌ የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ማሰልጠኛ ቅጥር ግቢ ውስጥ ይታሰራሉ። ዋለልኝ ከአሁን በፊት በገደብ ስለተለቀቀ እንደገና ወደ ከርቸሌ እስር ቤት ይላካል። በአዲስ አበባ ዩኒበርስቲ ማህበርና(USUAA) በብሔራዊ የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማህበር(NUEUS) በከፍተኛ አመራር አባልነት ሚና ተጫውቷል። ከአንድ ጓድኛው ጋር በተደረግ ቃለ መጠይቅ ስለዋለልኝ ይህን ተናግረዋል። በጽሁፍ ችሎታ ይደነቅ የነበረው ዶክተር እሸቱ ጮሌ ነበር። ቀጥሎ በጸሃፊነቱ የማስታውሰው ዋለልኝ መኰንን ነበር ። የቃላት አጠቃቀሙና የሐሳብ ፍስቱ(Flow) ልዩ ነበር ብለዋል።

ዋለልኝ መኰንን ከእስር ቤት ከተለቀቀ በኋላ የተማሪዎቹ ልሳን የነበረው ታገል መጽሄት ታገደ። ዋለልኝ መኰንንም እንደዚሁ!! ከትምህርት ቤቱ እገዳ በኋላ፤ በወቅቱ የመንገድ ማመላለሻ አስተዳደር ተብሎ ይጠራ የነበረው መንግሥታዊ ድርጅት ሥራአስኪያጅ አቶ ሽመልስ አዱኛ ሥራ እንዲጀምር ዕድል ይሰጡታል። በዚሁ ድርጅት ሥራ እየሰራ እያለ ብርሃነ መስቀል ረዳና ሌሎች የትግል ጓዶቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ድርጅት መሥራች ጉባዔ ስብስባ በርሊን ላይ በመጥራታችው፤ ዋለልኝም በዚህ ስብስባ ላይ ለመገኘት ወሰነ። ወደ ስብሰባው ለመቀላቀል አውሮፕላን ከመጥለፍ ሌላ አማራጭ አልነበረውም። ሕዳር 29, 1965 ዓመተ ምሕረት ከጥዋቱ አንድ ስዓት ተኩል ላይ ከአዲስ አበባ ተነስቶ (በአሥመራ በኩል ወደ አቴንስ ሮም ፓሪስ) ለመሄድ የተነሳውን የበረራ ቁጥር 708 ቦይንግ ጄት አውሮፕላን፣ ዋለልኝ መኰንን፣ ማርታ መብራቱ፣ታደለች ኪዳነ ማርያም ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ጌታቸው ሀብቴ፣ ዮሐንስ ፈቃዱና ተስፉ ቢረጋ ሊያስገድዱት ሞክረው ባለመሳካቱ ታደለች ኪዳነ ማርያም ስትተርፍ ዋለልኝ መኰንን እና ሌሎቹ በጸጥታ አስከባሪዎች በተተኮሰ ጥይት ሕይዎታቸው አልፏል።

አባቱ አቶ መኰንን ካሣ ከአዲስ አበባ በልጅ ልጃቸው ስለአደጋው ሁኔታ ስለተገለጸላቸው ከደሴ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ከቀዳማዊ ምንሊክ ሆስፒታል አስከሬኑን ተረክበዋል። ከአዲስ አበባ እስከ ደሴ ባለው አውራጐዳና ላይ ችግር ቢፈጥር ሃላፊነቱን አቶ መኰንን ካሣ እንደሚወስዱ በጊዜው የፀጥታው ክፍል ሃላፊ የነበሩት ባለስልጣናት ግዴታ አስፈርመዋቸው ነው ጉዞ ወደ ደሴ የጀመሩት። በደሴ ከተማ የነበረው የፀጥታ አጠባበቅ የተጠናከር ቢሆንም የወይዘሮ ስሕን ትምህርት ቤት ተማሪዎች የትግል ጓዶቹ፣ ዘመድ አዝማድ በተገኘበት በመድሃኒ ዓለም ቤተክርስቲያን በክብር አርፏል።የሚገርመው ነገር በመንግሥት ላይ ያመፅ በመባል ፍትሃት አልተደረገለትም። ዋለልኝ መኰንን በአንዳንድ ግለስቦች እንደ ተራ አወሮፕላን ጠላፊ ቢታይም በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት በተደረገው ትግል ታሪክ ውስጥ ያደረገው ግንባር ቀደም ተሳትፎውና የብዕሩ ለዛ ሚዛናቸው የደፋ ነው።

2 Comments

  • Mynameisaraya11@gmail.com'
    ARAYA KIROS commented on May 28, 2018 Reply

    Thank you ….. i was fully blind abt his real history . Now atleast i decide to read more and further……

  • ትግስት አለሙ commented on December 22, 2019 Reply

    ተመችቶኝአል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...