በድሮ ጊዜ በኢትዮጵያ ባንዳንድ ገጠሮች ውስጥ “ወፋ” የሚባል ልማድ ነበር። ያንድ ቀበሌ ባላገሮች ከወንዝ ወዲህ ማዶ እና ወድያ ማዶ ተሰላልፈው በጩቤ በጦር በዱላ ይከሳከሳሉ። አንድ ባላገር ከገበያ ሲመለስ የወፋ ጦርነት ሲካሄድ ከተመለከተ ቆም ብሎ ቅርጫቱን ያስቀምጣል። ከዚያ በቅርብ ከሚያገኘው ጎራ ተቀላቅሎ ትንሽ ተደባድቦ መንገዱን ይቀጥላል። የዱላ ጠበል ጠዲቅ እንደመቅመስ ነው።
ጦርነቱ ለርስት ወይም ለክብር የሚደረግ አልነበረም። በዛሬ አይን ስንመዝነው: ያለ ምንም አላማ የሚደረግ ውጊያ ነበር ማለት ይቻላል።
ይህንን ልማድ ያስቆሙት አራዳው ልጅ ኢያሱ ናቸው ይባላል። ልኡሉ ባላገሮችን ሰብስበው ለምን እንደሚጋደሉ ሲጠይቁዋቸው:
” ሁሌም በበልግ ላይ ደም ካልፈሰሰ ቆሌዋ ትቆጣለች። መሬቱም እህል አይለግስም” ብለው መለሱላቸው።
በዚህ ምላሽ የተገረሙት ልጅ ኢያሱ” ታድያ ደም ለማፍሰስ ከሆነ ይሄ ሁሉ አርሶ የሚያበላ ወጣት ለምን ያልቃል? ለቆሌዋ አንድ የጃጀ ሽማግሌ መርጣችሁ አታርዱላትም? “አሉ ይባላል።
የወፋ ልማድ በልጅ ኢያሱ ከተደመሰሰ ከብዙ ዘመን በሁዋላ በፌስቡክ ላይ ትንሳኤ ያገኘ ይመስላል። ፌስቡክ ላይ ውይይት የለም። ሙግት አይታሰብም። ንግግር የለም። ያለው አላማ የለሽ ክርክር ነው። በመሰረቱ ክርክር የሚለው ቃል ራሱ በድሮ አማርኛ ጦርነት ማለት ነበር። በእምባቦ ጦርነት ዋዜማ : የንጉስ ምኒልክ ገንቦ ተሸካሚ ሴቶች ለጠመንጃ የሚሆን ባሩድ( ዳሂራ) ሲቀምሙ:-
“ጎበዝ ተሰብሰቡ እንውቀጥ ዳሂራ
ክርክር አይቀርም ከራስ አዳል ጋራ”
ብለው የዘፈኑትን ያስታውሱዋል።” ክርክር አይቀርም “ሲሉ ጦርነት አይቀርም ማለታቸው ነው።
ፌስቡክ ላይ ክርክር ነፍ ነው። ማንኛውም አይነት ርእስ ህዝብን ወዲህና ወዲያ አቧድኖ የሚያፋልም የክርክር ምንጭ የመሆን አቅም አለው። ለምሳሌ ሰኞ እለት ኢንጂነር ስመኘው የክርክር ምንጭ ሆኖ ይነሳል። ዜጎች በጉዳዩ ላይ መላምታቸውን ሴራቸውን ግምታቸውን አልፎ አልፎም ሀሳባቸውን አቅርበው ይከራከርሉ። እልል ያለ ፍረጃ እና ጠገራ ስድብ ከያቅጣጫው ይጎርፋል። በመጨረሻ የጋራ ግንዛቤ ጠብ ሳይል ቀኑ ያልፋል። ዜጎች በዘለፋ ቆስለው: ባይሞቱም የአእምሮ ሰላማቸውን ገድለው የቀን ራስ ምታታቸውን ተቀብለው ወደ ምኝታቸው ያዘግማሉ። በማግስቱ ባዲስ ጉልበት ለአዲስ ክርክር ተዘጋጅተው ይነሳሉ።
የፌስቡክን አላማቢስ ጦርነት እንደ ወፋ ውጊያ ባዋጅ ማስቆም አይታሰብም። ይሁን እንጂ በጦርነቱ በተዋጊነትም ሆነ በገላጋይነት ባለመሳተፍ ለሰላም አስተዋጽዖ ማድረግ ይቻላል።
በነገራችን ላይ በፅሁፌ መግቢያ ላይ የወፋ ልማድ ይዘወተርባቸው የነበሩት ቦታዎች በስም ከመጥቀስ የተቆጠብኩት ሆን ብየ ነው። ሳር ቅጠሉ ከብሄር ኩራትና ውርደት አንፃር በሚመዘንበት በዚህ ዘመን የሆነ ቦታ መጥቀስ በራሱ እልም ላለ ጦርነት መነሻ ሊሆን ይችላል። እና ክርክር የሚያወግዝ ፅሁፍ እንዴት የክርክር ሰበብ ያቀብላል? 🙂