ትላንትና ከባልንጀራየ ምኡዝ ጋር ተገናኝተን ቢራ ወይንና የመሳሰሉትን አልኮሎች ስንጠጣ:-አገርን በፍቅር ስለማስተዳደር አሰፈላጊነት ” በሰፊው ሰበክሁለት። እሱ እያዛጋና እየተቅበጠበጠ ሲሰማኝ ቆይቶ ሳያስጨርሰኝ የሚከተለውን ቀደዳ ቀደደ።
“ማኪያቬሊ ስለተባለ ዝነኛ ደራሲ ሰምተህ ይሆን? ስለስልጣን ባህርይ እንደ ሌሎች ሳያለባብስ እቅጯን ፅፏል!! ይህ ሀቀኛ ጥልያን በፃፈው ድርሳን ውስጥ እንዲህ እምትል ጥቅስ ትዝ ትለኛለች:-የታጠቁ ነቢያት ሁሉ ሲያሸንፉ ያልታጠቁ ነቢያት ግን ተሸንፈዋል”
” ሰውየው ምን ለማለት ፈልጎ መሰለህ ? አሪፍ መሪ ነህ እንበል!! አገርን የሚያበለፅግ የህዝብን ኑሮ የሚያሻሽል ሀሳብ የምታፈልቅ መሪ ነህ እንበል። ፍቅርና እውቀት የሚገባቸውን ዜጎች በስብከት ልትለውጥ ትችላለህ። ግን ይሄ በቂ አይደለም!! ገገማው እብሪተኛው ጦር-ጠማሹ ስለፍቅር ብትሰብከው መስሚያው ኮብልስቶን ነው!! አገር ወደ ሁዋላ ስትሄድ የሚያተርፉ ሰዎች ይነሱብሃል። ከተሳካላቸው ከምትሰብከበት መድረክ ላይ ባፍጢምህ ይደፉሃል። እና ራስህን እና ሀሳብህን የሚታደግ ጉልበት ከሌለህ ወዮልህ!! አየህ!!! ቅዱስ ሀሳብ በራሱ ጊዜ እንደ ተስቦ ካንዱ ወዳንዱ አይጋባም። በሌሎች ጭንቅላት ላይ እንደዘውድ ልትጭነው ይገባል። ይህን ደሞ ያለ ሀይል አይታሰብም። አብርሃም ሊንከን የሚባል ያሜሪካ መሪ -ባሮችን ነፃ የሚያወጣ ፖሊሲ ነደፈ። ይህ ለባሮችና ብዝበዛን ለሚጠሉ ነጮች የምስራች ነበር። ባርያ ፈንጋይ ዜጎች ግን አምርረው ተቃውመታል። እና አብርሽ ቅዱስ ሀሳቡን ለማፅደቅ ሰይፍ ማንሳት ነበረበት።
የጥጃ ሳሩ መምሬ ማምሻ
ወዲህ በዳዊት ወዲህ በጋሻ
የምትል ጥንታዊ ዘፈን አለች ። መምሬ ማምሻ “ጥጃ ሳር ” በተባለ ጎጥ ውስጥ የሚኖሩ ነቄ ካህን ናቸው። ገጣሚው እንደነገረን መምሩ ዳዊት ብቻ ሳይሆን ጋሻም ነበራቸው። ገጣሚው ለግጥም ምጣኔ ስላልተመቼው ዘልሎት ነው እንጂ ጦርም ሳይኖራቸው አይቀርም። በማኪያቬሊ አገላለፅ መምሬ ማምሻ ታጣቂ ነቢይ ናቸው። በሽፍቶች ሰፈር ውስጥ ስትኖር ትጥቅ እንጅ እንጂ ፅድቅ እድሜ አያረዝምም!! ” በሞት ጥላ መካከል እንኳን ብሄድ አንተ ከኔጋ ነህና ክፉ አልፈራም” የሚለውን የዳዊት ጥቅስ መድገም ያባት ነው።
ግን በቂ አይደለም። ለምንም ለምንም-በሞት ጥላ መከከል ሲያልፉ ጋሻና ጦር ማንገብ አይከፋም። እና ምን ልልህ ነው?! ፍቅር ለማይዘልቀው ፍቅር መስበክ የሰነፍ ነው። መገደል መሸነፍ ነው!! ”