Tidarfelagi.com

ወደ እሷው ጉዞ

“ስሟ ግን ማነው?” አልኩት አቡሽን

“እብድ ደግሞ ስም አለው? አንተ ልጅ ዛሬ ምን ሆነሃል? ልታብድ ነው እንዴ?” መለሰልኝ።
ላብድ መሆኔን እኔም ጠርጥሪያለሁ። ማታ ሰክሬ ነው ብዬ ያባበልኩት ቅዠቴ አድሮ ከህሊናዬ ካልጠፋ ለማበድ እየተቃረብኩ መሆን አለበት።ባለፈ ለሊት ሰማይ ተቀዶ በሚወርደው ዶፍ እየታጠብኩ፣ በውሃ መያዣ ፕላስቲክ በያዝኳት አረቄ ጉሮሮዬን እያጠብኩ፣ በስካር እዚህና እዚያ እየረገጥኩ ወደቤቴ ልገባ ስል ነበር ያየኋት። እርቃኗን መንገዱ ዳር ቆማ ዝናብ ትመታለች። ፍፁም እርቃኗን!! ከላይ ወደታች አስተዋልኳት።

ፀጉሯ የዝናቡን ውሃ እያዘለ አሁንም አሁንም በረዣዥም የእጅ ጣቶቿ ስትሞዥቀው ውሃው በየአቅጣጫው ይረጫል። ከፊቷ የሚወርደው ዝናብ በረዥም አንገቷ ተንደርድሮ የተሰደሩ ጡቶቿ ላይ ይደርስና በሾሉት የጡቷ ጫፎች ጠብ……ጠብ…… እያለ ይወርዳል። እንደዘበት ከፈት ያደረገቻቸው ረዣዥም ውብ እግሮቿ፣ ውሃውን ከአካሏ ስታራግፍ የምትንጠው ቀጭን ወገቧ፣ በተንቀሳቀሰች ቁጥር ላይ ታች የሚለው ተለቅ ያለ መቀመጫዋ … አይኔ በሰውነቷ ውበት ፈዞ የሚያርፍበት ቦታ ጠፍቶት ገላዋ ላይ ሲንከራተት አየችኝ። ደነገጠች። ግን አልሮጠችም። አቅጣጫ ቀይራ የቀድሞ ጨዋታዋን ከዝናቡ ጋር ቀጠለች። ጀርባዋን ሰጠችኝ። እሷ ስለማታየኝ የተደበቀች መስሏት ይሆን? ዓይኔ ላይ የበራ የመኪና መብራት ነበር አይኔን ከሷ እንድነቅል ያደረገኝ። ከመሃል መንገድ ፈንጠር ብዬ ጥግ ያዝኩ። መኪናው ካለፈ በኋላ ወደነበረችበት አቅጣጫ ዞርኩ። አልነበረችም።

—እሷ—
እሷ እብድ ናት። ድፍን አውቶቢስ ተራ የሚያውቃት እና የሚፈራት እብድ። እብድ ምን ታሪክ አለው? በቃ እብድ ናታ!!

“እሺ የት እንደምታድርስ ታውቃለህ?” አልኩት አቡሽን

“ማን?” ብሎ መልሶ ሲጠይቀኝ እየሰማኝ ባለመሆኑ ተናደድኩበት። አልፈርድበትም። የማወራውን ለራሴ እንኳን ሳደምጠው የእብደት ወሬ ነው። ገላዋ ከዝናቡ ጋር የፈጠረውን ውብ መስተጋብር ያላየ እንዴት ብሎ ቅዠቴን ሊረዳው ይችላል?
አቡሽ ጓደኛዬ ነው። የክፍለ ሃገር አውቶቢስ መነሃሪያ ውስጥ ውድ የሆነውን የተራ ማስከበር ስራ አብረን ነው የምንሰራው። መንገድ ዳር ያለች ለእግር መዘርጊያ የማትመች ኮንቴነር በርካሽ ተከራይተን አብረን ነው የምንኖረው።

—ትናንትን ለመድገም—
አንዱን ጥግ ተከልዬ እየጠበቅኳት ነው። ከእትዬ ሸዋረገድ አረቄ ቤት ያለወትሮዬ ሸካክፌ በጊዜ የወጣሁት እንዳታመልጠኝ ነው። አሁንም አሁንም አረቄዬን ፉት እያልኩ ለማላውቀው ሰዓት ያህል ከራሴ እያወራሁ ጠበቅኳት። ብትመጣ ምንድነው የምላት? ማንስ ብዬ እጠራታለሁ? ኸረ ለመሆኑ ለምንድነው እየጠበቅኳት ያለሁትስ?

እርቃኗን እየተጎተተች ትናንት የነበረችበት ቦታ ቆመች። ዝናብ የለም። እሷ ግን ራቁቷን ናት። ያለዝናቡ ውበቷ ጎዶሎ ሆነብኝ። በደመነፍስ እግሮቼ ወደሷ ሲራመዱ ይታወቀኛል። እጆቼ ሊነኳት ወደፊት ተዘረጉ። ዝም ያለ ስሜት አልባ ፊት ነው ያላት። ጠይም ቆዳዋ እያየሁት ጠቆረብኝ። ጥቋቁር ጥቅጥቅ ያሉ ፀጉሮች አበቀለ። ሰውነቷ እንደመለጠጥ አለ። አፍጥጬ አየኋት። ‘እሷ’መሆኗ ቀርቶ ጥቁር ላም ሆነችብኝ። ላም!! ግን ደግሞ በአራት እግሮቿ ምትክ አራት የመኪና ጎማ ያላት ላም! ሁለቱ ዓይኖቿ የመኪና መብራት መሰሉ። ወደኋላዬ ሸሸኋት። እንደመኪና እያጓራች ‘ላሚቷ’ ጎማዋን እያሽከረከረች ስትርቅ የ‘እሷ’ ድምፅ የሰመመን ያህል ይሰማኛል።

“ልጆቼን በሏቸው። ቀርጥፈው!! በሚጥሚጣ አጥቅሰው ነፏቸው።”

ግድግዳውን እንደተደገፍኩ፣ በእጄ በውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ያለ አረቄዬን እንዳነቅኩ ነቃሁ። ሊነጋ እያቅላላ ነበር።ፊቴ ቆማለች።

“ልጆቼን በሏቸው። ቀርጥፈው። በሚጥሚጣ አጥቅሰው ነፏቸው።” አለችኝ ኮስተር ብላ።

ያወቀችኝም የሚመስል ፣ ያወቀችብኝም የሚመስል፣ አውቃ ከእንቅልፌ የቀሰቀሰችኝም የሚመስል ዓይነት ብልጭታ ፈገግታ ፈገግ ብላ ጥላኝ ሄደች። ሰው እንዳላየኝ አረጋግጬ ልብሴን እያራገፍኩ ወደቤቴ አቀናሁ። እየራቀች ስትሄድ ድምፅዋ ይሰማኛል።

“ልጆቼን በሏቸው…………… ”

—ልጆቿ—
ከሀገሬ የመጣሁ ሰሞን አውቶቢስ ተራው አካባቢ ውር ውር ስል ግርግር አይቼ ተጠጋሁ። የተሰበሰበውን ሰው አቋርጬ ወደ መሃል ስጠጋ የቀናት አራስ ህፃን ልጅ በእራፊ ጨርቅ ተጠቅልሎ ይዛ አንዲት አዳፋ የለበሰች ሴት ‘ኡ ኡ ኡ…’ ትላለች። የሚያውቋትና ድርጊቱ የለመዱት ዓይነት ከሚመስሉ ሰዎች ጉርምርምታ ሴቲቱ እብድ መሆኗን እናየወለደችውን ልጅ በሁለተኛ ቀኑ ዳቦ አጉርሳ አፍና እንደገደለችው ሰማሁ። ‘እሷ’ ናት!!

‘እሷን’ እዛ አካባቢ ማየት የአውቶቢስ መነሃሪያ ጊቢውን እንደምልክት እየቆጠርኩ ከመንቀሳቀስ እኩል የለመድኩት ነገር ሆነ። ትጮሃለች፣ በድንጋይ ያገኘችውን ሰው ታባርራለች፣ የትም ያገኘችውን ትበላለች …………

ከተሜነቴን ተላምጄ ‘የት ሰፈር ነህ?‘ ሲሉኝ ‘አውቶቢስ ተራ!‘ ማለት የጀመርኩ ሰሞን እብደቷ በረደላትና ‘አደብ ገዛች።’ ‘አርግዛ ነው በቃ!‘ እያሉ ሲያወሩ ሰማሁ።

ከክረምቱ ጠዋቶቼ በአንደኛው ጉርሴን ላበሳስል በወጣሁበት የውሃ መውረጃ ቱቦ አካባቢ ሰዎች ሰብሰብ ብለው አየሁ። ጠጋ ብዬ የሰዎቹ መሰባሰብ ስለምን እንደሆነ አጣራሁ። በቱቦው በሚወርደው ውሃ ውስጥ ህፃኗን አቅፋ ታለቅሳለች። ‘ከወለደችው ድፍን አንድ ቀን አልሞላም።’ ሲሉ ሰማሁ። ቱቦው ውስጥ ህፃኑን ደብቃው ሄዳ ስትመለስ ውሃው አፍኖ ነው የገደለው። ‘ለራሱ ምግብ ላመጣለት ነው የሄድኩት።‘ ትላለች ከእንባዋ ጋር እየታገለች። ጡት እንጂ ምግብ እንደማያስፈልገው የማታውቅ እብድ መሞቱን እንዴት አወቀች? እብድ አይደለች? ስል ተገረምኩ። ‘እሷ’ ናት!!

“እንዴት ማሰብ የማይችል ቢሆን ነው? ሰው እንዴት በጤነኛ ጭንቅላቱ ከዝህች እብድ ጋር ይተኛል? አብሯት የተኛው፣ ያረገዘችለት ሰው እሱም እብድ መሆን አለበት።” ብዬ ራሴን በአመዛዛኝ ሂሳብ መዳኘቴ ያለፈ ስህተቴ ነው። የአሁን እርማቴ ደግሞ “እብድ ሊሆን አይችልም። ያበደ ሰው የገላዋ የውበት ቀመር ሊገባው አይችልም። እንደኔ እርቃኗን ከዝናብ ስትጫወት አይቶ የፈዘዘ መሆን አለበት።”

—ከትናንት በስቲያን ለመድገም—
እየጠበቅኳት ነው። እርቃኗን ሆና ለማየት ዝናቡን እንዲያወርድ የሀገሬን ታቦት እለማመናለሁ። የምትደራርባቸው ድሪቶዎቿ አስቀያሚና ቆሻሻ ስለሚያደርጓት ቀን ቀን ለብሳ ሳያት እናደድ ጀምሪያለሁ። እየጠበቅኳት ነው። ……… እንደትናንቱ እንቅልፍ ወሰደኝ። እንደትናንቱ ሁሉ ያ ቅዠቴ መጣብኝ። አራት ጎማ ያላት ጥቁር ላም ሆና መጣችብኝ። እንደትናንቱ ሊነጋ ሲል በጩኸት ቀሰቀሰችኝ።

“ልጆቼን በሏቸው። ቀርጥፈው!! በሚጥሚጣ አጥቅሰው ነፏቸው።”

—ያን ቀን ለመድገም—
በየእለቱ ለሊት እጠብቃታለሁ። በየእለቱ እንቅልፍ ይጥለኛል። በየእለቱ ያ ቅዠቴ ይመጣብኛል። በየእለቱ ሊነጋ ሲል በጩኸቷ ትቀሰቅሰኛለች። ያን ማድረጓን ታውቀው ይመስል ፈገግ ብላ አይታኝ እያንባረቀች ትሄዳለች።………… አስር ቀን ሆነ። እያበድኩ መሰለኝ። ላያት እየጓጓሁ በጠበቅኳት ቁጥር ጭራሽ ያየሁት ውበትም ምስሉ እየደበዘዘ በላሟ እየተተካብኝ መጣ። ተውኩት። መጠበቄን ተውኩት። ባልረሳውም ምስሏን ልረሳው ሞከርኩ። እቤት ከጓደኛዬ ጋር አደርኩ። ቅዠቴ መጣብኝ። ጥቁሯን ላም ሆነች። ግን እንደሌላው ቀን እያጓራች አልሄደችም።

ላሚቷ የደከመች መሰለች። ጎማዎቿ መሄድ ያቃታቸው። ‘ላሚቷ አደብ ገዛች!’ አደብ ለመግዛቷ ምክንያት እኔ እንአሆንኩ እየተሰማኝ እፀፀታለሁ። ……… እንዳለፉት አስር ቀናት በሷ ጩኸት ሳይሆን ከአቡሽ ጋር በምናድርባት ኮንቴነር መንኳኳት ነቃሁ። እየተደናበርኩ በቀዳዳ አጮለቅኩ።
“ማነው እሱ?” አለ አቡሽ

“ማንም አይታይም። ገና ለሊት ነው።” አልኩት ማጮለቄን ሳላቆም። በመንገዱ መብራት መንገዱ ግልፅ ብሎ ይታያል። ዝናብ እየዘነበ ነው። ……… አየኋት!!

“ሽንቴን ልሽና!” ብዬ ከፍቼ ወጣሁ።

መውጣቴን ስታይ ፈገግ ብላ መሄድ ጀመረች። የምኖርበትን ታውቃለች? ማደሪያዬን ያንኳኳችው እሷ ናት? እየጠበቅኳት እንደነበር ታውቅ ነበር ማለት ነው? ዛሬ ከቦታዬ ስታጣኝ ነው የመጣችው? ኸረ ለመሆኑ ይህቺ ሴት እብድ ናት ጤነኛ? ራሴስ ጤነኛ ነኝ? ራሴን እየጠየቅኩ ዝናቡ እየመታኝ ትንሽ ወደሷ ራመድ እንዳልኩ ቆምኩ። ተራ በተራ የለበሰቻቸውን ድሪቶዎች እያወለቀች መጓዟን ቀጠለች። እየተከተልኳት እንደሆነ ለማወቅ መሰለኝ ዘወር እያለች ታየኛለች። የማደርገው ሳይገባኝ ተከተልኳት። ከሰው አይን ሰወር ያለ ቦታ ስትደርስ ፍፁም እርቃኗን ሆነች። ……

ይሄ ከሆነ ከወራት በኋላ ‘እሷም’ በቅዠቴ እንዳባተተችኝ ጥቁር ላም ‘አደብ ገዛች!!’ ……

2 Comments

  • helinaberhane26@gmail.com'
    Helina berhane commented on December 6, 2017 Reply

    Magnificent

  • solomon215mekonnen@gmail.com'
    ሰለሞን መኮንን commented on July 22, 2018 Reply

    wow!!!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...