Tidarfelagi.com

“ወልቃይት የማን ነው?” የማይረባ ጥያቄ

አንድ

በነገረ አስተሳሰብ ወይም በአስተሳሰብ ሕግ (ሎጂክ) ትምህርት ላይ አንድ የማስታውሰው ምሳሌ አለ፤ ‹‹ሚስትህን መደብደብ ትተሃል ወይ?›› የሚል ጥያቄ ነው፤ ጥያቄው የሚነሣው ጠያቂው አውቃለሁ ብሎ ከያዘው እውቀት ወይም እምነት ነው፤ ስለዚህም ጠያቂው የሚፈልገው ጥያቄ ለማስተላለፍና መልስ ለማግኘት አይደለም፤ ጠያቂው የሚፈልገው በጥያቄ መልክ የራሱን ‹‹እውቀት›› ወይም እምነት ለተጠያቂው ለማስተላለፍና ተጠያቂውን የጠያቂው ደቀ መዝሙር ለማድረግ ነው።

ሚስትህን መደብደብ ትተሃል ወይ? መልስ የሌለው ጥያቄ ነው፤ ‹‹አዎ›› የሚል መልስ ሰውዬው ሚስቱን ሲደበድብ እንደነበረ አመነ ማለት ነው፤ ‹‹አልተውሁም›› ከአለ በራሱ ላይ መሰከረ፤ ሁለቱም መልሶች ተጠያቂውን የሚያስወነጅሉ ስለሆኑ መልስ አይደሉም፤ ከዚያም በላይ ጥያቄው ትክክል አይደለም፤ የማይረባ መጥፎ ጥያቄ ነው።

‹‹ወልቃይት የማን ነው?›› የሚለው ጥያቄ ትክክል አይደለም፤ የማይረባና መጥፎ ጥያቄ ነው፤ ጠያቂው የሚፈልገው መልስ የአማራ ነው፤ የጎንደር ነው፤ የትግሬ አይደለም፤ የሚል ነው፤ ነገር የሚገባው ተጠያቂ ጥያቄውን ጠያቂው በፈልገው መልክ አይመልስለትም፤ ሊመልስለትም አይገባም፤ ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው የሚል መልስ አይፈለግም፤ የማይፈለግበትም ምክንያት ‹‹ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው፤›› ማለት ወልቃይትን ከጎሠኛነት አጥር ስለሚያወጣ ነው፤ የትግራይ አይደለም፤ የአማራ አይደለም፤ የኢትዮጵያ ነው፤ አሁን ትግራይና አማራ የኢትዮጵያ ናቸው፤ ይህ ከተባለ በኋላ ወልቃይት የትግራይ ነው? ወይስ የአማራ? የሚለውን ጥያቄ ማንሣት የጎሠኛነት ጥያቄ ነው፤ የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ አይደለም፤ ጥያቄው የማይረባ የሚሆንበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፤ ሁለተኛው ምክንያት የጎሠኛ ጥያቄ በመሆኑ የወያኔን የጎሠኛ መመሪያ የሚያከብር መሆኑ ነው።

ትልቁና መሠረታዊው ጥያቄ በአማራ ክልል ስር የነበረው ወልቃይት በወያኔ አገዛዝ ወደትግራይ ክልል መግባቱ ነው፤ እዚህ ላይ ጥያቄው የወልቃይት ወረዳ ወይም አውራጃ ነው፤ በውስጡ የሚኖሩት ሰዎች የጎሣ ዓይነት ወይም የጎሣ ስብጥር አይደለም፤ የፈለገውን ዓይነት አንድ ጎሣ ወይም የብዙ የጎሣ ስብጥር ሊኖርበት ይችላል፤ ክርክሩ መሆን ያለበት የወልቃይት አውራጃ ከጎንደር ክልል ወጥቶ ወደትግራይ የገባበት መንገድ ትክክል አይደለም፤ የአስተዳደር ለውጡ የተፈጸመው የፌዴራል መዋቅሩን ሥርዓት በጣሰ መንገድ አንዱ ክልል (ትግራይ) በሌላው ክልል ላይ የጉልበተኛነት ወረራ አካሂዷል ነው፤ ይህ ወረራ ሕጋዊ አይደለም፤ ይህ ወረራ ሊቀለበስ ይገባል፤ ዋናው መቋጠሪያ ይኸው ነው።

ግን ጉዳዩን የጀመርነው ከመሀሉ ነው፤ ሲጀመር ወያኔ ከኦሮሞ ቡድኖች ውስጥ ኦነግን መረጠና አማርኛ ተናጋሪውን አለ እያለ እንደሌለ ቆጠረው፤ በዚያን ጊዜ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎቹም ኢፈትሐዊነቱን አልተናገሩም፤ ዋና የፖሊቲካ ጉዳይ አድርገው አላነሱትም፤ ለምን? እነሱ በሎሌነት በመመረጣቸው በደስታ ተውጠው ስለነበረ ጌቶቻቸውን ለማስቀየም ፍላጎት አልነበራቸውም፤ ግን ወያኔ በእጁ ያሉትን ምርኮኞች ከአደራጀ በኋላ ኦነግ ተባረረና በኦሕዴድ ተተካ፤ የኦነግ መሪዎች አገር ውስጥ ሆነው ለመታገል የሚያስከፍለውን ዋጋ ላለመክፈል በአሜሪካና በአውሮፓ ተቀምጠው በስልክ ‹‹ትግሉን›› መምራት መረጡ፤ ወያኔ አነግን በብዙ መንገድ ተጠቅሞበታል፤ አንደኛና ዋናው አማርኛ ተናጋሪውንና ኦሮምኝ ተናጋሪውን ለመለያየትና በቅራኔ ለማጋጠም፤ ሁለተኛ የኦሮሞ መሪዎች ነን የሚሉ ሁሉ ለወያኔ ትሑት አገልጋይ ከመሆን ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው አረጋገጠላቸው፤ ኦነግንና እስላማዊ ኦነግን አፋጅቶ በኦሕዴድ አጋዥነት ሁለቱንም ከትግል መድረኩ አስወጣቸው።

አለ ተብሎ እንደሌለ የተቆጠረው አማርኛ ተናጋሪው በነታምራት ላይኔ፣ በነበረከት ስምዖን፣ በነህላዌ ዮሴፍ፣ በነተፈራ ዋልዋ፣ በነ (ሁሉም ያለጥርጥር አማርኛ ተናጋሪዎች ናቸው፤ ነገር ግን ከየት ከየት እንደበቀሉ አጠራጣሪ ነው፤) ተወከለ፤ ከጎንደርም ይሁን ከጎጃም፣ ከወሎም ይሁን ከሸዋ የእነዚህን ሰዎች ውክልና የተቃወመ የለም፤ እንዲያውም ለአሽከርነቱ ውድድር ነበር፤ በሁለቱ ድርጅቶች — በብአዴንና በኦሕዴድ — አማካይነት ወያኔ ወደሰባ በመቶ የሚጠጋውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጥጥሩ ስር አደረገ፤ ይሄ ሁሉ ሲሆን በአገር ውስጥ ያሉት የአማርኛ ተናጋሪውና የኦሮምኛ ተናጋሪው ወኪሎች ነን ባዮቹ ለፍርፋሪ ሲፎካከሩና ሲነታረኩ ወያኔ የራሱን ክልል በትምህርትና በልማት ለማሳደግ እየሞከረ ነበር።

ለእኔ ፍሬ ነገሩ አማርኛ ተናጋሪውም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪው ሃያ አምስት ዓመታት ሙሉ እየተፎካከሩ ወያኔን ከማገልገል ሌላ መብትና ሥልጣን ፈልገው አያውቁም፤ ስለዚህም ከማይናገር ከብቱን፣ ከማይራገጥ ወተቱን እንደተባለው ወያኔም በከብቱም በወተቱም ተጠቀመበት።

ሁለት

በ1996 ዓ.ም. የክህደት ቁልቁለት በሚል ርእስ ትንሽ መጽሐፍ አሳትሜ ነበር፤ በዚያ መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 96ና 97 መሀከል ካርታዎች አሉ፤ ከነዚህ ካርታዎች አንዱ የኢጣልያ ምሥራቅ አፍሪካ (AFRICA ORIENTALE ITALIANA) 1928-1933 ዓ.ም. የሚል ነው፤ በዚያ ካርታ ላይ ፋሺስት ኢጣልያ ትግራይን በሙሉና አፋርን በሙሉ በኤርትራ ክልል ውስጥ አድርጎት ነበር፤ በደቡብም የኢጣልያን ሶማልያ ወደሰሜን ገፍቶ ኦጋዴንን በሙሉና ግማሽ ባሌን ጨምሮበት ነበር፤ ምዕራቡን ክፍል — ወለጋን፣ ኢሉባቦርን፣ ጋሞ ጎፋን፣ ሲዳሞን በአንድ ላይ አስሮ ጋላና ሲዳማ የሚል ስያሜ ሰጥቶት ነበር፤ ሀረር ሰሜን ባሌንና አርሲን ጠቅልሎ ነበር፤ ወያኔም ከፋሺስት ኢጣልያ የወረሰውን አስተሳሰብ ይዞ የጎሣ ክልሎችን ፈጠረ፤ በዚያን ጊዜ ግማሹ እልል እያለ ግማሹ እያጉረመረመ ተቀበለ፤ በዚህም ሥርዓት አንድ ትውልድ በቀለና በጫትና በጋያ አደገ።

ወያኔ የበቀለበትን ትግራይን ሲያይ አነሰችው፤ በዚያ ላይ በሰሜን በቂልነት ደም ከተቃባቸው ከኤርትራውያን ጋር በደቡብ ደግሞ የሥልጣን ችጋሩ ጠላት በአደረጋቸው ኢጣልያ ‹‹አማራ›› ብሎ በከለላቸው ሰዎች በጎንደርና በወሎ በኩል ታፍኗል፤ በዚያ ላይ በትግራይ ውስጥ ካለው የእርሻ መሬት የተሻለ በጎንደርና በወሎ አለ፤ ጉልበተኛ ሆኖ መቸገር አይበጅምና በጊዜ፣ በጠዋቱ ከጎንደርም ቀንጨብ፣ ከወሎም ቀንጨብ አደረገና አበጠ፤ ሲያብጡ ቦታ ይጠብባል፤ ስለዚህ ወደቤኒ ሻንጉልና ወደጋምቤላ በመዝለቅ ሁለት ዓላማዎችን ማሳካት ይቻላል፤ አንደኛ ትግራይ ሰፊ ይሆንና በእርሻ ልማት የሚከብርበት ተጨማሪ መሬት ያገኛል፤ ሁለተኛ ጠላት ብሎ የፈረጀውን አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ የውጭ ንክኪ እንዳይኖረው ያፍነዋል፤ ከሱዳንም ጋር ጊዜያዊ ወዳጅነትን በመሬት ይገዛል፤ የወያኔ የእውቀትና የብስለት እጥረት ከብዙ ትንሽም ትልቅም ኃይሎች ጋር ያላትማቸዋል፤ ሱዳንን በመሬት በማታለል ሱዳንን ከደቡብ ሱዳን፣ ከኤርትራ፣ ከግብጽ፣ ከሳኡዲ አረብያ፣ ከየመን፣ ከሶማልያ … መለየት የሚችሉ ይመስላቸዋል (ልክ አማርኛ ተናጋሪውንና ኦሮምኛ ተናጋሪውን እንደለዩት)፤ የተዘረዘሩት አገሮች ሁሉ በሱዳን ላይ ከወያኔ የበለጠ ጫና ማድረግ የሚችሉ ናቸው፤ አሜሪካን ለብቻው ብቻ ሳይሆን ከነዚህ አገሮች ጋር አብረን ስንገምተው የወያኔን ደካማ ሁኔታ ለመገንዘብ ቀላል ነው፤ በአካባቢያችን ከአሉት አገሮች ሁሉ ወረተኛ የውጭ አመራር ያለው ሱዳን ነው፤ ሱዳን የኤርትራን መገንጠል የደገፈው በአሜሪካ ጫና መሆኑን አንርሳ፤ ለማንኛውም አሁን በወልቃይት የተጀመረው ውጊያ ከቀጠለ የወያኔና የሱዳን የጓዳ ጨዋታ ያበቃለታል።
ጉዳዩ ሰፊ ጥናት የሚያስፈልገው ነው።

ሦስት

ወደየጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ስንመለስ፡– ጥያቄው በቁሙ የወልቃይት-ጸገዴ ተወላጆች እንዳቀረቡት ሲታይ የወያኔ አገዛዝ ሃያ አምስት ዓመታት የደከመበት የጎሠኛ ሥርዓት ቢያንስ በአስተሳብ ደረጃ የተሳካ መሆኑን ያረጋግጣል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎሠኛ አስተሳሰብ ገና እንዳልወጣ የሚያረጋግጥ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ በጎሣ ሥርዓት እየገዛ በጎሣ ሥርዓት የሚሸነፍ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው፤ ወያኔ ይህንን አዲስ ክስተት ገና አልተገነዘበውም።

ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ከመለስ ዜናዊ ጋር ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ተገናኝተን ስንከራከር አማራ የሚባል ጎሣ አሁን የለም፤ ግን አንተ ትፈጥረዋለህ ብዬው ነበር፤ ገና በሕጻንነት ነው እንጂ አሁን ተፈጥሮአል!
በደቡብ አፍሪካ ኔልሰን ማንዴላ በእስር ላይ በሚንገላታበት ጊዜ ደ ክለርክ የሚባለው የደቡብ አፍሪካ መሪ ማንዴላን ከእስር አስወጥቶ እንደአኩያው በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግረው የሁለቱ ተቃራኒ መሪዎች መተማመን የደቡብ አፍሪካን ችግር ለጊዜው ፈታው፤ ማንዴላ በክብር ሞተ፤ ደ ክለርክ በክብር ይኖራል፤ የሚያሳዝነው በወያኔ አመራር ውስጥ እንደደቡብ አፍሪካዊው ደ ክለርክ ያለ ሰው እንኳን ሊኖር ሊታለምም አይቻልም፤ እንኳን በወያኔ ውስጥ በአገሩም እንዲህ ዓይነት ሰው እንዳይኖር አረጋግጠዋል።
የተጀመረውን ግብግብ ኢትዮጵያ ካላሸነፈች ማንም አያሸንፍም!
ኢትዮጵያ የድንክዬዎች አገር ሆናለችና የገጠማትን ችግር እግዚአብሔር በጥበቡ ይፍታላት!

Ethiopian academician and peace activist who has been actively engaged in a peaceful movement to bring justice, equality and peace for all the people in Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...