ከዚህ በፊት ስለወለጋ የሚያትት አነስተኛ ጽሑፍ በዚህ ግድግዳ ላይ ለጥፌ ነበር። ይሁንና ያቺ ጽሑፍ ለወለጋ ክብር የምትመጥን አልመሰለኝም። ብዙ ድርሳናትን ለሚያስጽፈው ምድር ትንሹን ብቻ እንደ መወርወር ነው። በመሆኑም በዛሬው የኢትኖግራፊ ጉዞአችን ወለጋን ደግመን ልንዘይረው ተዘጋጅተናል። ጉዞ ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ! ዳይ!
——-
የወለጋ ምድር የእናት ጓዳ ነው። ከዚያ ምድር የሚፈልቁት የኦሮሞ ባህላዊ ምግቦች ስፍር ቁጥር የላቸውም። ጩምቦ፣ አንጮቴ፣ ጨጨብሳ፣ ጩኮ፣ “መርቃ” (ገንፎ) ሁላቸውም ጣት ያስቆረጥማሉ። የወለጋ ሴትን ያገባ እንዴት የታደለ መሰላችሁ? እጅግ ሲበዛ ሙያተኞች ናቸው። ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሄር በሰለሞን ዴሬሳ ተጋብዞ ነቀምቴ በሄደ ጊዜ ባየው የወለጋ ባህላዊ ቡፌ ተመስጦ ፍዝዝ ብሎ ነው የቀረው። ጋሼ አሰፋ ጫቦም ከደርጉ ዋነኛ ሰው ከኮሎኔል ደበላ ዲንሳ ጋር ወለጋ ሄዶ ያጋጠመውን ግብዣ ሲጽፍልን “ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል” ነው ያለው። እኔም በልጅነቴ “ጩምቦ ጉልበተኛው ምግብ” የሚል ጽሑፍ ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ባነበብኩ ጊዜ በጣም ነበር የተገረምኩት። ጸሓፊው “በአንዲት አነስተኛ ሳህን የቀረበልንን ምግብ ለሰባት ሆነን መጨረስ አቅቶን ነበር” ያለ ይመስለኛል። እዚህ ላይ “መሮሌ” ከተሰኘው የዘሪሁን ወዳጆ ዘፈን የተወሰኑ ስንኞችን መጥቀስ ያለብኝ ይመስለኛል። ዘሪሁን እንዲህ ነበር ያለው።
አስ ኮቱ አርጆ ደቅኔ ቡና ቀላ ቀለንና (ወደዚህ ነይ አርጆ ሄደን “ቡና ቀላን” እንቀምሳለን
አስ ኮቱ ቄለም ዴምኔ መርቃ ገርቡ ኩተንና. (ወደዚህ ነህ “ቄለም ደርሰን የገብስ ገንፎ እንጎርሳለን)
ቡና ቀላ ከቅቤ ጋር የሚቀቀል ቡና ነው። አንዳንዴ ደግሞ ቡናው በቅቤ ውስጥ ተነክሮ በምጣድ ላይ ይጠበሳል። በኦሮሞ ባህል መሰረት “ቡና ቀላ” የሚጋበዘው የክብር እንግዳ ነው። የወለጋ ሴቶች “ቡና ቀላ”ን ባማረ መዓዛ በማዘጋጀት ይታወቃሉ።
ታዲያ የወለጋ ሴቶች በሙያቸው ብቻ አይደለም የሚታወቁት። በውበታቸውም ዘወትር ተጠቃሽ ናቸው። “ውቢት ኢትዮጵያ”ን የሚረሳ አለ? … አዎን! ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን “የ13 ወር ፀጋ” በሚል ርዕስ ከሚያሳትማቸው ዝነኛ ፖስት ካርዶች ላይ የማትጠፋው “ውቢት ኢትዮጵያ” የተሰኘችው ወጣት የወለጋ ልጅ ናት (የተፀውኦ ስሟ አልማዝ አመንሲሳ እንደሆነ ተነግሮኛል)። በልጅነቴ የማውቃት አንዲት ውብ ሴት ደግሞ በገለምሶ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታስተምር ነበር። ያቺ ወጣት በዚያ ዘመን በኛ ሀይስኩል ከነበሩት ሁለት ሴት መምህራን አንዷ ነበረች። የወጣቷ ስም “ደሜ” መሆኑን አስታውሳለሁ። “ደሜ” እጅግ የተዋበች ሴት ነበረች። ብዙዎች የጣሊያን ክልስ ናት ብለው ቢገምቱም እርሷ ግን ሙሉ ኦሮሞ ነበረች (ደሜ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ነዋሪ መሆኗ ተነግሮኛል)።
የወለጋ ምድር የጀግኖች አምባም ነው። በርካታ ስመ-ጥር አርበኞች ወጥተውበታል። በዚህ ረገድ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የሁላችንም ኩራት የሆነው ጀግናው አብዲሳ አጋ ነው። የአብዲሳ አርበኝነት ለየት የሚለው እስከዛሬ ድረስ የሚታወስበትን ጀብዱ የፈጸመው በአውሮጳ ምድር በመሆኑ ነው። አንድ ጸሐፊ እንዳለው በአውሮጳ መሬት ላይ ጦር እየመሩ ጀግንነትን ማሳየት የቻሉ አፍሪቃዊያን ከጥንቷ ካርታጎ (የአሁኗ ቱኒዚያ) የተገኘው አኒባል እና የኛው አብዲሳ አጋ ብቻ ናቸው።
ወለጋ የምርጥ ምሁራን መፍለቂያም ነው። በጥንት ጊዜ በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ተከታታይ ምሁራዊ ጽሑፎችን ያበረከቱት ብላታ ዴሬሳ አመንቴ የወለጋ ሰው ናቸው። የርሳቸው ልጅ የሆኑት ልጅ ይልማ ዴሬሳ ደግሞ የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ምሩቅ ናቸው። እኝህ ምሁር በኢትዮጵያ የፋይናንስ አሰራር ላይ ከፍተኛ አሻራ ጥለው ማለፋቸውም ይታወቃል። በሌላ በኩል የወለጋ ምድር እንደ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ፣ ፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ፣ ፕሮፌሰር ህዝቅኤል ገቢሳ፣ ፕሮፌሰር ተሰማ ታኣ፣ ዶ/ር ገመቹ መገርሳ፣ ዶ/ር ሽጉጥ ገለታ፣ አቶ አማኑኤል አብረሃም፣ አምባሳደር ብርሃኑ ዲንቃ፣ ገጣሚ ሰለሞን ዴሬሳ የመሳሰሉ ምሁራንን ወጥተውበታል። እንዲሁም በደርግ ዘመን በካቢኔው ውስጥ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ሃምቢሳ ዋቅወያ እና አቶ ዮሴፍ ሙለታ የወለጋ ሰዎች ነበሩ።
በፖለቲካው ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸውን ፋኖዎችን በማብቀልም ወለጋ አንደኛ ነው። የደርግ ዘመን ከፍተኛ ባለስልጣን ከነበሩት ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ እና ሻለቃ ደምሴ ዴሬሳ ጀምሮ እነ ሃይሌ ፊዳ፣ ባሮ ቱምሳ፣ ሌንጮ ለታ፣ ገላሳ ዲልቦ፣ ነጋሶ ጊዳዳና ቡልቻ ደመቅሳን የመሳሰሉ ፖለቲከኞች ከወለጋ ነው የተገኙት። ዛሬም በፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉ በርካታ የወለጋ ቡቃያዎች አሉ። የአሁኑ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም የወለጋ ተወላጅ ናቸው።
ወለጋ የጥበብ ምድር መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ከደምቢ ዶሎ ከተማ ብቻ የፈለቁትን የጥበብ ዋርካዎች ብቆጥርላችሁ ትገረማላችሁ። ሰለሞን ደነቀን ታውቁት የለም?… አዎን! ውብ በሆኑ የኦሮምኛ እና የአማርኛ ዜማዎቹ የምናውቀው ያ ወጣት የደምቢ ዶሎ ቡቃያ ነበር። ብዙዎቻችን ሰለሞንን የምናስታውሰው በ1980 በለቀቀው የመጀመሪያ አልበሙ ነው። በዚያ አልበም የተካተተው የኦሮምኛ ዜማ የሚከተለው አዝማች ነበረው።
ያ ደበሌ ዝማሙ ያ ደበሌ ዝማሙ ( አንቺ ደበሌ ዝማሙ ሆይ)
አመልሊ ኬ ጉዳዳ ገንደ መሌ ሲንዳቡ (አመልሽ ብዙ ነው ሰፈር እንጂ አያስቆምሽም)
አን ደበሌ ሲንዋሙ. (እኔስ ከእንግዲህ ደግሜ አልጠራሽም)
በዘፈኑ ውስጥ የተጠቀሰችው “ደበሌ ዝማሙ” ማን እንደሆነች ለማወቅ አልቻልኩም (የሰው ስም መሆኑን የተረዳሁት ከሰለሞን አዘፋፈን ነው)። ሰለሞን እንዲህ ብሎ የዘፈነላት ከቤቷ የማትቀመጥ ሴት ናት። ሴትዮዋ ከሰፈር ሰፈር የምትንዘላዘለው ለብልግና አይደለም። ወሬኛ ሴት በመሆኗ ለወሬ ለቀማ ስትል ነው የምትዟዟረው። በመሆኑም amalli kee guddaadhaa ganda malee sindhaabu ማለትም “አመልሽ ትልቅ ነው ከሰፈር እንጂ አያስቆምሽም” ብሎአታል።
ተሾመ አሰግድ፣ ሀይሉ ዲሳሳ እና ኤቢሳ አዱኛም የደምቢ ዶሎ ተወላጆች ናቸው። በሌላ በኩል የወለጋ ምድር እንደ አብተው ከበደ፤ እልፍነሽ ቀኖ፣ዳግም መኮንን፣ ዳዊት መኮንን፣ ዳንኤል ታደሰ ወዘተ… የመሳሰሉ የጥበብ ባለሙያዎችን አብቅሏል።
ከማንም በላይ የወለጋን ምድር እንዳፈቅር ካደረጉኝ ከዋክብት መካከል አንዷ ሌንሳ ጉዲና ትባላለች። ሌንሳ የሟቹ የቄስ ጉዲና ቱምሳ ልጅ ናት። እኝህ ታዋቂ ቄስ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነየሱስ ፕሬዚዳንት ነበሩ። በ1965 ገደማ ደግሞ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል። ቄስ ጉዲና ከቅስናው ጎን ለጎን በሜጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር ውስጥም ሰፊ ተሳትፎ ነበራቸው። የደርግ መንግሥት በ1969 ከአቡነ ቴዎፍሎስ እና ከጉራጌው ሼኽ ሰይድ ቡደላ ጋር ካሰራቸው በኋላ በ1971 ማብቂያ ላይ ያለ በቂ ምክንያት ገድሎአቸዋል።
ሌንሳ ጉዲና ለቤተሰቦቿ አራተኛ ልጅ ናት። ይህች ልጅ በወጣትነቷ ለኦሮሞ ህዝብ ብሄራዊ መብት መከበር በሚደረገው ንቅናቄ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበረች። በተለይም የኦሮሞ ሴቶች በ1969 ማብቂያ ላይ በብሄራዊ ቴአትር ባዘጋጁት ታሪካዊ የባህል ዝግጅት ላይ በታዳጊነቷ ተሳትፋለች። የደርግ መንግሥት አባቷን ሲያስር ግን ሀገር ጥላ ኮብልላለች። በሀገረ አሜሪካ ለአስራ ሶስት ዓመታት ከኖረች በኋላ ደርግ ሲወድቅ ወደ ሀገሯ ተመልሳለች።
ሌንሳ በብዙዎች ዘንድ በደንብ የምትታወሰው በኪነ-ጥበብና በስነ-ጽሑፍ አፍቃሪነቷ ነው። ከልጅነቷ ጀምሮ ከአርቲስቶችና ከጸሐፊያን ጋር ጠንካራ ቀረቤታ ነበራት። ለምሳሌ ሌንሳ ጉዲና በ1984 በታተመው የዓሊ ቢራ ካሴት ውስጥ የተካተተ አንድ ምርጥ ዘፈን ደራሲ ናት። የዘፈኑ ርዕስ “በርኖታ” ነው። ትምህርት እንደማለት። እስቲ ከዘፈኑ ግጥሞች በጥቂቱ ቀንጨብ እናድርግ።
በርኖትኒ ዱጋ ኦፊራ ኤገላ
ኣዳ ሁበቺሴ ሴና ሲጢንጢላ
ሃጎጊ በሌሳ ሀሚሌ ኩፌ ካሳ
ኢጃ ጃሜ በና ሰሙ ቢሊሶምሳ
የአማርኛ ትርጉሙ እንደሚከተለው ሊሆን ይችላል።
እውነተኛ ትምህርት ከራስ ይጀምራል
ባህልን አስታውሶ ታሪክን ያስተምራል
ብዥታን አጥርቶ ሞራል ያነቃቃል
የዐይን መግለጫ ነው፣ ህሊናን ያጠራል።
——–
ሌንሳ የዘፈን ግጥሞችን ከመጻፍ በተጨማሪ ምርጥ የጽሑፍ ስራዎች ለህትመት እንዲበቁ በማድረግ የሚያስመሰግን ተግባር ከውናለች። ለምሳሌ ፕሮፌሰር ክላውድ ሳምነር Oromo Wisdom Literature በሚል ርዕስ የጻፏቸው ሶስት ምርጥ መጻሕፍት ለህትመት እንዲበቁ ያደረገችው እርሷ ናት። ሌንሳ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ነው የምትኖረው። ይህቺ ሁለገብ የስራ ሰው በሄደችበት ሁሉ በጎው እንዲያጋጥማት መልካም ምኞታችንን እንገልጽላታለን።
——
መጋቢት 11/2006
ሸገር-አዲስ አበባ