ክፈት
ጌታው ክፈት
ደብድበን, ወጋግረን, ሰብረነው ሳንዘልቅ;
ክፈት በለው በሩን- ክፈት በሩን ልቀቅ::
ሕዝቡን ዘግተውበት; ነስተውት ማለፊያ
ንገረው ለጌታህ እዚህ ያለውን ግፊያ!
በክፋት ተገፍቶ የዘጋውን ሳንቃ
ጥበቃችን ሳትመሽ ትዕግስታችን ጠልቃ
ክፈት በለው በሩን,
ክፈት
በሩን ክፈት!
ይህ ምስኪን ሕዝባችን;
ልቡን በከፈተ
በሩን በከፈተ
ስንቴ ውስጡ ይረር
ስንት’ዜ ደጅ ይደር?
ከውስጡ ተክዋርፎ
ቤቱ ተቆልፎ
ከውጭ እያደረ
ስንት ዓመት በረንዳ?
ስንት ዓመት በፍዳ?
ክፈት በለው ክፈት!
ይህ ውጭ አዳሪ ሕዝብ…
ሲታገስህ መሬት
ሲነሳበት እሬት
መሆኑን ተንትነህ,
ዘርዝረህ በትነህ,
ንገረው ለዘጊው,
አስታውሰው ለዘንጊው!
ክፈት
ጌታው ክፈት!
“የግዜር ቤት ነው” ብሎ ከፍቶ ባሳደረ;
“ቤት የኛ ነው” ብለው ያሸፉ ጀመረ::
ክፈት በለው ክፈት!
በግድግዳ ታጥረው
ሳንቃውን ቀርቅረው
ያልታዩ መስሏቸው
ለሚሞኙ ሞኞች- ሄደህ ንገራቸው,
ሕዝብ ያመረረ ቀን ወየው ለበራቸው!!