Tidarfelagi.com

ክትባት እንዴት እንዳመለጠኝ

አበሻ ገራሚ ህብረተሰብ ነው! ማስክ ገድግደህ ሲያይህ” ይሄን ያህል ትንቦቀቦቃለህ እንዴ” እያለ ያሸማቅቅሀል ፤ ከዚያ አጅሬው አስተኝቶ ለሳምንታት ያክል አበራይቶ ትቶት ይሄዳል፤ ከዚያ እንዴት ነህ? ስትለው” በዝሆን እግሩ ረግጦ አድቅቆ ለቀቀኝ በማለት ፈንታ” ይዞ ለቀቀኝ “ በማለት አቃሎ ይነግርሃል፤ ከህመሙ በረከት እንዲደርስህ ወጥሮ ያበረታታሀል፤ ስለክትባት ስታነሳበት “ ቺፕስ ሊያስገቡብን” ነው ይልሀል፤ ባለፈው አንዱ “ ፈረንጆች ቺፕስ ክንዴ ላይ ቀረቀሩብኝ “ እያለ የዝግባ ፍልጥ የመሰለ ክንዱን ለታዳሚው ሲያስጎበኝ በሆነ ዩቲውብ ቻናል ላይ አየሁት ፤ አነጣጥሬ ስሾፈው ክንዱ ላይ ያለው ኮረሪማ እሚያክል ኪንታሮት ነው፤

እኔ ያለሁበት ከተማ ውስጥ የክትባት እደላ ቢጀመርም ምዝገባውና ወረፋው አይቀመስም ፤ አንድ ቀን ግን ዝም ብየ በድንኩዋን ሰበራ ጎራ አልሁ፤
“ምን ፈልገህ ነው?” ሲሉኝ
“የማትፈልጉት ክትባት ይኖራችሁዋል? ” አልኩ ራሴን እያከክሁ’
“እድሜህ ስንት ነው?” አለቺኝ ነርሲቱ
“ኦፊሻል እድሜየ አርባ ይገመታል ፤”

“አዝናለሁ! አሁን እየከተብን ያለነው ካምሳ አመት በላይ የሆኑትን ነው“ አለችኝ።
“የሰባ አመት አዛውንት አተነፋፈስ ነው ያለኝ ፤ እንደምንም አጠጋግተሽ አስገቢኝ” ብየ ተማፀንኩዋት፤
“ኦኬ፤ ተመዝግቦ የቀረ ሰው ካለ፤ በምትኩ ትከተባለህ”
“እጅሽን ከቁርጥማት ይሰውርልኝ” በማለት መርቂያት ቁጭ አልኩ
ጥበቃው እንዳይታክተኝ አጠገቤ ከተቀመጠው ሰውየ ጋ ላውጋ ብየ ዞር አልሁ፤ በሁለት ከዘራ መሀል ጎብጦ የሚንቀጠቀጥ አዛዛዛዛውንት አይቼ
“ስንት አመትዎ ነው?’ በማለት ጠየኩት፤
“ ምን አልከኝ ? ” አለኝ፤
ከኪሴ ማይክ አውጥቼ
“ቼክ ማይክ! ዋን ፥ቱ ፥ ትሪ ! ስንት አመት ሆነዎት? “
“ባለፈው ሳምንት መቶ አመት ሞላኝ “
“እና ርስዎም ክትባቱን ይፈልጉታል?”
“አይ ለኔ አይደለም! አባቴን ላስከትብ መጥቼ ነው”
በመጨረሻ ተጠራሁ፤
ነርሲቱ ፥ ክንዴን አፈፍ አድርጋ ይዛ እንደ ጥጥ ስታባዝተው ከቆየች በሁዋላ፤
“የደም ስርህ ላገኘው አልቻልኩም” አለቺኝ ፤
“ የደምስሬ wireless ነው፤ በቀላሉ አይገኝም“ አልኩዋት
“አትቀልድ ፤ በዚህ ሁኔታ መርፌ ለመጠቀም ያስቸግረኛል”
“እንደ ልጅነት ልምሻ ክትባት ለምን አፌ ላይ ጠብ አታረጊልኝም?”
“ብዙ ጊዜ የምትመገበው ምግብ ምንድነው ?” ስትል ጠየቀችኝ፤
“ሩዝ ! ይገርምሻል ሩዝ አብዝቼ ከመውደዴ የተነሳ ወዳጆቼ ‘ ሩዝቤልት’ የሚል ቅፅል ስም አውጥተውልኛል”
“በል አሁን ወደ ቤትህ ተመልሰህ፤ ገንቢ ምግብ ብላ፤ ዳምፔል አንሳ! ፑሽ አፕ ስራ ፤ ከዚያ ከሁለት ወር በሁዋላ ተመለስ”
ይህን ስትለኝ ይሄን ልላት ብየ ተውኩት፤
“ሴት!Yo! ልትከትቢኝ ነው ወይስ ቦዲጋርድ ልትቀጥሪኝ ነው የምትፈልጊኝ? ”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • kelemteferamerenay@gmail.com'
    kelemteferamerenay@gmail.com commented on June 12, 2021 Reply

    Betam des ylal yketl amesegnalehu

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...