Tidarfelagi.com

ካ ገ ባ ች በ ኋ ላ …1 

‹‹ሌላ ወንድ አቀፋት›› የሚል መርዶ ሸሽት
ሌላ ሴት እያቀፍኩ በያንዳንዷ ምሸት
“እሷ ናት” እላለሁ!
(የኔ እብደት ሲገርመኝ ይባስ የሴቶቹ)
ፍቅር የሰለቻቸው ፍቅር የሰለቹ
እሷ ናችሁ ስላልኩ ‹‹እሷ ነን›› እያሉ
እኔ እንዳነሳቸው ራሳቸውን ጣሉ !

በሰም ገላቸው ውስጥ ወርቅ እሷን እያየሁ
ያሉትን ረስቸ ነበር አስባለሁ …
ውስጣቸው እሷ አለች የት ናቸው እነሱ
ከሌለሁ እኔ ጋር ወደቁ ተነሱ
ዓይኔ አስታወሳቸው በዓይኔ ተረሱ
በታሰረ ትውልድ ብራና ልብ ላይ በደሌን ነቀሱ!
የራሱ ፀሊም ቀን የከረፋው ሁሉ
የኔን የበደል ገድል ይደግማል በቃሉ !
ወድቀው ጣለን ሲሉ ጣላቸው ይላሉ !

እንኳንም ጣልኳቸው !!
እንኳንም ወደቁ
ከስጋ መሰላል መውደቅ አይቀሬ ነው ፍቅር ካልታጠቁ !
ከሙሉ ሰውነት ስጋ ተናጣቂ
በረከሰ እቅፍ ውስጥ በርኩሰት አጥማቂ !
ስማቸውን ረስተው የኔን ስም አዋቂ !!

እሷ ነን የሚሉት እንዴት ነው እሷነት …
ከመሬት ተነስተው ስለተቆነጁ
በለዛ ቢስ ማግጠጥ መለየት ያከሳው ዘመኔን ላይዋጁ
ባልጋው ቢናኙበት በጎዳና ታይታ
በሰዓቱ አቻነት ቀን አይሆንም ማታ !!

የኔ ቀን ነበረች የማለዳ ፀሃይ የመንቃቴ ጮራ
በህይዎቴ አድማስ ላይ ሰርክ የምታበራ
የደከመ ኩራዝ እያንጨለጨሉ
ፀሃይ ባቀናው ልብ እነአብሪ ትሎች እሷ ነን ይላሉ !
በጋን የነጠቁት በክረምት ጨረቃ አካሉ ይሞቃል?
ፀሐዩን የቀሙት በኩራዝ ይደምቃል ?

የሰርጓ ቀን ማታ …

አትሸኟትም ወይ ባይ
ከወንበር ተነስቶ
ሊሸኛት ሲጣደፍ
ወግ ነው በሚል ሰበብ
የአዞ እንባ ሲረግፍ
ከምር የምትሄድ አይመስለኝም ነበር …

እንደልጅነቴ እንደልጅነቷ
ከሰርጉ በኋላ ባሏም ወደቤቱ እሷም ወደቤቷ. . .
ይሄዳሉ እያልኩኝ . . .
የመረረው ፅዋ እንደቃቃ እስኪፈርስ
አንድ ሆነ ያሉት ልብ በጊዜ እስኪቆረስ
ስንት ዘላላም አለፍኩ ?
ከማግኘት ሲረዝም የማግኘት ተስፋ
ነገ ሊሻገሩት ያሳደሩት ኩሬ ከባህር ሲሰፋ
የዘላለም ቁጥር እንዲያ ነው ቀመሩ
መኖርን መናፈቅ ቁመው እየኖሩ !

ካ ገ ባ ች በ ኋ ላ …
ካ ገ ባ ች በ ኋ ላ …
ካ ገ ባ ች በ ኋ ላ …

One Comment

  • fkpro77eyuel@gmail.com'
    Fikadu commented on July 8, 2019 Reply

    ሸገር ብሎግ ተመችቶኛል ይመቻቹ፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...