Tidarfelagi.com

ካገባች በኋላ (ክፍል ሁለት)

የሰርግ ሰታቴው ታጥቦ ተመልሶ
የድግሱ ድንኳን በተካዩ ፈርሶ
ቅልቅል ድብልቅ …ምላሽ ቅላሽ ጣጣ
በደነዘዝኩበት አይኔ ስር ሲወጣ
ሰርጉ አለቀ ሲባል የኔ ቀን ጀመረ
ቢገፉት የማይወድቅ የመገፋት አለት ፊቴ ተገተረ !

ለኔ ግን አሁንም ….
የበረዶ ግግር የመሰለ ቬሎ
ከነቅዝቃዜው ልቤ ላይ ተስሎ
ይሰማኛል ብርዱ ጨፍጋጋ ደመና መብረቅ ነጎድጓዱ !
ይታየኛል አጀብ ሃይሎጋ እያለ ሲጎርፍ በመንገዱ
ይታየኛል ቅፍለት አቧራ እያሰነሳ
ትታያለች እሷ የሰው አይን ለብሳ!!
(((እንዴት ነው የምታምረው)))

መቸም የማረሳው እንደመርዝ ፍልጻ
የተሰካ ነገር የነፍሴ ልብ ላይ
ባልተጠራ እጣዋ ሳልጠራ ሂጀ የሰርጓን አጀብ ሳይ
ደመና ሰንጥቆ እንደሚታይ መብረቅ
አየሁት መሰለኝ አጀቡን ሰንጥቆ
አይኗ ዓይኔ ላይ ሲወድቅ
አየኋት መሰለኝ ለህዝቡ እየሳቀች ለኔ ስታለቅስ
ወደሰርጉ ድንኳን ቶሎ ላለመድረስ እርምጃ ስትቀንስ

ከንጥሻ ቅፅበት ባጠረች እይታ
አየኋት አየችኝ ከፍርግርግ ኋላ የሚያስፈታት አጥታ !
ያኔ ነው የሞትኩት የሆኔ ነገሬ አብሮ የታሰረው
ያኔ ነው የቀን ጣም ነፍሴን የመረረው !

አ ላ ም ን ም ማ ግ ባ ቷ ን !

የሙሸራው አጀብ በፊቴ ነው ያለፈው
ድፍን መንደርተኛ ከነብሴ መደብዘዝ
የሰርጓን ድምቀት ነው ሰርክ የሚለፍፈው

ምናይነት ህዝብ ነው ??

በእምነቴ አክናድ አንገቷን አቅፌ
እንደጎጆ ካስማ ፍቅሯን ተደግፌ
ፀሃይ፣ ዝናብ ሳንል ከጎኔ ተጣብቃ
በደጁ እንዳላለፍን በጇ ጨርቄን አንቃ
ያች ከማድቤቷ በጭስ አጨንቁራ
ያኛው በሱቅ መስኮት እየተንጠራራ
‹‹ያዝልቃችሁ›› ሲለን የኖረ ጎረቤት…
የኖረ ጎረቤት …
የ ኖ ረ ጎ ረ ቤ ት ….
(ቤት የሚመታ ቃል ለዚህ ስንኝ የለም)
በቃ እንዲህ ናት አለም !!

አይኗ ከአይኔ ላይ ላፍታ ሳይነሳ
ፈገግታዋ አስውቦኝ ፈገግታየን ለብሳ
ሌላ አገባች ሲባል ከበሮ ሚያነሳ !
ም ን አ ይ ነ ት ህዝብ ነው?

አንድ ሰፈር ሆዳም ምድረ ፍርደ ገምድል
በሰርግ ጭብጨባ ፍቅር የሚገድል !
ከዛ ሁሉ አጃቢ ከዳስ ሙሉ እልል ባይ
አንድ ሰው ይጠፋል ትላንትን ዙሮ ሚያይ ??
የት ደረሰ ያ ልጅ ከሙሽራው በፊት ከጎኗ የኖረው
የት ሄደ ያ ድልድይ እሷን ያሻገረው
የሚል ነጠላ ነብስ ?
ምናይነት ህዝብ ነው ?

ክደት መሸፈን ነው የሰርገኛ ግብሩ?
ማደናቆሪያ ነው እልልታ መዝሙሩ?

ማን ያውቃል …
ሙሽራ እያጀበ ሰርግ ቤት የዋለ
ከሚያገበሰብሰው የድግስ ቡፌ ላይ
የተካደ አፍቃሪ የጎን አጥንት አለ !
ባንዱ ደምና አጥንት አንዱ ሲደላደል
ትላንትን በመካድ ነገን ደፍሮ መግደል
ለዚህ ማጨብጨብ ነው ስርየት የለሽ በደል …
ጠላቴ ነው ህዝቡ !!

ካገባች በኋላ …..
ካገባች በኋላ…
ካገባች በኋላ…

One Comment

  • value commented on July 16, 2019 Reply

    ያምራል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...