ባለፈው ከውጭ ወዳገር ቤት ስመጣ አንዱ ደውሎ:-
” ጀለስካ ወዳገር ቤት ለመግባት ኤርፖርት ታይተሃል የሚባል ነገር ሰማሁ ልበል”
” ልክ ነው!”
“በሩ ላይ ጠብቀኝ ታክሲ ይዤ መጣሁ”
“እቃ ውሰድልኝ ልትለኝ ባልሆነ?”
“ምናለበት ብትቸገርልኝ”
” አዝናለሁ ሻንጣየ ውስጥ ላየር ማስገብያ የሚሆን ቦታ እንኩዋ የለም”
“እኔማ ለወንድሜ መዳኒት ትወስድልኛለህ ብየ አስቤ ነበር። እምቢ ካልክ ምን አደርጋለሁ?! ምስኪን ወንድሜን እግዜር እንዳደረገ ያድርገው! ” አለ አንጄት በሚበላ ድምፅ።
ትንሽ ከራሴ ጋር ታገልኩ። በሀሳቤ ወንድምየው ዘውዲቱ ሆስፒታል በደማቅ ሰማያዊ ያጥሚት ፌርሙስ ተከብቦ ተኝቶ :በመስኮት አሻግሮ የመዳኒቱን መምጣት በጉጉት ሲጠባበቅ ታየኝ።
“መዳኒት ከሆነማ መቼስ it is ok ” አልኩ።
ከጥቂት ደቂቃ በሁዋላ አጅሬ የላስቲክ በርሚል የምያህል ፌስታል አንጠልጥሎ ከተፍ አለ። ከፌስታሉ ውስጥ ሁለት እጁን ከተተና የሆነ ነገር መጎተት ጀመረ። ከጉድጓድ ውሃ እሚያወጣ ይመስል ተንጠራርቶ ሲስብ ሲስብ ቆየ። ከጥቂት ጉተታ በሁዋላ የድሮ ቮልስ የሚያክል ጫማ መሽልቆ ሲያወጣ ተስፋ ቆረጥኩ።
“መዳኒት ነው የምልከው አላልክም እንዴ?” አልኩ ደሜ ፈልቶ።
እሱ ምናለ:-
” ። ለወንድሜ ቁርጥማታም እግር ከዚህ ጫማ የተሻለ መዳኒት አይገኝለትም!! ”
——
ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣብያ እንደደረስኩ የጉምሩክ ፈታሹ የጀግና አቀባበል አደረገልኝ። አራት ላፕቶፕ የሸሸግሁበትን ሻንጣየን ተቀብሎ ያለምንም ፍተሻ ኬላውን አሳለፈልኝ። በመጨረሻ ልሰናበተው ስል ቀስ ብየ: የምጨብጠው አስመስየ እጁ ላይ መጦርያ የሚሆነው ነገር አስመጥኩለት። አመስግኖኝ ከሄደ በሁዋላ የሰጠሁት አምስት ዶላር እንደሆነ ሲረዳ እየሮጠ ተመልሶ ደረሰብኝ።
“በውቄ ይሄኮ ምሳ እንኳ አይገዛም”
“ታድያ ቁርስ ግዛበታ”
ትንሽ ከተጨቃጨቅን በሁዋላ:-
“ባይሆን ይቺን ግጥም አይተህ ሚዛን የምትደፋ ከሆነ ፌስቡክህ ላይ በመለጠፍ ካሰኝ” አለና ከኪሱ የታሸ ወረቀት አውጥቶ ሰጠኝ።
ተስማማሁ።
ግጥሙ ይሄው
———-
እምየ ኢትዮጵያ
ያለሽበት ችጋር😔
የማያልፍ ቢመስልም
አይዞሽ እናት አጋር!
በዚህ አካሄድሽ ሊያልፍልሽ አይችልም!!
ፀሀይ ኑሮ ከብዷት እንደ ሰው ተሰዳ
ጨረቃም ተዳክማ ያመት ረፍት ወስዳ
ሌቱ ቢጨልምም አይቀርም ይነጋል
አይዞሽ እማምየ
የሚባለው ነገር ህዝቢን ያዘናጋል!!
የሰማይሽ ቀለም አለላ መምሰሉን
የጠላት ቢላዋ ከጀርባሽ መሳሉን
ብናመዛዝነው
አይዞሽ እማምየ!
ሁሉም ለበጎ(ች)ነው!
ኢትዮጵያ ሆይ ኩሪ
ውብ አገሬ ኩሪ
ጠላትሽ ቢመኝም ሆነሽ እንድትቀሪ
-ያዘንተኛ ድንኳን!
እሰይ! እንኳን!!!
———–
ሰውየው ግን ጤነኛ ነው?