አያልቅ የብሶት ገጽ
ወዴትም ብንገልጠው፣
ሐዘን መጻፍ ነው ወይ ለኛ የተሰጠው ?
አያልቅ የቀን መንገድ -ብንሄደው ብንሄደው፣
ፈቀቅ አይል ጋራው- ብንወጣ ብንወርደው፤
ረቂቅ ግዝፈቱ አይፈርስም ብ’ንደው፣
በ’ሳት ሰረገላ ሰማዩን አንቀደው!
ምን ቢጠቁር ቆዳው -ምን ቢነጣ ፊቱ፣
ምን ቢሞላ ጓዳው- ቢራቆት ሌማቱ፣
ምድር ጥግ እስከጥግ አንድ ነው ሀለቱ፤
ሳይሻል አይቀርም እየሳቁ ማልቀስ፣
ሲጽፉት ይቀላል ፍቅርና ፤ መድረስ
በወደብ ፍለጋ አትባዝን አትድከም፣
ጀልባህን ማክበድ ነው መልህቅ መሸከም፤
በዕንባ ባሕር ላይ በሳቅ ጀልባ መቅዘፍ፣
በሰፊው ሕይወት ላይ ሳይቆሙ መንሳፈፍ፣
ከየትም መነሳት ወደየትም ማለፍ፤
መድረሻህ ጉዞው ነው፣
በወደብ ፍለጋ ዛሬህን አትግደል፣
ያለውን መኖር ነው ነፍስን ማደላደል፤
ምን ቢደምቅ ስብከቱ -ሳይንስ ቢተነተን ፣
የሰው መዳረሻው- መኻል ላይ መሟሟት፣
ወይ መኻል ላይ መትነን!!