በጠዋት ወደ ቢሮ ለመሄድ ራይድ ጠራሁና አንዱ ቪትዝ መኪና ውስጥ ገባሁ።
ተመቻችቼ፣ ቀበቶዬን አጥብቄ እንደተቀመጥኩ ጉዞ ጀመርን።
ከሬዲዮው ሁሌም በዚህ ሰአት፣ በሁሉም ጣቢያዎች ላይ የሚወራው የስፖርት ወሬ ያውም ከፍ ባለ ድምፅ ጆሮዬ ይገባል። ስፖርት ስለማልወድ ረጅሙ መንገዳችን ገና ምኑም ሳይነካ ሊሰለቸኝ ነው።
‹‹ኡፍ…›› አልኩ ሳላስበው።
‹‹ምነው?›› አለ ልጁ።
በሆዴ ያልኩት የመሰለኝ ኡ…ፍ ያለ ፈቃዴ ከአፌ መውጣቱን ሳውቅ ደነገጥኩና፤
‹‹ይቅርታ…ስፖርት…ኳስ ምናምን ስለማልወድ ነው…›› አልኩት ወደ ሬዲዮው እያመለከትኩ።
‹‹እ….ልቀይረዋ!›. አለ ልጁ ፈጠን ብሎ።
‹‹አይ…ችግር የለም…ደስ ካለህ አዳምጥ…እኔ ሌላ ነገር አስባለሁ…›› አልኩኝ የምንተፍረቴን።
‹‹አረ እኔም አልወድም…ሌላ ነገር ስለሌለ ነው የተውኩት…..›› አለና መንገዱን ትቶ፣ ስገባ እንኳን ባላየኝ አኳሃን ከላይ እስከታች በመርማሪ አይኖቹ አየኝ።
ግር አለኝ። በአስተያየቱ ምቾት በማጣት ባለሁበት ነቅነቅ አልኩ።
ከዚያ እየነዳ፣ አንዴ መንገዱን፣ አንዴ ቴፑን፣ አንዴ ደግሞ እኔን ሰረቅ አድርጎ እያየ (ምን ማለቱ ነው?) የሚከተሉትን ነገሮች በሚከተለው ቅደም ተከተል አከናወነ።
መጀመሪያ ቴፑ ውስጥ የነበረውን ሲዲ አወጣ። የጎሳዬ ተስፋዬ..‹‹ሲያምሽ ያመኛል›› ነበር።
ከዚያ ብሉ ቱዝ ለማጫወት ቴፑን አሰናዳና ከስልኩ ጋር ሊያገናኝ ሞከረ።‹‹አልገናኝም ብሏል›› የሚል መልእክት በተደጋጋሚ ሲመጣለት እሱን ተወ።
ከዚያ ከአንደኛው የመኪናው ኪስ ትንሽዬ ቀይ ፍላሽ ዲስክ አመጣና ቴፑ ላይ ሰካ።
አነበበበለት።
የመጀመሪያው ሙዚቃ መጫወት ጀመረ። የቴዎድሮስ ታደሰ ‹‹እየቆረቆረኝ›› ነበር። ምንኛ መታደል ነው! ዓርቤ በቴዲ ንጉስ ሊጀመር ነው! ምን ያደርጋል! በፍስሃ ወንበሬ ላይ ከመመቻቸቴ ግን ተቋረጠ።
ዞር ብዬ አየሁት።
አላስተዋለኝም።
ቀጥሎ የሚመጡትን ሙዚቃዎች ለመስማት እንኳን እድል ሳይሰጣቸው ‹‹ቀጥሎ›› የሚለውን እየተጫነ የሚፈልገው ዘፈን ላይ ሲደርስ ለቀቀው።
Kiki, do you love me? Are you riding?
Say you’ll never ever leave from beside me
‘Cause I want ya, and I need ya
And I’m down for you always
የድሬክ ኪኪ ነበር።
‹‹ይሄ ይመችሻል ብዬ ነው…እ?›› አለኝ እንደገና እያየኝ።
‹‹እየቆረቆረኝ››ን ይቆረቁራታል ተብሎ የድሬክ ኪኪ ለምን እንደተፈተልኝ የተገለፀልኝ ወዲያው ነበር።
ምክንያቱ ደግሞ ይሄ መከረኛ የዓርብ አለባበሴ ነው።
ከሰኞ አስከ ሃሙስ ‹‹ለቢሮ የሚመጥን›› አለባበስ ለብሼ ዓርብ ሲመጣ እንደማደርገው ‹‹ፈታ›› ያለ አለባበስ ነበር የለበስኩት። ቀላል ካናቴራ፣ ጫፉ ላይ ዘርፍ የተበጀለት ቬል ቦተም ጂንስ ሱሪ እና በሴንቲሜተሮች የሚያስረዝመኝ ከስክስ ጫማ ነው ያደረግኩት። ልጁ ከፍ ዝቅ አድርጎ ሲያየኝ የነበረውም ለዚህ ነው- ልብሴን አይቶ ሙዚቃ ሊመርጥልኝ።
ሳቄ መጣና፤
‹እህ…እሺ….›› አልኩኝ።
እንደ ተመቸኝ እርግጠኛ ሆኖ በኪኪ ታጅበን መንገዳችንን ቀጠልን።
ድሬክን እየሰማሁ በሰከንዶች ሚዛን ላይ አስቀምጦ ‹‹ራፕ ምድብ›› ውስጥ ባስገባኝ አለባበሴ ጉልበት ተገረምኩ። ይሄ ልጅ አላነጋገረኝም…ይሄ ልጅ ሊያውቀኝ አልሞከረም። ግን በአለባበሴ ተመስርቶ በሰከንዶች እይታ በፍጹም እርግጠኝነት የሙዚቃ ምርጫዬን መለየት መቻሉን ተማምኗል። ፈረንጅ ፈረስት ኢምፕሬሽን የሚለው ነገር ጉልበት ይሄ ነው። ጅንሴን አየ….ጫማዬን ተመለከተ….ማንነቴን ገመተ።
ከትላንት በስቲያ ስብሰባ ለመሄድ አድርጌው የነበረ ከቁርጭምጨጭምቴ የሚያልፍ ባለ አበባ የጨዋ እና ከሰኞ እስከ ሃሙስ የቢሮ ቀሚሴን አድርጌ ቢያገኘኝ ኖሮ ምን ሙዚቃ ይጋብዘኝ እንደነበር ለመገመት ሞከርኩ።
ምናልባት ጎሳዬን አያስወጣውም ነበር።
ምናልባት የቴዲ እየቆረቆረኝን እንዲቀጥል ያደርግ ነበር።
ወይ ደግሞ አስናቀች ወርቁን ፈልጎ ያጫወትልኝ ነበር።
ህእ።
ለማንኛውም የኔ የሙዚቃ ምርጫ እንደ ፔንዱለም ከዚያ ጥግ እዚህ ጥግ የሚምዘገዘግ ነውና በድሬክም፣ በኃላ በመጡት ጄዚ እና ካርዲ ቢ…በተለይ ደግሞ በዱዋ ሊፓ ‹‹ኒው ሩልስ›› ሙዚቃ ከልቤ መደሰቴ አልቀረም። ልብሴን መምሰሌ፣ የልጁን ግምት መሆኔ አልቀረም። ማንነቴ በልብሴ መወሰኑ በመጠኑ ቢቆረቁረኝም….
One: Don’t pick up the phone
You know he’s only callin’ ’cause he’s drunk and alone
Two: Don’t let him in
You’ll have to kick him out again
Three: Don’t be his friend
You know you’re gonna wake up in his bed in the morning
And if you’re under him, you ain’t gettin’ over him….እያልኩ መዝፈኔ አልቀረም።
በነገራችሁ ላይ if you’re under him, you ain’t gettin’ over him የሚለውን ወደ አማርኛ እንመልሰው ብንል ምን እንለው ይሆን? ‹‹የኔ እናት…ጭኖችሽን እየከፈትሽለት እንዴት ከልብሽ ሊወጣ ይችላል›› ነገር….?
ልዩ አርብ ይሁንላችሁ ወዳጆቼ!