(‹‹ከፋይ ገበሬ ነው›› ከገጣሚ ሞገስ ሐብቱ አንዲት ግጥም በውሰት የመጣች ሰንኝ ናት)
‹‹ኢትዮጵያ የአሜሪካን ህግ በጣሰ እና ባልተፈቀደ የአባይ ቦንድ ሽያጭ ምክንያት ከ6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ለአሜሪካ መንግስት ልትከፍል ነው። ›› የሚለውን ዜና ሰማን።
የኢትዮጵያ መንግስት አሜሪካ በሚገኘው ኤምባሲው በኩል ቦንዱን አሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሲሸጥ የሀገሪቱን ህግ ጥሷል። ቅጣት ይገባዋል ነው ጭብጡ።
….መቼም ሁኔታው በንዴት ያጦፋል። ያንገበግባል።
እንደኔ እንደኔ፤ የዚህ ዜና ርእስ ‹‹ ምንም ያላጠፋው ጎስቋላው የኢትዮጵያ ገበሬ እና ከርታታው የመንግስት ሰራተኛ የአሜሪካን ህግ በጣሰ እና ባልተፈቀደ የአባይ ቦንድ ሽየጭ ምክንያት 6ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለአሜሪካ መንግስት ሊከፍል ነው።›› ቢሆን ይሻላል።
ያኔ እውነት ይሆናል። ምክንያቱም፤
ከፋዩ የሀገሬ ገበሬ ነዋ!
ከፋዩ በተቀደደ ጫማ የሚሄደው የሀገሬ ምስኪን መምህር ነዋ!
ከፋዩማ ….ዘወትር ፖለቲከኞች በእጣ ፈንታው የሚቆምሩበት፣ በንዝህላልነታቸው የሚያስበሉት፤ ከምስር መግዣው ቀንሶ ለቦንድ የሚያዋጣው ሀገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ነው።
…የልጆቹ ዩኒፎርም ማሰፊያን ለአባይ ግድም የሚሰጠው ሀቀኛ የመንግስት ሰራተኛ ነው።
ያው እናውቃለን።
ይህችኛዋም እንደ ትንሽ ነገር ‹‹በአፈፃፀም ችግር›› ሰበብነት ትታለፋለች።
ዛሬ ዛሬ ብርቅ ያልሆነብንን ፖለቲካዊ ድቀትን ለመሸፋፈን የምትመጣው ‹‹የአፈፃፀም ችግር›› የተባለች ሀርግ ‹‹እየሰራን ነበር….ስናቃዳው ፈሰሰ›› የምትል አንካሳ ምክንያት ትመስለኛለች።
ግን እነሱ ሲያቃዱ የሚያፈሱት የእኛን ላብ ነው።
እነሱ ሲያቃዱ የሚያፈሱት ከሌለን የሰጠነውን ጥሪታችንን ነው።
….አረ መቼ ነው ይሄ ምስኪን ህዝብ የሌሎችን እዳ መክፈል የሚያቆመው?
መቼስ ነው ጥቂቶች ለሚፈጥሩት ጨለማ ብዙሃኑ ሻማ መሆን የሚያቆመው?
ምናልባት ደበበ ሰይፉ እንዳለው…፤
መንፈሳቸው ባልጫጨ፣
ሃሳባቸው ባልሸፈተ፣
ልባቸው (በራሳቸው ጥቅም) ባልከነፈ፣
ከሁሉም በላይ ግን መነሻቸውንም፣ ግባቸውንም ራሳቸውን ብቻ ባላደረጉ ሰዎች ስንመራ ይመስለኛል።
እስከዚያው ግን ከፋይ የሚዘራው ያጣው ገበሬ ነው።
የአውቶብስ ሳንቲም የሌለው የመንግስት ሰራተኛ ነው።
እስከዚያው ግን ከፋይ፤ እንቁላሉን ሰጥቶ ጨርሶ በስጋው የሚከፍለው ምስኪኑ ነው።