Tidarfelagi.com

“ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስአበባ”

ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ“ ከጉሬዛም ማርያም እስከ አዲስአበባ“የተባለ ሸጋ መጽሐፍ ጽፈው ለገበያ አቅርበውልናል። ለፌስቡክ ባለንጀሮቼ በልበሙሉነት የምጋብዘው መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ ያንድ ኢትዮጵያዊ የባዮሎጂ ሊቅ ግለታሪክ ቢሆንም፤ እግረመንገዱን ከጣልያን ወረራ እስከዛሬ ድረስ ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ በሚጣፍጥ አማርኛ ይተርካል ። ከባለታሪኩ ሕይወት ጋር የሩቅና የቅርብ ግኑኝነት ያላቸው ዝነኛ ኢትዮጵያውያን ታሪክና ገጠመኝ ተወስቷል። ስለ ሶማ ፋኖዎች – በላይ ዘለቀ ፤ እጅጉ ዘለቀና ሽፈራው ገርባ(”ይሻላል ሽፈራው ሶማ የቀረው ተብሎ የተዘፈነለት ) የቀረበው ታሪክ እስካሁን ያልተነገረ ነው ። በመጽሐፉ ውስጥ ፤ የፕሮፌሰር ሽብሩ ተማሪ የነበረው ለገሰ ዜናዊ የቅድመ-ሽፍትነት ባህርይ ተዳስሷል ።የለገሰ(መለስ)ዜናዊ ቅድመ አያት ፊታውራሪ ተሰማ ማን ናቸው? መነሻቸውስ ከየት ነው? መጽሐፉ አስገራሚ ምላሽ አለው።

ከመጽሐፉ አንድ ሁለት አንቀጾች ላቃምሳችሁና ዞር ልበል፤

ጸሐፊው በቀይኮከብ ዘመቻ ወቅት ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጋር የተገናኘ ትዝታቸውን ሲያወጉን፤

“ከቀናት በኋላ በምጽዋ ፌስቲቫል ለመሳተፍ ጉዞ ተደረገ። በመንገድ ላይ የአሉላ አባነጋ ሀውልት የሚቆምበት ቦታ ተመረቀ። ከምረቃው በፊት እዚህ ቦታ ላይ ሆነን የሊቀመንበሩን መምጣት ስንጠባበቅ ነበር። በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እና በአንድ ፖሊቲ ቢሮ ሲቪል አባል መካከል ጠንከር ያለ ክርክር ብጤ ተጀመረ።በአካባቢው ስለነበሩ የጣልያን መቃብሮች ምክንያት ሁለቱ መወዛገብ ጀመሩ።ዋናው ጉዳይ ሀውልቶቹ ይከሉ(ይወገዱ) የሚል አሳብ በፖሊት ቢሮ አባሉ ሲቀርብ ፕሮፌሰር መስፍን ለምን ሀውልቶች ይነሣሉ የሚል አቋም ይዞ ተነሣ።

እኛ አሸናፊዎች የአሸናፊነታችን አሻራ በቦታው ማስቀመጥ ቢሳነን ለምን ያሸነፍናቸው ጠላቶችን አስቀመጡ ብለን (ለእኛ አሸናፊነት መሰከሩ ብለን) መደንፋት ከፍ ያለ የግንዛቤ ጉድለት ነው ብሎ ጋሽ መስፍን ተከራከረ… ይህ ውዝግብ ሲካሄድ ብዙ የደርግ አባላት ከብበው ያዳምጡ ነበር።ይህን ውዝግብ በሚያስደነግጥ መልኩ ጋሽ መስፍን ደመደመው፤“ አንተና አንተን የመሰሉ ሰዎች እኮ ናቸው እነኝህን ሰዎች ወደ ገደል እየመሯቸው ያሉ”ብሎ ኃይለቃል ተናገረ።”

ጸሐፊው ስለራስ ደጀን በጻፉት ላሳርግ።

”ከካናዳ በተመለስኩበት አካባቢ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያደረገውን አገራዊ ስህተት ለማረም ሞክሬ ነበር። አንድ የአየር መንገዱ ማስታወቂያ ላይ “ራስ ዳሸን”የሚል ጽሁፍ አይቸ ይህንን ስህተት ለማረም አንድ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ጽፌ ነበር። ፍሬ ነገሩ ስሜን አካባቢ ጎንደር ብሎም ኢትዮጵያ ውስጥ“ራስ ደጀን ” አባ ያሬድ“ ቧሂት” እና ሌሎች የተራራ ሰንሰለቶች እንጂ ራስ ዳሸን የሚባል የሚባል የለም የሚል ነበር….
…ሁለት የፈረንሳይ ኦፊሰሮች “ፌሬ እና ጋሊኒየ”(Ferret and Galinier)በ1830 ዓም መጀመርያ አካባቢ ተራራውን ከጎበኙ በኋላ ይህንን ለአውሮፓ ሲያስተዋውቁ “ደጀን ”ማለት ተስኗቸው“ዳሸን” ስላሉ እኛ የእነሡን ስተት እንደማረም ያን ስተት አንግበን እየተንገታገትን በሌለ ስም እየተጠቀምን ነው ያለን“
(ገጽ266)

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

One Comment

  • hiwanedesta28@gmail.com'
    Hiwane commented on November 23, 2016 Reply

    Shibru Gotegna new!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...