. . . አብዮት ሲመጣ (እንዲመጣ ሲደረግ) ልብ ወለድ መጽሃፍት ቢረባም ባይረባም በፓምፍሌት ተተኩ፡፡ ለመጀመሪያ ሰሞን ደስ የሚል ነገር ነበረው፡፡ ምክኒያቱም አዲስ ነው፡፡ (እዚህ ዘመን ላይ ቦታ ስለማይበቃን ልዝለለው እንጂ በሰፊው የምለው ኑዛዜያዊ ግለ ሂስ ነበር)
ብዙ ሳልቆይ ሲጀመር መሰላቸቴን ያጠፋው የመሰለኝ ለአብዮት/ትግል ማሟሟቂያ የተፈጠረው ስነ ጽሁፍ ወደ አሰልቺ ነገር ተለወጠ፡፡ ከላይ ያነሳሁልህን ‹ሰው ምን ይለኛል?› እና ‹እግዜር ምን ይላል?›ን ፖለቲከኞች ከሕዝብ ነጥቀው ‹ድርጅቴ ምን ይለኛል?› በሚለው ተኩት፡፡ እግዚአብሄር ከስልጣን ወረደ፡፡ ባህላዊው የተባለው ሕብረተሰብ ኋላ ቀር ነው ተባለ፡፡ እግዚአብሄር ቢሞትም የነበረው ቢናቅም ቦታውን የነዚህን ሁለት ስራ መስራት እንችላለን የሚሉ ድርጅቶች ወሰዱት፡፡
በልጅነቴ ያስደስተኝ የነበረው ግን ልብ ያላልኩት ያለማንም ቁጥጥር ማሰብ መፈለጌ ከፈተናው አላመለጠም፡፡ እደውም ፈተናው በፒር ፕሬዠር (Peer Pressure) ታጠቀ፡፡ በተለያየ አቅጣጫ የአብዮቱ ግራኞች (ተቃዋሚ የሚባለውም ሁሉም) ደራሲያንና ድርሰትን አጥፍተው ነው ለተሰሚነት የሰሩት፡፡ ማለት ከኢማጂኔቲቭ ሊትሬቸር ወደ ፕሮፓጋንዳ ተሄደ፡፡ ቀደምት ደራሲያን በተለያየ ስየማ እየተቀነበቡ (ፍሬምድ እየሆኑ) ዝም እንዲሉ ሆነ፡፡ የዚያን ጊዜ ድርሰቶች (ግጥሞች) በአብዛኛው ፕሮፓጋንዳ ነበሩ፡፡ ፕሮፓጋንዳ ታዲያ ብዙ ጊዜ ስላለቀ እውነት ደጋግሞ የሚያወራ ነው፡፡ ፓርኖግራፊክ ነው፡፡ በተቃራኒው የፈጠራ ደራሲና የፈጠራ ድርሰት ቢዋጣም ባይዋጣም በምናባቸው አማራጭ ማሕበራዊ እሴት ያሳያሉ፡፡
የጸጋዬ ገብረመድህን ግጥሞች ከጸጋዬ ደብተራው ግጥሞች የበለጠ ደስ ይሉኛል ካልክ ባንዳ ነህ፡፡ በተገላቢጦ ካልክ አናርኪስት ነህ፡፡ የፈለግከውን የወደድከውን ለመውደድ በየትም አቅጣጫ መናገር የማትችልበት ጊዜ ነበር፡፡ ይሄን የተረዳሁት ረቂቅ ፈላስፋ ስለነበርኩና ሁሉ ነገር ስለገባኝ አልነበረም፡፡ ተደጋግሞ ስሰማውና በቀጥታና በተዘዋዋሪ ስከለከል ሰለቸኝ፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መከልከል ይሰለቻል፡፡ ልክ ተደጋግሞ እንደተጠጣ አጃ ወይም ጠዋትና ማታ እንደተበላ ካሮት ወይም የፈለግከውን፡፡
ምናልባት የገጠመኝ የተለየ ይሆናል፡፡ የሩስያ ልብ ወለድ ካነበብክ የደባሪ ሩኪ (ሶሻል ኢምፔሪያሊዝም) ታነባለህ፣ የአሜሪካን ደራሲ ካነበብክ በኢምፔሪያሊዝም ልትለከፍ ነው፡፡ ወይም ጆሊ ጃክ ነህ፡፡ ዋናው ማንበብህ አሳስቧቸው ሳይሆን የዛን ዘመን ትውልድ ለማጥፋት ሆነ ብለው ታጥቀው የተነሱ ሰዎች ያሉ ይመስላል፡፡
ማን ገባው? ምናልባት የገባቸው እንደ አቤ ጉበኛ እንደ ሀዲስ አለማየሁ ያሉ ደራሲያን ነበሩ፡፡ ‹አድሃሪ› በተባለ ቃል ተቀንብበው እንዲሰወሩ ሆነ፡፡ የገባው ጥቂት ነው . . .
‹‹ . . . . ስለ ትከሻዎች ወግ ላንሳ፡፡ ከፈረንጆች የተወሰደ አባባል መሰለኝ፤ ‹የዛሬዎቹ ትንንሾች ታላላቅ የሚሆኑት በትላንት ታላላቆች ትከሻ ላይ ሲቆሙ ነው›› የሚል፡፡ ይሄን ተረት በወተት ጥርሶቻችን ነክሰን እምነት ባቀለጣቸው የልጅ አይኖቻችን እናያለን፡፡ ስለዚህ ትከሻ ፍለጋ እንወጣለን፡፡
ከሚያጋጥሙን አንዳንዶቹ ትከሻ የላቸውም፡፡ ጫማችንን አውልቀን ልንፈናጠጣቸው ስንጠጋ ፓስታ የመሰሉ ሰዎች ያጋጥሙናል፡፡ ትመለሳለህ፡፡
አሁንም ‹የትከሻ ያለህ› ትልና ወይም ይወራና ስትሄድ እነዚህ ደግሞ ትከሻ አላቸው፡፡ ግን ደብቀውታል፡፡ አላቸው ግን ብትፈልግ አይገኝም፡፡ የሆነ ኩታ ውስጥ እየተነፈሰ ተቀምጧል፡፡ ምክኒያቱም ልጆች ነንና ለምጸት አልደረስንም፣ ያኗኗር አያኖ አይገባንም፡፡ ከዛ ደግሞ መታገስ ስለሚያሳቅፍህ በሳልነት የሚሰበከው የዛገ ዴዜዴራታ አለ፡፡
ሶስተኛው ትከሻ ብዙ ሲወራለት ትሰማና እግርህን ተጣጥበህ ለመሳፈር ትሄዳለህ፡፡ ትከሻው አለ፡፡ ትከሻውም ግርማ አለው፡፡ ገና እንደተፈናጠጥክ ግን ትወድቃለህ፡፡ አየህ የይስሙላ ነው፡፡ እንዲያንሸራትተን ብለው ትከሻቸውን ቫዝሊን ቀብተውታል፡፡ ‹ጸባይ ስለሌለው ነው መፈናጠጥ ያልቻለው› ብለው በሚያምናቸው መዋቅር ውስጥ ይቶከቱካሉ፡፡ ሲገርመን ነበር ትከሻቸው ‹ለምን ያብለጨልጫል?› እያልን፡፡ ‹የሚፈልቀው እርጥበት ሜዳሊያ ነው› ብለውን ነበር፡፡ ጠርጥረን ነበር ግን ‹አትጠርጥሩ ኦፕቲሚዝም ጥሩ ነው› ተባልን፡፡ አመንናቸው፡፡ አዳልጦን ከወደቅንበት ተነስተን፣ አቧራችንን አራግፈን አለ የተባለውን አራተኛ ትከሻ ለመፈለግ እንወጣለን . . . ››
. . የማህሌት አርዕስት ሲጀመር ‹ስዕል በብጥስጣሽ ጨርቆች ላይ› የሚል ነበር፡፡ ይሄ አርዕስት ‹አይስብም› ይበሉ ምን ትዝ አይለኝም፡፡ ‹ይለወጥ› ተባለ፡፡ ‹ማህሌት› ሆነ፡፡ የድርሰቱ ጉዳይ ስለማህሌት አልነበረም፡፡ በኪነት ስራ ላይ ስለሚከሰት የውክልና (Representation) ችግር ነው፡፡
የተቀበልኩበት ምክኒያት መታዘቡ ስለሰለቸኝ ነው፡፡ ምናልባትም ይታተም ብዬ ይሆናል፡፡ ትዝ አይለኝም፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ ብዙ ነገሮች ማመን ያቆምኩበት ዘመን ነው፡፡ ብዙ ነገሮች ሳሰላስል ‹የትም አንደርስም› የምትባለዋ በአእምሮዬ የገባችበት ዘመን ነው፡፡
‹አይታተም› ቢሉም አይታተምም፡፡ ‹ይታተም› ቢሉ ይታተማል፡፡ ግድ አይሰጠኝም፡፡ ምክኒያቱም ታች በጥልቀት ማንም የትም አይደርስም፡፡ ሀሞት የለሽነት ወይም ግድ የለሽነት አልነበረም፡፡ ቁንዳላህ ላይ እንደ ዶቃ የታሰረ የማይታይ መራራ ንቃት አለበት፡፡ ሳይመጣ አውቀዋለሁ፡፡ ትንንሽ ነገሮች ናቸው እነዚህ፡፡ ግን እኮ አንድን ስርዓተ ማሕበርና ሶሻል ቡድን ለመገመትና ለመረዳት ሰው ያልሰራውን መስራት የለብህም፡፡ በግብዝነቱ እጅ ከፍንጅ ከተያዘ ይበቃል፡፡
ኤቭሊን ዎ አንድ ስለ ኢትዮጵያ በጻፈው ፅሑፍ ያለው ትዝ ይለኛል፡፡ (ኢትዮጵያን ኋላ ቀር ነች እያሉ የሚተቹትን ሲነቅፍ)፡፡ እንዳለ ቃል በቃል ማለት አልችልም፡፡ ዋና ሃሳቡ ግን እንዲህ ነው፤
‹የአንድን ሕብረተሰብ ትልቅነት የምትገምተው አውሮፓን ስላልመሰለ ወይም የሰለጠኑ አገራትን ስላልመሰለ ሳይሆን በራሱ እምነትና የእሴት ስሌት ውስጥ የተቃረነ ነገር ሲሰራ ነው›
አሪፍ አባባል ናት፡፡
‹‹ . . . ከማሕሌት በኋላ ገና ማሕሌት ሳትታተም አዲስ አበባ እያለሁ ‹የብሩክታዊት ጠጠር› የተባለ ሌላ መድብል ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሰጥቼ ነበር፡፡ ተገምግሞ መልስ እስካገኝ ሶስት አመታት አካባቢ ወሰደ፡፡ መልሱ ሲደርሰኝ ‹ድርሰቶችህን አብዛኛው ተደራሲ ሊረዳቸው ስለማይችል ሊታተሙ አይገባቸውም› የሚል ነበር፡፡
ከነዚህ ከተገፉት ድርሰቶች ብዙዎቹ አሁን በቅርብ የታተመው ‹አለንጋና ምስር› መድብል ውስጥ አሉ፡፡ ይከብዳሉ? አይከብዱም፡፡ ዛሬ ስለሆነ አይደለም፡፡ ድሮም አይከብዱም፡፡ ውሳኔው የተሰጠው ‹ተደራሲውን/አንባቢውን እናውቃለን› በሚል ሽፋን ስር ነው፡፡
የሚሰጡት ምክኒያት ከጆሮህ ላንፋ ርቆ አይሄድም፡፡ ቲያትሩ ስለሚዲክምህ ‹አቦ ምን ይደብሩናል!› ብለህ ስራህን መቀጠል ነው፡፡ . . . . ››
* * *
. . . የምስላቸው ልጆች ሕብረተሰብ ውስጥ ያላቸው ቦታ ፈታኝ ነው፡፡ ልጆቹን ሳይሆን አብዛኛውን ግዜ አካባቢያቸውን እንድናይ ያደርገናል፡፡ የልደት ቀን ሲያከብሩ የሚውሉ፣ ከረሜላ የለንም ብለው የሚያለቅሱ አይደሉም፡፡ ብዙዎቹ የሚገቡበት የግጭት ስፋት አዋቂዎች ከሚገቡበት ያነሰ አይደለም፡፡ መከፋታቸው (ጥላውን) መደሰታቸው (ውጋገኑን) ያሳደጋቸው ሕብረተሰብ ላይ ይጥላል፡፡››
አዳም ረታ ከአዲስ ነገር ጋዜጣ ጋር ካደረገው ቃለ መጠይቅ የተወሰደ
2001 ዓ.ም
One Comment
i like it