Tidarfelagi.com

ከአበታር ወደ አባተ

አንዳንዴ የአማርኛ ዘፈን ቪዲዮ ሳይ ብዙ ነገር ይገርመኛል፤ የአማርኛ ሙዚቃ ቪድዮ ከማየትሽ በፊት ጃንጥላ መያዝ ይኖርብሻል ፥ ዝናብ የሌለው የፍቅረኞች ትእይንት ጥቂት ነው፤ በገሀዱ አለም ያገራችን ሰማይ ያሻሮ ብረት ምጣድ ማለት ነው፤ የብብታችን ላብ ካዲሳባ ሰማይ የተሻለ ያካፋል፤ ታድያ ዳይሬክተሮች ይሄን ሁሉ ዝናብ ከየት አመጡት? ቆየቸ ሳጣራ ፥ ከካሜራ ባለሙያው ጎንለጎን ጀሪካን አዝሎ የሚከተል የፍሳሽ ባለሙያ መኖሩን አጋገጥሁ፤ ለካ በመዲናይቱ ውሀ የተወደደው የሙዚቃ ኢንዱስትሪው አላግባብ ስለሚያባክነው ነው።

ከፍቅር ቀጥሎ ብዙ የተዘፈነለት ጀግንነታችን ነው፤ ጀግንነት ሲነሳ አድዋን ድል ማጣቀስ የማይቀር ሆኗል ፤ባማርኛ ሙዚቃ ቪዲዮ ውስጥ አድዋ ሲቀርብ ባጭሩ እንዲህ ነው፦የጣልያን ጦር ይሮጣል፤ የወገን ጦር ያባርራል፤ ዘፋኙም ይፎክራል፥
ጣልያኖች መሮጥ ሲሰለቻቸው ይወድቃሉ፤ እየተረፈረፉ ያልቃሉ፤ አንዱ ቪዲዮ ላይማ አንዱ አበሻ ሰበዝ እምትመስል ጦር ይዞ ጠመንጃ የያዘውን ጣልያን በአምስት ርምጃ ርቀት ሲያባርርው ታያለህ፤የዱላ ቅብብል እንጂ ውጊያ አይመስልም፤ ከጣልያን ወገን የሚረፈረፈውን ያክል ከወገን ጦር አንድ ሰው ሲወድቅ አለመታየቱ ያስገርማል፤ እነ ፊታወራሪ ገበየሁ እኮ በወረርሽኝ አይደሉም የሞቱት ዠለስ ፤ አባቶቻችን ጦርነቱን “ ተጋድሎ “ ብለው የጠሩት በከንቱ አይደለም፤ መግደልን ብቻ ሳይሆን መገደልን ጭምር ስለሚያካትት ነው፤

እስካሁን ካየሁት ሁሉ ለየት ያለው ፥ ቴክኖ ላይ የሚራቀቅ አንድ ዲያስፖራ የሰራው ያድዋ አኒሜሽን አጭር ቪዲዮ ነው፤ ፊልሙ ሲጀምር ጣልያኖች ሀመር መኪና በሚመስል ዘናጭ ካሚዮን ተጭነው ወደ አድዋ ይመጣሉ፥ ( በዘመኑ ጣልያኖች የተጠቀሙት የመስክ መጉዋጉዋዣ አህያና በቅሎ ነበር) ከዚያ ኡዚ በሚመስል ጠመንጃ አውቶማቲክ ይተኩሳሉ፤ ( በርግጥ በዘመኑ አውቶማቲክ ፉከራ እንጂ አውቶማቲክ ተኩስ አልነበረም) ጦርነቱ ሲጀመር የኢትዮጵያ አርበኞች የወርቅ ጋሻና አንግበው በጎራዴና በገጀራ መሀል ያለ ነገር እያወዛወዙ ወደ ጣልያን መድፈኞች ሲጋልቡ ታያለህ፤ ሌሎች ደሞ ሲሮጡ ትመለከቻለሽ! ያሯሯጣቸው ፍጥነት አይነሳ! ሁሴን ቦልት እንደዚያ አይፈጥንም! ወደ መድፍ አፍ እሽቅድድም እንደዋዛ? ከፊታቸው ያለው አፈሙዝ ነው ባውዛ?

አንዱ አርበኛማ የመድፉ ጥይት በግንባሩ አቅጣጫ ሲመጣበት እንደ ቅዝምዝም ሽል ብሎ አሳለፈውና ወደፊት ገሰገሰ፤ አንደኛው አርበኛ ደግሞ ጋሻውን እንደ ዲስክ ወረወረው፤ ጋሻው የጣልያኑን ደረት ሰነጠቀው፤ ብቻ ባለ ቴክኖው አይፈረድበትም፥ ከአቫታር ወደ አባተ መሸጋገር ቀላል አይደለም፤ የሙዚቃም ሆነ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በታሪክ ዙርያ መጠበብ ሲያምራችሁ የታሪክ ባለሙያ ብታማክሩ አትጎዱም።

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...