Tidarfelagi.com

ከታጋቹ ማስታወሻ የተቀነጨበ

ብዙ ያሜሪካ ላጤዎች ውሻ አላቸው። እኔ ውሻ የማሳድርበት አቅም የለኝም፤ ቢሆንም በቅርቡ ቤት ውስጥ ከሚርመሰመሱት ጉንዳኖች መካከል የሰልፍ መሪውን መርጨ አለመድኩት፤ ምሳ ስበላ አንድ ሩዝ ፍሬ ጣል አደርግለታለሁ፤ ወደ ዘመዶቹ ይዞ ሊሄድ ሲል አንገቱን ይዤ አስቀረዋለሁ፤ እኔ የስዊድን ቮድካየን ስቀመቅም፤ ለገብሬ(የጉንዳኔ ስም ነው) በቆርኪ ወተት እቀዳለታለሁ፤ እየተላመድን ስንሄድ ከክብሪት ሳጥን ቆንጅየ ቤት ቀለስኩለት፤ ብዙም ሳይቆይ ትዛዝ ሰጥቷቸው ነው መሰል ሌሎች ጉንዳኖች ከቤቴ ጠፉ! ፤ እየሰነበተ ግን እንደ ጥንቱ መባከኑን ሲተው ወፍሮ ጥቁር እንቁላል መሰለ ፤ በቀደም ለታ ከኦክስፎርድ ዲክሽነሪ ላይ ለመውረድ ሲሞክር ተፈጥፍጦ ሞተ፤

ቀሳ የመውጣት አንዱ ችግር ራስህ በጣም እንድታዳምጥ ማስገደዱ ነው ፤ እና ራስህን በጣም ካዳመጥክ የሌለ ነገር ሁሉ ሊሰማህ ይችላል፤ በጣም ሲቸግረኝ ለሀኪም ወዳጄ እደውልለታለሁ፤ እሱ ደሞ ከየአቅጣጫው ችግሩ መስማት ስለሰለቸው ነው መሰል በችግሬ ማላገጥ ጀምሯል።

“ ችግር አለ?” ይለኛል ስልኩን አንስቶ፤
“ ባክህ! ስውጥ ጉሮሮየን ያመኛል”
እለዋለሁ።
አስር ደቂቃ ያክል ዝም ብሎ ሲቆይ መፍትሄ ሊያመጣ መስሎኝ ነበር፤በመጨረሻ እንዲህ አለ!
“ አንተ ዝምብለህ ለምን ትውጣለህ?”
ከሁለት ቀን በሁዋላ ደግሞ ደወልኩ፤
“ችግር አለ?”
“ ባክህ ይሄ ን ያክል ጊዜ ተጠንቅቄ መጨረሻ ላይ ሳልረታ አልቀረሁም”
“ደሞ ምን ሆንክ ?”
“ ሃይለኛ ራስ ምታት አለብኝ ”
“ ትኩሳት አለህ?”
“ አለኝ”
“ በቃ ትንሽ ታበድረኛለህ ! እኔ እምኖርበት ከተማ በጣም ይቀዘቅዛል ! ”
“ ምነው ይሄንን ታልማ ታልማ እሚል ቀልድህን ትተህ ችግሬን ብሰማኝ” አልኩት ንድድ ብየ!
“ ሪላክስ! ሌላስ ምልክት አለህ?”
“ ጅማቴን ይጨመድደኛል”
“ ሌላስ?’
” ድንዝዝ እሚያረግ ስሜትም አለኝ’
‘ አዝናለሁ! ቤት ውስጥ ተኮራምተህ ይሄን እየዋልህ ሪህ ተጫውቶብህ ነው፤
ደነገጥሁ “ የሚያሰጋ ነገር አለው ?” አልኩት!

“ Well እግርህ አካባቢ መለስተኛ መሽመድመድ ሊያስከትልብህ ይችላል፤ግን አትጨናነቅ! ክትባቱ ሲደርስ አዝለን እንወስድሀለን”

Bewketu Seyoum (Ge’ez: በዕውቀቱ ስዩም) is an Ethiopian writer and poet from Mankusa, northwest of Addis Ababa.

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...