ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የአሜሪካ ጉብኝታቸውን ፈጽመው ወደ አዲስ አበባ የሚመለሱበት ሰዓት ላይ ደርሰናል። ልዑካኑ በሁለት ተከፍለን ነበር ከሆቴል ወደ አውሮፕላን ማረፊያው የሄድነው። የመጀመሪያው ቡድን ከጠዋቱ 4፡30 ሲነሣ፤ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ 6፡15 ላይ ከሆቴል ተነሣ። አስቀድመን ለመነሣት ያሰብነው ከጠዋቱ 4፡30 አካባቢ ነበር። ነገር ግን ማክሰኞ ጠዋት የነበረው ውይይት ጊዜ ወሰደ።
ከሚነሶታ ስንነሣ እኩለ ቀን አልፏል። አውሮፕላኑ ሦስት ክፍሎች ስለነበሩት የመጨረሻው ክፍል ሁለተኛው ወንበር ላይ ተቀመጥኩ። ድካሙ ሊሰማኝ ጀምሯል። ዕንቅልፍ በትክክል ከተኛሁ ዐሥር ቀናት አልፈውኛል። አብዛኛውን ጊዜ የምተኛው ከአንድና ከሁለት ሰዓት አይበልጥም። አብዛኛዎቹ ሥራዎች የሚጠናቀቁት ሌሊት ስምንት ሰዓት ካለፈ በኋላ ሲሆን የሚጀመሩት ደግሞ ከንጋቱ 11 ሰዓት ላይ ነው። ዶክተር ዐቢይ በእነዚህ የጉብኝት ቀናት ከ2 ሰዓታት በላይ የተኛበትን ቀን አላስታውሰውም። የቀን ጉባኤያት፣ የምሽት ስብሰባዎች፣ የሌሊት የጎንዮሽ ውይይቶች በየቀኑ የተለመዱ ነበሩ። ያውም ከረዥም በረራ በኋላ። በድካም የሚዘሩ በደስታ ያጭዳሉ የሚለው እየታሰበ እንጂ ጉዞው አትራፊና አድካሚ ነበር።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሁለተኛው የልዑካን ቡድን መጣ። ቤካ መገርሳ የሰጠኝን ‹True North> የተሰኘውን መጽሐፍ እያነበብኩ ነበር። አንድ የፕሮቶኮል ሹም መጣና ዶክተር ዐቢይ እንደሚፈልገኝ ነገረኝ። መጽሐፌን ብቻ ይዤ ወደ መጀመሪያው ክፍል ሄድኩ። ‹ለምን ወደ ኋላ ሄድክ?› አለኝ። ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ለሚሳፈሩት አባቶች ቦታ ለመልቀቅ ብዬ ወደ ኋላ መሄዴን ነገርኩት። ‹ቦታውኮ በቂ ነው› አለና መካከለኛው ወንበር ላይ እንድቀመጥ ጋበዘኝ። የፕሮቶኮል ሹሙ ቦርሳዬንና ኮቴን ይዞት መጣ። የተወሰነ ጊዜ ስለነበሩት ፕሮግራሞች ስንነጋገር ቆየን። አውሮፕላኑ ከተነሣ በኋላ ደግሞ ከሌሎች ባለሞያዎች ጋር ለሚመጡት አባቶች ወንበር መደልደል ጀመርን።
ዲሲ ላይ 43 ሰዎችን እናሳፍራለን፡፤ ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ። ሁሉንም በሁለት ክፍሎች ደለደልናቸው። አውሮፕላኑ ዳላስ አውሮፕላን ማረፊያ ካረፈ በኋላ ቅዱስ ፓትርያርኩን የያዘው መኪና መጣ። መኪናው ወደ ላይ ከፍ ካለ በኋላ በዊልቼር ለመግባት አስቸጋሪ ሆነ። የአውሮፕላኑና የመኪናው ወለል ሊገጣጠም አልቻለም። ዊል ቼሩ ደግሞ መቀየር ነበረበት። ይህ ሥራ አውሮፕላኑ ውስጥ በነበርነውና በአየር መንገዱ ሠራተኞች ትብብር እስኪከናወን ድረስ ጊዜ ፈጀ። በመጨረሻም ወደ መጀመሪያው ክፍል የሚገቡትን አባቶች ተቀብለን ሁለተኛውን ቡድን መጠበቅ ጀመርን። ሁለተኛውና 36 ሰዎችን የያዘው ቡድን በኋላ በር በኩል ገባ። የሕክምና ዕቃዎችና ሌሎች ነገሮች እስኪጫኑም የራሱን ጊዜ ወሰደ።
ከተፈቀደልን ጊዜ ዘግይተን ነበር። ሁሉንም ነገር አጠቃልለን በሩ ከተዘጋ በኋላ ከዳላስ አውሮፕላን ጣቢያ ለመነሣት ወረፋ ያዙ አያሌ አውሮፕላኖች ከፊታችን ተሰልፈው ይታዩ ነበር። ተራችን ደርሶ አየሩን እየሰነጠቅን ወደተፈቀደልን ከፍታ ወጣን። ይህ ጉዞ አስገራሚ ጉዞ ነው። ከዋሽንግተን ዲሲ ወደ አዲስ አበባ የሚደረግ ጉዞ አይደለም። ከ1984 ዓም ወደ 2010 ዓም የሚደረግ ጉዞ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ወደፊት ምንጊዜም ሲነሣ የሚኖር የዕርቅና የአንድነት ጉዞ ነው። የአውሮፕላኑ ፓይለት በመጨረሻ እንደተናገረውም መንግሥትና ቤተ ክህነት በአንድነት የተጓዙበት አስገራሚ ጉዞ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትርና ፓትርያርክ በአንድ ላይ የተሣፈሩበት ጉዞ ነው። አራተኛው ፓትርያርክ ከአራተኛው የኢሕአዴግ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የሚጓዙበት ነው።
ዶክተር ዐቢይ አውሮፕላኑ ውስጥ እየዞረ ሁሉንም ተሣፋሪዎች ሰላምታ ይሰጥ ነበር። ፎቶ በሽበሽ ሆነ። እዚህም እዚያም የደሩ ጨዋታዎች ነበሩ። እየቆየ ሰው ሁሉ እየተዳከመ መጣ። ቦታዬን ቀየርኩና ከብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ ጎን ተቀመጥኩ። ብጹዕ አቡነ አብርሃም፣ ብጹእ አቡነ ጎርጎርዮስና ብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሚያቀርቡትን ሪፖርት ማዘጋጀት ጀመሩ። እኔም የጽሕፈት አገልግሎት ለመስጠት አብሬያቸው ነበርኩ። ከአራት ጊዜ በላይ ታርሞ በመጨረሻ ሥራው ለብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ተሰጠ።
አሁን ማረፍ እንችላለን ብለን ወደየወንበራችን ስናመራ አንድ አባት መታመማቸውን ሰማን። ወደ ኋለኛው ክፍል ስንገባ ታማሚው ራሳቸውን አያውቁም፡፤ ቅዱስነታቸውን ለመንከባከብ ሁለት ነርሶችና አንድ ሐኪም አብረውን ነበሩ። ሦስቱም የነፍስ አድን ሕክምና ላይ ተሠማሩ። ኦክስጅን እየሰጡ ወለል ላይ አስተኟቸው። ሐሳብና ጸሎት ከየአቅጣጫው መጣ። አዲስ አበባ ስንደርስ አምቡላንስ እንዲዘጋጅ ለመንገር ወደ ፓይለቶቹ ሄድኩና ለዋናዋ አስተናጋጅ ነገርኳት። ከአብራሪዎቹ አንዱ ወጥቶ አነጋገረኝ። ቦሌ ካሉት ጋር ተነጋግሮ መልሱን ሊነግረኝ ወደ ጋቢናው ገባ። እኛም ወደ ታመሙት አባት ሄድን። ፈተናው ገና አላለቀም። የምድሩ ነገር ሲያልቅ የሰማዮቹ የክፋት ሠራዊት ታጥቀው ተነሥተዋል። እርሳቸውን እያስታመምን ሌላ ሰው ደግሞ ታመመ። አሁን ውጊያው ከሥጋና ከደም ጋር አለመሆኑን ተረድተናል። ሁሉም እንደየ እምነቱ ይጸልይ ነበር። ሐኪሞችና ነርሶቹም ርብርባቸው ሁለቱ ላይ ሆነ።
የታመሙት አባት መለስ እንዳለላቸውና በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ሐኪሙ አበሠረን። ብዙዎቹ አባቶች ከሃያ ዓመታት በኋላ ነው ወደ ሀገራቸው የሚመለሱት። ናፍቆቱና ጉጉቱ አለ። ትኩረታቸው ጉዞው ላይ ስለነበር ምግብ አልቀመሱም። ዋናው ችግር የነበረው እርሱ ነው። የኛ አባቶች ደግሞ ለአውሮፕላን ምግብ እስከዚህም ናቸው።
ቅዱስነታቸውን ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ለመውሰድ የሚያስችል ምቹ መኪና መኖሩ ተጠቆመ። እርሱን ለማግኘት ግን አዲስ አበባ ከሚገኙት ጋር መነጋገር ያስፈልግ ነበር። እንደገና ተመልሼ ከአብራሪዎቹ ጋር ተወያየን። መኪናው የሚገኝበትን አድራሻና እንዴት ማስፈቀድ እንደሚችሉ ጠቆምኳቸው። እነርሱም ወደ አዲስ አበባ ለመደዋወል ገቡ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አምቡላንሱና መኪናው ዝግጁ መሆናቸውን ነገሩን። የአትላንቲክ ውቅያኖስን ያቋረጥነው በዚህ ዓይነት ሁኔታ ነበር።
አብራሪው ወደ አዲስ አበባ እየተቃረብን መሆኑን አበሠረን። ሐኪሞቹ የውስጥ ዝግጅት ማድረግ ጀመሩ። ታምመው የነበሩት ሁለቱም አሁን ተሽሏቸው ወንበራቸው ላይ ተቀምጠዋል። ሚነሶታና ዋሽንግተን ዲሲ የወሰደው ጊዜ ብዙ በመሆኑ እንገባለን ከተባለበት ሰዓት እጅግ ዘግይተናል። ሕዝቡ ከጠዋቱ ጀምሮ እንደተቀጠረ ሰምተናል። ግን ምን ይደረግ። ይህ ጉዞ በዓይነቱ የተለየ በመሆኑ የሚያጋጥመው ነገርም የተለየ ነው።
አዲስ አባባ እንዳረፍን ቅዱስ ፓትርያርኩን ለማውረድ አሁን በዝርዝር በማልገልጻቸው ሕክምናዊ ነገሮች ምክንያት ብዙ ጊዜ ወሰድን። ዊልቼሮቹ ሲቀያየሩ ሌላ ጊዜ ጠፋ። የመጀመሪያውንና ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር የነበረውን ልዑክ በጎኑ በር አውርደን እንደገና ሌሎቹን በኋላ በር ማውረድ ነበረብን። ይህ እስኪሆን ድረስ ሁላችንም የመጀመሪያው ክፍል ውስጥ ተቀምጠን ነበር። በአውሮፕላን ማረፊያው የተሰለፉትን ካህናት፣ መዘምራን፣ መለከት ነፊዎችና የማርሽ ባንዱን እያየን እንደነቅ ነበር። በመጨረሻ በሁለት በር የወረዱት ልዑካን አውሮፕላኑን ዞረው በመምጣት በቢዝነስ ክፍል መውረጃ በኩል ሲገናኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎቻችን ወረድን።
አካባቢው በዝማሬ፣ በከበሮና በመለከት ተንቀጠቀጠ። ጥምቀት ነበር የሚመስለው። ሁለቱ ቅዱሳን አባቶች ሲገናኙ የነበረውን ስሜት ቃላት ይገልጹት ዘንድ ዐቅም ያንሳቸዋል። የተወሰንን ሰዎች ወደ ዋናው ሳሎን ስናልፍ ሌሎቹ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ወደ ሌላው ሳሎን ሄዱ። ዶክተር ዐቢይና አቶ ለማ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጡ በኋላ ሌሎቻችን ሻንጣዎቻችንን ተቀብለን ደስታና ድካም የሚተራመሱበትን ሰውነት ይዘን ወደየቤታችን አቀናን። የነበረው ይህ ነው። በዚህ ጉዞ ከላይ ካየነው ፈተና በቀር የገጠመ አደጋ አላውቅም። ያየነውን እንናገራለን፤ የሰማነውንም እንመሰክራለን እንዲል መጽሐፉ።