ሰሚ የለለው ጩኸት ምን ያህል ውስጥን እንደሚያቆስል የደረሰበት ብቻ ታልሆነ ማን ይረዳዋል?።ባይወጣልኝም እስቲደክመኝ እለቀስሁ አልጋዬ ላይ በደረቴ እንደተደፋሁ በልሁን ተከፋ ጉዳት እንዲጠብቀው አምላኬን እየለመንሁና እየተማፀንሁ ቆየሁና ምናልባት ተኔ በፊት እዚህ ቤት የቤት ሰራተኛ ተነበሩት ውስጥ ምናልባት ምናልባት እክፍሉ ውስጥ የደበቁት የቤት ቁልፍ ባገኝ ብዬ ፍራሹን ፣አልጋውን፣የልብስና የጫማ ማኖሪያውን ሌሎች እክፍሉ ያሉትን አንድም ታይቀረኝ ፈለግሁ። ምንም ታላገኝ ቀረሁ። የጭንቀቴን ፍራሹ ጨበጥ ጨበጥ እያደረግሁ ትፈልግ ተፍራሹ ጠርዝ ላይ ተፍራሹ ጥጥ ጠጠር ያለ ነገር ነክቼ እጄን ቲጎረብጠኝ በጎን በኩል ክሩን ፈትቼ እጄን ወደ ውስጥ ሰደድሁ። ነገሩን ጎትቼ ታወጣው በፀጉር ሻሽ የተቋጠረ ነገር ነው ፍትቼ ታየው ተኔ በፊት የነበረች ኢልፉ የምትባል ሰራተኛ ለናቷ የጣፈችው በርከት ያለ ደብዳቤ አገኘሁ።
ምን እንደጣፈች ለማወቅ ልቤ ቢከጅልም ባለሁበት ሁኔታ ላይ ሌላ ጉድ ተጨምሮ ታለሁበት ክፍል ታልወጣ በጭንቀት ጨርቄን ጥዬ እንዳላብድ ሰጋሁ።አንዱን ጀመር ታረገው “እናቴ ምናለ ያኔ ተይ ይቅርብሽ አትሂጂ ስትይኝ በሰማሁሽ ኖሮ።ይቅር በይኝ እማማ ፀልይልኝ እናቴ ።ፀሎትሽ ረድቶኝ ተዚህ ታለሁበት ሲኦል ቤት በሂወት ተወጣሁ…”ደብዳቤውን ማንበቤን ለመቀጠል ወረቀቱን የያዘው እጄ ያኔ በልጅነቴ አብዬ ወባ ይዞት ቲንቀጠቀጥ ተነበረው በላይ እየተንዘፈዘፈ ወረቀቱን በወጉ አልይዝልሽ ትላለኝ አቋረጥሁትና ተንበርክኬ ወደ ፈጣሪዬ ጠሎት ጀመርሁ። እየጠለይሁ ተታች የሚንጋጋ ነገር የሰማሁ ትለመሰለኝ አልጋዬ ጥግ ላይ ኩርምት እንዳልሁ ድምጡን ትጠባበቅ እንቅልፍ ጣለኝ። ብንን ትል የክፍሌ በር ተከፍቷል እትዬ ክፍላቸው ስልክ ያወራሉ ድምጥ ታላሰማ ወደ ትዬ ክፍል ተጠጋሁና ጆሮዬን ደቀንሁ..”እሄውልህ ባሌ ላይ በመመስከር ለጥብቅና ስራህ ፈተና ሊሆኑ የሚችሉትን ስለባሌ ብዙ መረጃ ያላቸውን ሁለት ምስክሮች የት እንዳሉ ሻንቆ ስለደረስበት ዛሬ ለሊት አንቆ ያመጣልኛል አታስብ” አሉ ።እኔንም ወጥተው ታያንቁኝ ወደ ክፍሌ ተመለስሁና ጫማ ለብሼ ወደ በልሁ ማደሪያ ሮጥሁ።
እንደደረስሁ የበልሁ ሬድዬን በሩ ስር ወድቃ ትለፈልፍለይ በልሁ ግን እማደሪያው ውስጥ የለም።ከሩጫ በማይተናነስ እርምጃ ግቢውን እየዞርሁ ፈለኩት የለም።እምይዝ እምጨብጠው ጠፋኝ ኡ…ኡ….ኡ…እርርርርርርርርይ ብለሽ ጩሂ ሰፈር መንደሩን አቅልጭው አቅልጪው አለኝ ። ግን መጮህ ተሳነኝ። ነገሩ ጉሮሮዬ እስቲሰነጠቅ ብጮህም ተሞት ያድናቸው ይመስል የኔን ቁመት ሁለት በሚያህል ድንጋይ ተላዩ ላይ ደሞ ሽቦ በተተጫነበት አጥር ተከበው የሚኖሩት የቀየው ነዋሪዋች የኔ ጩኸት ቤት በኩል ይሰማቸዋል። ” የሽሮ ድንፋታ ፥ እንጀራ እስቲመጣ” እንዳለችው እምዬ ሰዋቹ ሳይደርሱልኝ የትዬ ዱላ እፌን ይዘጋው እንደሁ እንጂ። ይልቅስ መጮሁን ትቼ እትዬ ታይነሱ ማምለጫዬን ልፈልግ ወደ በሩ ትሄድ ቁልፍ ነው ግቢውን እይዞርሁ በመሀል ቀና ብዬ ታይ ለሊት ድምጥ ከሰማሁበት ግቢ ውስጥ አንድ ጥቁረቱ ተጥላሸትም የጠለመ ረጅም ሰውያ ተ ፎቅ ላይ በመስኮት እኔን ባይኑ ቲከተለኝ አየሁት ። እዛው በቆምሁበት ሰውነቴ በድን ሆኖ አይኔን ታልነቅል ትክ ብዬ ታየው ማታ በልሁ ላይ የሆነው ነገር ፣ እትዬ ጥዋት ሻንቆ ብለው መጣራታቸው እና የሰውየው አስተያየት የትዬ ሰው ትለመሆኑ ለመረዳት ግዜም አልፈጀብኝ። እያየሁት በድንጋጤ እቆምኩበት ሽንቴ ሊያመልጠኝ ደረሰ ወድያው በደመነፍስ ግቢውን እንደሚያጠዳ ሰው አጎንብሼ መሬት ያገኘሁትን ድንጋዩንም ወረቀቱንም እየለቃቀምሁ ቀና ታልል ደግሜም ታላየው ወደ ቤት ገባሁ….
ይቀጥላል