ቀጥታ ወደ ክፍሌ ገባሁ የሰውየው አስተያየት እና አስፈሪ ገፅታ ተፊቴ አልጠፋ አለኝ።ትናንት ያንን ምስኪን ደሀ በልሁን አስሬ እስሩ እየሄድኩ ተፖሊሶቹ ጋር ታልሄዱኩ እያልሁ ትጨቀጭቀው ሰውየው አይቶን ታይሆን አይቀርም እትዬ በልሁ ሚስጥር ያወጣ መስሏቸው የጨከኑበት። አይ እትዬ ምን አይነት ጨኳኝ ሰው ኖት በሚስኪን ደሀ ነብስ ላይ እየተጫወቱ ቤተስኪያን ቢስሙ ምን ዋጋ አለው ። “ተመቶ ሀምሳ ዳዊት ፥ የልብ ቅንነት”አለች እምዬ ፈጣሪ እንደሁ የሚያየው የልባችንን ነው።እኩለ ቀን ላይ ተክፍላቸው የወጡት እትዬ ምሳ አቅርቢ ታይሉኝ ምሳቸውን ወስደው በሉና ቡና እንዳፈላ አዘዙኝ።ቀናም ብዬ ታላያቸው ቡናውን አፈላሁ። አቦሉን ተስኒው ቀድቼ ልሰጥ ተነሳሁ ። ትኩር ብለው ፊቴን ቲመለከቱ ተሞት ጋር ፊት ለፊት የተፋጠጥሁ መሰለኝ። ቴት መጣ ታይባል ፍርሀት ወርሶኝ መላ አካላቴን ቲንጠው ስኒው ተነቡናው ተጄ ላይ አምልጦ ታልጠፋ ቦታ እግራቸው ስር ወድቆ ተከሰከሰ። ብቻ ምን ያደናብርሻል ብለው ቲጮሁ ተደናግጬ ቀና ተማለቴ ተነስተው ፊቴ ላይ በጥፊ መረጉብኝ። እትዬ ብቻ ታይሆኑ ተሰፈረባቸው ጋኔን ጋር ነው መሰል በጥፊ ያጣፉኝ ፊቴ ላይ እንደመብረቅ የጮኸው ጥፊያቸው ናላዬን አዞረው።ቤቱ ቲሽከረከርብኝ እንደምንም ሶፋ ተደግፌ ተመውደቅ ተረፍሁ። ምኑን ተረፍሁ ተጥፊው በላይ ታፈር ሚደባልቅ የሚያውቁትን ስድብ በሙሉ ምንም ታያስቀሩ እኔው ላይ ጨርሰውት ተነስተው ወጡ። እልህ ተንዴት ጋር ውስጤ ተቀጣጥሎ ተጀርባቸው ዘለሽ እነቂያቸው እነቂያቸው ቢለኝም “ፌንጣ ብትቆጣ እግሯን ጥላ ሄደች” የምትለው እምዬ ተረቷ ቲያቃጭልብኝ ተሳቸው ጋር መተናነቅ ለማለቅ ነው ብዬ ወደ ክፍሌ ገባሁ። እክፍሌ ሆኜ ምን ማረግ እንዳለብኝ ታወጣ ታወርድ ዋልሁና ዛሬ ማታ እክፍሌ ውስጥ ተጋድሜ እስቲቆሉፍብኝ ታልጠብቅ የትዬን እና የዛን ጠሎት ቤት ጉድ የማይበትን መላ ዘይጄ እስቲመሽ ቸኩዬ ትጠባበቅ መሸ።
እትዬ ወደ ምኝታ ክፍላቸው ገብተው ጋደም እንዳሉ ። ምኝታዬ ላይ ሶስት ትራስና ጨርቅ አስተኝቼ ብርድ ልብሱን ሸፈንሁትና እትዬ ትወጣ እንዳያዩኝ ተክፍሌ እንደህፃን ልጅ በዳዴ እየዳሁ ወጥቼ እላይኛው ፎቅ ላይ ታሉት ክፍሎች ቁልቁል ጠሎት ቤቱን ለማየት ምቹ የሆነውን መርጬ በመግባት ተደብቄ መጠባበቅ ጀመርሁ።
ጉደኛዋ እትዬ ልክ በትናንትናው ሰአት እኩለ ለሊት ላይ ጥቁሩን ካፖርታ ለብሰውና ጥቁሩን የሹራብ ኮፍያ እስከ ቅንድባቸው አጥልቀው ተክፍላቸው ወጡ። ቁልቁል እንዳየኻቸው የፈረደባት ልቤ እንደከበሮ ትደልቅ ጀመር ።አይዞሽ ሰንዬ ቁጭ ብለሽ በሰቀቀን ሞትሽን ተምትጠብቂ ታግለሽ የክብር ሞት መሞት ይሻልሻል በርቺ አልኩኝ ልቤን ተመዝለል ላረጋጋት ብዬ። እትዩ እንደወጡ ቀጥታ ወደ እኔ ምኝታ ክፍል ሄደው በሩን ተውጪ ቆለፉት። ተዛ ወደ ጠሎት ቤቱ አመሩ ሁለመናዬ አይን ሆኖ የሚሆነውን ለማየት ተጣደፈ። የጠሎት ቤቱን በር እስተጥግ ከፈቱት። ጠባባ የጠሌት ቤት ክፍል ተጥግ እስተ ጥግ ታየችኝ ። በሩ ላይ ቆም እንዳሉ ትንሽ አሰብ አረጉና ወድ ጀርባቸው መለስ ብለው ሳሎን ቤት ውስጥ ታሉት አሻንጉሊቶች መሀል ተለቅ ያለውን በማንሳት ተሆዱ ውስጥ ቁልፍ አወጡ። ቁልፉን ይዘው እኔ ወደተሸሸኩበት ፎቅ ደረጃውን ሽቅብ ቲወጡ ድንብርብሬ ቢወጣም ፈጠን ብዬ ተበሩ ላይ ወደ ውስጥ ገባሁና እክፍሉ ውስጥ ታለው መታጠቢያ ቤት ውስጥ ተደበቅሁ…..
ይቀጥላል