የሞት ሞቴን ይቅር ይበሉይ እትዬ ታለወትሮዬ ዛሬ የታሸገ ውሃ አምሮት ውል ቲልብይ ግዜ ነው ትለተኙ ታላስፈቅዶት የወሰድሁት አልሁና በድንጋጤ ምን እንደምሰራም ታይታወቀይ ውሃውንም አፌንም ከፈትሁና አንቆረቆርኩት።
ታሁን ታሁን እትዬ ዘለው አናቴ ላይ የሚከመሩብይ ትለመሰለይ አይኔን ታልነቅል ትመለከታቸው ..ቃል ታፋቸው ታይወጣ ፍታቸው ሞላውን እየተቀያየረ ይብስ ብሎ ደሞ ተግንባራቸው ላይ ላብ ችፍ ችፍ ማለቱን ትላየሁ ግራ ተጋባሁ። “ዋ! ሴትዬማ በጤናቸውም አይመስለኝ ብዬ አሰብሁና…እትዬ ምን ሆነዋል? እያልሁ ጠጋ ትል ..ለካ ነገሩ ወዲህ ነው። ምንድን ነው አትሉይም?
ጥዋት ቁርስ በወጉም ታይበሉ እንዲያ እየለፈለፉ በላይ በላይ የላፉት ውስኪ በፍጥነት እንደገባው ሁሉ ሆድ እቃቸውን ደበላልቆት እንዳገባቤ ታልወጣሁ ብሎ ቲተናነቃቸው ኖሯል ውሃውን ልወስድ ወደ ማድቤት ትገባ ተይተው ያየኋቸው እትዬ ትመለስ ሳሎኑ መሀል እንደንጨት ተገትረው ቲያጉረጠርጡ ያየኋቸው።
መናገር ተስኗቸው ገንፍሎ እንዳይወጣ በሁለት እጃቸው ግጥም አርገው ተያዙት አፋቸው ላይ አንድ እጃቸውን ላንድ አፍታ ለቀቅ አረጉና ወደ ላይ ሊላቸው እንደሆነ በምልክት ነግረውኝ መልሰው በፍጥነት አፋቸውን ቲይዙ…
በውስጤ ታስር ግዜ በላይ..ተመስገን ፈጣሪዬ፣ ተባረክ የድሀ አምላክ፣ተመሰገን የጭንቅ አምላክ ….እያልሁ ሮጬ ማስታጠቢያ አመጣሁና አፋቸው ስር ደቀንሁት። ተወገብ በላይ እየተናጡ ጣጣቸውን እንደጨረሱ የጠጡት ውስኪ አተት ነው ኮተት እንደሚሉት በሽታ ተላይም ተታችም ነው መሰል ያጣደፋቸው። ሆዳቸውን ደግፈው እንዳቀረቀሩ ሽንት ቤት ሽንት ቤት አድርሽኝ አሉና ደገፍ አሉብኝ።
ወይ ፈጣሪ ላንተ ምን ይሳንሃል ተሰላሳ ደቂቃ በፊት ልክ ልኬን አረ ተልኬም በላይ ቲነግሩይ ቲሰድቡይ የነበሩ ሴትዬ እንዲህ ልካቸውን ትላሳየኽልይ ተመስገን። ለጦሎት ቤቱ ጀርባችንን እንደሰጠን ወደ ሽንት ቤት አስገባኻቸው ተመጣደፋቸው የተነሳ በሩን ተውስጥ ታይዘጉ ትለተቀመጡ …እትዬ ቲጨርሱ ይጥሩይ አይዞት።አልሁና በሩን ተውጪ ዘጋሁባቸው።
ወንድሜ በልሁ ውሃ ውሃ እያለ ታላጠጣው ተምቀር ሞቴን አልሁና የተረፈችኝን ውሃ ይዤ ወደ በልሁ በረርሁ።ቁልቁል ትወርድ የትዬ ጌታ እያ ዘንዶ እንቅልፋቸውን ጨርሰው ይገላበጣሉ። በልሁ አጠገብ እንደደረስሁ ሰርቄ ዘንዶውን እየተመለከትሁ ከፉሉን ውሃ እበልሁ አፍ ውስጥ ከፊሉን ደሞ ታፉ ውጪ እየደፋሁ አጠጣሁት። ጉድ ሆየልህ ነበር በልሁ እትዬ ተተኙበት ተነሱ ትለው ቅድም እንዲያ አጠገቡ ቆሜ ትወተውተው ታለቅስ አይኑን እንደጨፈነ ዝም ያለው በልሁ አሁን እትዬ ተነሱብይ ትለው አይኑን ገልጦ ውይ እህቴን የሚል በሚመስል ሀዘን በተሞላበት እይታ ቲመለከተይ እንባዬ እርግፍ አለ።በዚህ መሀል በሩ በሀይል እየተመታ ሰናይት የሚል ድምጥ ከላይ ትለተሰማይ ሽቅብ ሮጥሁና የጠሎት ቤቱን የወለል በር ዘግቼ ምንጣፉን እንደነበረው አስታስተካክል እትዬ ቢጣሩም እንዳልሰማሁ ሆንሁ። እንደጨረስሁ ወደ ሽንት ቤት በመሄድ አቤት እትዬ ጠሩይ እንዴ አልሁና በሩን ትከፍት …እትዬ ባንድ ግዜ ወደ ነባሩ ማንነታቸው ወደ አውሬነታቸው ተቀይረው ተውጪ ዘግተሽብይ ለምን ጠፋሽ ብለው ለጉድ ቲወርዱብይ.. እኔ ግን በልሁ ተበላልይ ብዬ በሰሀን አጥቅሼ የወሰድኩትን ምግብ እዛው በልሁ ጋር ረስቼው መምጣቴን ትላስታወስኩ ተጉድ አውጥቶ ፈጣሪ የሰጠይን እድል ታልጠቀም የኔንም የሱንም ሞት ያፈጠንሁት መስሎ ተሰማይ እሳቸው ቲሳደቡ አካሌ ተፊታቸው ቢቆምም እኔ ግን አልነበርሁም….
ይቀጥላል