አዳምን ልነካው ስለ ደፈርኩ ይቅርታ እጠይቃለው። ይቅርታ ጠይቄ ግን እፅፋለው። ((የማፈንገጥ አንድ ገፅ የአዳምም መልክ ነው።))
ግራጫ ፀጉር አለው። ትከሻው ሰፊ ነው። አይኖቹ መነፀር ይለብሳሉ። እጆቹ ለስላሳ ናቸው። ጣቶቹ ሲጋራ ይይዛሉ። እሱን ሳይ ሲጋራ አጢስ ብሎኝ ያውቃል።
ብሄራዊ ሰፈር የምከርም ስለሆንኩኝ አዳምን በአመት ውስጥ አንዴ ሳላገኘው ቀርቼ አላውቅም። አዳም እንዴት ነህ ብዬ ብዙ ጊዜ ከትኩረቱ አናጥቤዋለው። ጥርሱን ትንሽ ፈገግ አድርጎ ሰላም ይለኛል። መዐዛ ቡና ከስኒዎቹ ቡና ሲጠጣ፣ ራስ ሆቴል ደጃፍ ሲራመድ አታጡትም። ካሳንችስም እግር እንደሚያበዛ ሰምቼአለው። ((አለማየሁ ገላጋይ ቤት ዙሪያ። ወዳጅ ናቸው። እኩያ ወዳጆች።))
አዳም ረታን ሳስበው ይደክመኛል። አካሌን ያዝለዋል፣ ነብሴን ያደክመዋል። ልሸከመው አልችልም፣ ቆሜ ስለ እርሱ መናገር ያስፈራኛል። በርከክ ብዬ ባወራ እመርጣለው። እንደ ሰማይ የራቀ፣ ከአድማስም ባሻገር የደረሰ ነውና። (ከአድማስ ባሻገር መድረሻ አለው እንዴ?))
ለኢትዮጵያ ስነፅሁፍ ንጉሰ ነገስት ነው ተብሎ ለሚታመነው አዳም ረታ “ብዙዎች እልልታ” ሲያበዙ ይሰማኛል። ይኽ እልልታ ከማወቅ፣ እሱን ከመረዳት፣ ፅሁፎቹን አገናዝቦ ከመረዳት የመጣ ነው ወይንስ አዳምን አላነብም፣ አላደንቅም ማለት ወፈፌ ያስብል ይሆን ወይ ብዬ እፈራለው!?
እንጀራ፣ ሕፅናዊነትን፣ ሰአሊ ደራሲነቱን ((ጥልቅ ገለፃውን በማሰብ ነው ሰአሊ ማለቴ።)) በቃላት የሚስል ፀሀፊነቱን ለማስታወስ፣ በድህረ ዘመናዊነት ውስጥ የሚንፈላሰሰውን ስብእናውን፣ ጥልቅ ንባቡን (የህዳግ ማጣቀሻዎቹን ማየት በቂ ነው)፣ የምናብ አድማሱን ስፋት፣ የበይነ ዲስፕሊን ሀልዬትን በተግባር ስለሚገልፅ አዳምን መንካት ያስፈራኛል።
አዳም በአማርኛ መምህሩ አንደበት፡-
አዳም በምናብ፣ በስሜቱ አንዴ ልጅ፣ ሌላም ጊዜ ወጣት፣ ሲያሻውም ቢሸመግልም የ60 አመት ጎልማሳ ነው። ((1950 ነው የተወለደው))። የረታ ልጅ በልጅነት ራዲዮ አድምጥ፣ ጋዜጣ አንብብ የተባለ ነው። እሱ ግን እግር ካስ የሚወድ እግረኛ ነበር። በትምህርት ቤት በራዲዮ የሰማውን፣ ከጋዜጣ ያነበበውን ለክፍል ተማሪዎች ያቀርብ ነበር። ይኽ ድግግሞሽ የቤት ስራ ግን ያሰለቸው ነበር። bored provokes new spirits.
እናም አዳም የጋዜጦቹን እና የራዲዮኑን ጭማቂ ወሬዎች አሽቀንጥሮ ጥሎ በመንገድ ያየውን “ዶሮዎች ከቅርጫት አምልጠው ዶሮ ነጋዴዎቹ ነፃነቴን ያሉትን ዶሮዎች ለመያዝ የሚያደርጉትን ርኩቻ ፅፎ አነበበ።” መምህሩም ከታዘዘው ይልቅ ያልታዘዘውን ለፃፈው ልጅ ምስክር ሆኑ። ((አፈንጋጭነት አንድ)) አዳም ደራሲ ይሆናል ብለው በእኩዬቹ ፊት ተናገሩ። እሱ አልበረደው፤ አልሞቀውም። ((አሁንም እኮ ምንም ብትለው አይሞቀውም።))
አርአያ የለውም፡-
ግጥም እንደ ነብስ ቢወድም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በወመዘክር የመፅሀፍ መደርደሪያዎች ላይ ያሉትን ቢሰለቅጥም። የባህር ማዶ ፀሀፊዎችን እይታ በተለይም ደግሞ ተረት፣ ሳይንስ ፊክሽን እና ፋንታሲ ፅሁፎችን ቢያነብም “እከሌ፣ እንቶኔ” የተባለ ፀሀፊ ለፀኀፊነት እንድነሸጥ አድርጎኛል አይልም። ተረት፣ ሳይንስ ፊክሽን እና ፋንታሲ የሆኑት የፅሁፍ አይነቶች የወደደበት ምክንያት በድግግሞሽ አድካሚ ከሆነው ኑሮ ስለሚያፋቱት ይመስለኛል። ከአለም ነጥቀው ሩቅ ይወስዱታላ። ((አፈንጋጭነትን ሁለት))
የስነ መልክአ ምድር ትምህርት እና ስራ፡-
በካርታዎች ስራ ድርጀት ለ8/ 9 አመታት የቢሮ ሰራተኛ ነበር። በነዚህ የሲቪል ቅጥረኝነቱ ብዙ ማንበቢያ ጊዜ አግኝታል። እጅጉን ጥልቅ አንባቢነቱም እጁን እንዲያነሳ ((እጅ ማንሳት ለብዕር እንደሆነ ይሰመርልኝ።)) ብዕሩንም እንዲሲል፣ እንዲፅፍ ከልጅነት ጊዜ ተረቶች ወደ አዋቂነት ፅሁፎች/ ፀሀፊነት ገፍተውታል።
የጂኦግራፊ ተማሪነቱ እና ሰራተኝነቱ አንድ መልካም ነገር እንዳዋሱት ይሰማኛል። የስነ መልክአ ምድር ትምህርት ሀሳቦች/ ሀልዮቶች/ ሀቲቶች) ከሂሳብ፣ ከፊዚክስ የጥናት ዘሮች ይዋሳል። ስነ መልክአ ምድር ሆደ ሰፊ የሆነ የሙያ ዘርፍ መሆኑን ሌሎችን መስኮች በመቀበል ያሳያል። አዳምም ከዚህ የጥናት ዘርፍ እና ባለሙያነት “የበይነ ዲሲፕሊን” አስተምህሮን እንደቀሰመ ይሰማኛል። ማንም ብቻውን ይቆም ዘንድ ልክ አይደለም። ደጋፊ፣ ረዳት፣ አጋዥ እንደሚያስፈልገው በእውኑ አወቀ። ((በቀደመው ዘመን የድህረ ዘመናዊነት ሀሳብን ቢረዳም።))
የአዳም እንጀራ፡-
ከማህሌት ጀምሮ እስከ አፍ ድረስ አዳም ብዙ ነገሮችን ሞክራል። በሀሳብ፣ በታሪክ ግንባታ፣ በምናብ አፅናፍ (ወደፊትም፤ ወደኃላም ዘመን) በስነፅሁፍ ዘርፎች በአጭር ታሪኮች፣ በኖቬላዎች፣ በረጅም ልብወለድ (ለእኔ የአዳም ረጅም ልብ ወለድን አባይ ልብ ወለድ ነው የምለው።] ወንድሜ፣ እህቴ ለአንድ ሺ ገፅ የተማረከ ነው። የስንብት ቀለማትን ብዙ አመት ነው የፃፈው። ስለዚህ መፀሀፍ ከአስር አመት በፊት ጀምሮ ሲናገርበት ነበርና!]
ለኢትዮጵያዊው ስርወ ሀገር ውስጥ እንጀራ እኩያ ነው። ይኽን ውብ የሐገር “ሰንደቅ” ስንቱ ሲያናንቀው፣ ሲያጣጥለው እሱ ግን ለፅሁፉ ውክልና አደረገው። የጤፍ ዘር ደቃቅነትን አልናቀም። ያ ደቃቃ ዘር ተዘርቶ በመልካሙ መስክ ሲዘራ እልፍ ይሆናል። ተፈጭቶም፣ ተጋግሮም አይን ያለው ይሆናል። በክብነት ውስጥ ባለ ብዙ አይን ያለው እንጀራም ይፈጠራል። Semiotic representation. የእንጀራ መነሻውና መድረሻው በክብነት ውስጥ አያስታውቅም። ይኸንን ውክልና ለታሪክ ግንባታው፣ ለአዳም የስነፅሁፍ ዛር ውቃቢው ሆነ።
ምናብና አዳም፡-
በ 34 አመት የፀሀፊነት የአደባባይ ህይወት ውስጥ። ከማህሌት እስከ አፍ ድረስ ያሉትን ታሪኮች “በፍፁም” ህሊናህ ካልሆንክ በምን መስመር፣ በምን ሀሳብ፣ በምን መቼት እንዳገናኛቸው ግራ ሊገባህ ይችላል። አንዳንዴም ምንድን ነው የሚፅፈው አይገባም ልትል ትችላለህ። ((ይኽን ነገር ኩራዝ አሳታሚ ውስጥ የነበሩ ሰዎችም ይሉት ነበር። ባለ መቀሶች ሳንሱራሞች]
ምናብ ለአዳም የበኩር ልጁ ነው። በምናብ አማካኝነት ወደ ኋላ ተጉዘህ፣ ወደ ፊት ቀድመህ ተራምዶ ታሪክን፣ ሀልዩትን፣ ሂስን እና ሌሎች የሰውነት እና የአለምን ስራ ማስተሳሰር ይችልበታል። ይህን ንስር አይናማነቱ፣ ልሂቅነቱን ማሳያ መልክ ነው። አዳምም ፅሁፍ አላቂ አይደለም። አላቂነት የፀሀፊው ምናብ ነው። ትልቅ ምናብ ያለው ፀሀፊ አለቀ የተባለን ታሪክ አንስቶ ነብስ ዘርቶ ይቀሰቅሰውና ህያው ያደርገዋል ይላል። የአዳም ረታ የምናብ ከሀሊነትን በዚህ ታላቅ እሳቦቱ ውስጥ ገብተን መቅመስ አለብን።
አዳም የምናብ ሀያልነቱን በሁሉት ነገር ማስተዋል እንችላለን። አንደኛው በሕፅናዊነት ስራው ውስጥ በአንዱ መፅሀፍ ውስጥ ልጅ ሁና ጭቃ ስታቦካ የነበረችው ልጅን፣ በሌላኛው መፅሀፉ ከሞት ብኌላ በሰማይ መንገድ ላይ ነብሳን ሊያናግራት ይችላል። አሳድጎ፣ አበልፅጎ ያሳያሀል። እንደ ሰው ልጅ መወለድ፣ ማደግ፣ መሞት በሚለው ግቢ ሳይወሰን። ከአድማሱ ወዲያ ይወስደዋል። የአዳም ምናብ፣ የራሱን አለም ሰርቶ ሁለተኛ ፈጣሪነቱን ያሳያሀል።
ዘነበወርቅ አድጎ በባህር ማዶ የእድሜውን እኩሌታ ያሳለፈው አዳም አንድን ጉዳይ እጅግ ጥልቅ በሆነ መንገድ ይገልፅልሀል። ለምሳሌ የመርፌዋን አይን አስመልክቶ ብዙ ገፅ ሊፅፍ ይችላል። ይኽ ገላጭነት የምናቡ አስካልን ማሳያ ነው። አንባቢው አንድን ጉዳይ እንደ ሽንኩርቱ ድርብርብ ገላ እየገሸለጠ ያሳይሀል። ተገርመህ ታነበዋለህ።
የምናብ አስተምህሮው ይቀጥላል። የሚያልቅ ታሪክ የለም ለሚለው አዳም ረታ። በመፅሀፎቹ ውስጥ አንዳንዴ ታሪኮች በእንጥልጥል ይቀራሉ። እነዚህ በእንጥልጥል የቀሩ ታሪኮችን አንባቢው በምናቡ መሙላት ይችላል ይላል። ግድ ፀሀፊው ሁሉን መንገድ ይዞ መጋዝ የለበትም ባይ ነው። አንባቢው ባለው መረዳት (እውቀት እና ምናብ) ታሪኩን መቋጨት ይችላል። the golden thought of open ended rules.
ሕፅናዊነት እና በይነ ዲስፒሊን
አንድ ታሪክ ከሌላው ታሪክ፣ አንድን ሙያ ከሌላው ሙያ ጋር፣ አንድን መፅሀፍ ከሌላው መፅሀፍ ጋር ማስተሳሰር ይቻላል። ብቻውን የቆመ ሀልዮት የለም። አዳምም ይኽንን Interdisciplinary and Multiplicity ምግባር በስራዎቹ ማወቅ ያስፈልጋል። ሀሳቡን፣ የአፃፃፍ ቅርፁን፣ ሙዚቃዎቹን፣ ካርታዎቹን፣ በመፅሀፋ ውስጥ ያለውን ቀለሞች በአንድ አገናኝተህ ተንትነህ ካላነበብክ አዳምን እፍታውን ብቻ ነው የምታውቀው።
ከተለምዶዋዊ የአተራረክ መንገድ አፈንግጦ፣ በደህረ ዘመናዊነት ዙፋኑን ለወረሰው አዳም በነጠላ እውቀቶች መረዳት አዳጋች ነው። በድርብ፣ ድርብርብ የእውቀት ጋቢዎች ውስጥ መመዘን ይገባል።
የመጨረሻ መጀመሪያ፡-
አዳም በወሰደው ባመጣው መንገድ፣ እቴ ሜቴ ሎሚ ሽታን ዘምረናል። ከሰማይ የወረደው ፍርፍር መረቅ በዝቶበት፣ ምስር ፈልገን በአለንጋ አስገርፎናል። በግራጫ ቃጭሎች ተደመን ማህሌት አቅርበናል። ለፍቅሩ ህማማት በገና ደርድረናል። ኦ አዳም ብለንም ለስንብት ቀለማት ተንበርክከናል።
እናም:-
ፐ እና ኦ የተባሉት ቃላት አይዘይሩትም። አዳም የሚለው ሀያል ስም ራሱ የበይነ ዲሲፕሊን ደረጃ ነው።