Tidarfelagi.com

ኦነግና ኢህአዴግ በአንድ ቀን ጦርነት (ክፍል አራት)

(እውነተኛ ታሪክ)

ረቡዕ ሰኔ 17/1984…. ከጧቱ 12፡30 ገደማ

አክስቴ ከሁላችንም ቀድማ ነው ከእንቅልፏ የተነሳችው። እኔና ልጆቿ ከመኝታችን በመነሳት ላይ በነበርንበት ጊዜ ደግሞ እርሷ ወደ ሰፈር ሄዳ ወሬ ቃርማ መመለሷ ነው። “ምን ተፈጠረ?” አልናት።
“ኢህአዴጎች ሳይጠበቁ በኦነግ ጦር ላይ ጥቃት ከፍተዋል?”
“መቼ ነው ውጊያው የተጀመረው?…”
“ከሌሊቱ አስር ሰዓት ገደማ ነው አሉ”
“በየት በኩል ነው የመጡት?”
“እኔ እንጃ! ውጊያው ግን በጋራ ጉራቻ ነው የተጀመረው”
“አሁን የቱ ጋ ደርሰዋል?”
“ኦነጎች እያፈገፈጉ ወደ ሰፈር ገብተዋል አሉ፤ ኢህአዴጎቹ ከጋራው ላይ ሙሉ በሙሉ ያስለቀቋቸው ይመስላል”

ከአክስቴ ጋር እንዲህ ስንባባል እንኳ ከርቀት የሚመጣ የተኩስ ድምጽ ይሰማል። ከአክስቴ ልጆች ጋር “ምን እናድርግ” እያልን ስንጠያየቅ አክስቴ “ወደዚህ ስለማይመጡ እዚሁ ቆዩ” አለችን። እኛም በዚሁ ተስማማን።

ይሁን እንጂ ከውጪ የሚሰማው ሁካታና ግርግር ሊያስቀምጠን አልቻለም። በመሆኑም የሁካታውን ምክንያት ማጣራት አለብን በሚል ሰበብ ከቤቱ ወጣን (በቤቱ ውስጥ የነበሩት የአክስቴ ልጆች አራት ናቸው- ሶስት ወንድና አንዲት ሴት፤ “ሙበጀል” የሚባለው ትልቁ ልጇ ደግሞ ከርሷ ቤት ጀርባ ባለ ስፍራ ላይ በተሰራው የራሱ ቤት ውስጥ ነበር። ከትንሽ ጊዜ በኋላ ግን እርሱም መጥቶ ተቀላቀለን)።
*****
የአክስቴ ቤት በሰፈሩ ደቡብ ምዕራብ ክንፍ የመጨረሻ ጥግ ላይ ነው የተሰራው። ቤቱ የሳር ክዳን የለበሰ ሆኖ ውስጡ በጣም ሰፊ ነው። ግድግዳው በቀይ አፈር የተመረገ ሲሆን ከላዩ “በራሳ” በሚባል ቢጫ ቀለም ባለው አፈር ተለቅልቋል። ምርጊቱም በጣም ወፍራም ነው። በግድግዳው አንዳንድ ስፍራዎች ላይ ለጭስ መውጫ ተብለው የተተው ጥቂት ቀዳዳዎች አሉ። ቤቱ በሁለት በኩል የመግቢያ በር አለው። ዋናው በር ወደ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ የሚያስወጣው ሲሆን ሁለተኛው በር በሰሜን ምዕራብ በኩል ወደ ውጪ ያስወጣል። በዚህ በር ትይዩ ደግሞ የአክስቴ ልጅ (የሙበጀል) ቤት ይገኛል።

የአክስቴ ቤት በደቡብ፣ በምዕራብና በሰሜን በኩል አጥር የነበረው ሲሆን በምስራቅ አቅጣጫ ግን ምንም ከለላ አልነበረውም። ይህ የአክስቴ ቤትና የልጇ ቤት በግቢው ምስራቃዊ ጥግ ላይ ነው የተቀለሱት። ከቤቶቹ በስተሰሜን በኩል ከብቶች የሚያድሩበት ስፍራ አለ። በስተደቡብና በስተምዕራብ በኩል ያለው የግቢው ክፍል ግን በሳር ተሸፍኗል። በግቢው ደቡብ ምዕራባዊ ማዕዘን (corner) ላይ አንድ የአንጎራ (በኦሮምኛ ስሙ “ጂልቦ”) ይገኝበት ነበር።

የሰፈሩ መስጊድና የአክስቴ ቤት በአጥር ብቻ ነው የሚለያዩት። መስጊዱ ከቤቱ ዝቅ ባለ ስፍራ ላይ ነው የሚገኘው። በሁለቱ መካከል የሰፈሩ ሰው ወደ ወንዝና ወደ እርሻው የሚወርድበት ጠባብ ጎዳና አለ። በዚህ ጎዳና ላይ አስር ሜትር ስንሄድ ደግሞ “ረውዳ” ከሚባል ሰፊ ሜዳ እንደርሳለን። ይህ “ረውዳ” የሚባለው ስፍራ የሰፈሩ ከብቶች ለግጦሽ የሚሰማሩበት በመሆኑ አይታረስም።

ስለቤቱና ስለአካባቢው እንዲህ የምጽፈው ለቀጣዩ ትረካችን ስለሚጠቅመን ነው። በስፍራው የተፈጠረውን ነገር ቀስ እያላችሁ ትደርሱበታላችሁ።
*****
ከላይ እንደገለጽኩት በቤቱ የነበርነው ልጆች ውጪውን ለማየት በሚል ከቤቱ ወጥተናል። ይሁንና እኛ በወጣንበት ጊዜ ከቤቱ በታች በሚያልፈው ጠባብ ጎዳና ላይ በሰልፍ የሚጓዙ የኦነግ ወታደሮችን አየን። ነገሩ ድንጋጤ ስለፈጠረብን ወደፊት መጓዙን ትተን በቤቱ ግድግዳ ላይ በመለጠፍ በመንገዱ የሚያልፉትን ኦነጎች ማየት ጀመርን። ታዲያ ከነዚያ ወታደሮች መካከል “ግርኖቭ” የሚባለውን መትረየስ በትከሻው ላይ የተሸከመ ረዥም ልጅ ድምጹን ከፍ አድርጎ “Sheeka! Sheeka! Asitti battala qabanna moo ol dachaana?” ሲል ሰማነው። “ሼኹ… ሼኹ..!እዚሁ ቦታ እንያዝ ወይንስ ወደላይ እንመለስ” ማለቱ ነው። ወታደሩ ወደ ተጣራበት አቅጣጫ ስንመለከት “ረውዳ” በሚባለው መስክ መግቢያ ላይ ሌሎች ወታደሮች አድፍጠው ሲጠባበቁ ተመለከትናቸው።

ባለመትረሱ ወታደር “ሼካ…ሼካ..” ብሎ የጠራው ሰውዬ በትክክለኛ ስሙ “ሼኽ ፊኒንሳ” ይባላል። በዚያ ወቅት በኦነግ ውስጥ በ“ሼኽ” ማዕረግ ከሚጠሩት ሶስት ሰዎች አንዱ ነው። (አንደኛው ሰውዬ “ሼኽ ጠሊሌሳ“ ይባላል። ከሰኔ 1983 እስከ ጥር 1984 በገለምሶ ለነበረው የኦነግ የዞን ኮሚቴ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ ነበር። በጥር ወር 1984 ግን ከዱጋሳ በከኮ ጋር ወደ ደደር ተቀይሯል። እርሱ ከሄደ በኋላ ደግሞ “ሼኽ ቢቂልቻ” እየተባለ በሼኽ ማዕረግ የሚጠራ ሌላ ሰው መጣ። ይህ “ሼኽ ቢቂልቻ” የፕሮፓጋንዳ ሃላፊ ሆኖ የተሰየመ ይመስለኛል)።

ሼኽ ፊኒንሳ የሻምበል አዛዥ ነበር (“ሻምበል” በኦነግ አሰራር መሰረት “አባ ቡትታ” ተብሎ ነው የሚጠራው)። ልጁ ለጠየቀው ጥያቄ የሰጠውን መልስ በትክክል ባልሰማውም “እዚሁ እንቆያለን” ያለው ይመስለኛል። ይህንን ተከትሎ ግን ያልታሰበ ነገር ተከሰተ። አክስቴ ቁና ቁና እየተነፈሰች “ቡራቡሬ ለባሾቹ በላይ በኩል መጥተዋል! ቶሎ ወደቤት ግቡ” አለችን። እኛም በድንጋጤ ወደውስጥ ዘለቅን። ታዲያ ገና ከመግባታችን የአክስቴ ግቢ ተቀወጠ። የገባንበት ቤት ዙሪያ ተኩስ… ተኩስ በሆነ።

“ክላሽ” ሙዚቃ በሚመስለው እሩምታው ተንቦቀቦቀ። ግርኖቭ መትረየሶችና ካሊበሮች ተንፈቀፈቁ። “ኤም-14” በተለመደው ድምጹ “ዱም ዷ… ዱም ዷ” እያለ አስገረገረ። “ፋል” የተባለው መሳሪያ ጠንከር ባለ ድምጹ እንደ ብራቅ ጮኸ። ከወዲያም ከወዲህም እሳት ተተፋ። የተቃጠለ ጎማ የሚመስል የባሩድ ሽታ ወደቤቱ እየገባ አፍንጫችንን ሰነፈጠው። ጆሮዎቻችን በተኩሱ ድምጸት ሊበሱ ደረሱ። መሬት ቀውጢ ሆነች።

በልጅ ወኔዬ ያንን ረባሽ ትርዒት መስማት ዘገነነኝ። ሆዴ ከዚያ ወዲህ አይቼው በማላውቀው የሽብር ስሜት ተላወሰ። አዕምሮዬ በጭንቀት ተወጠረ። በተለይም ቤቱ የሳር ክዳን የለበሰ መሆኑ ሲታወሰኝ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ የምሞት እየመሰለኝ በፍርሃት ተብረከረክኩ። ከአሁን አሁን “ጥይትና ቦንብ በጣሪያው ላይ ወድቆ ሁላችንንም ይፈጀን ይሆናል” እያልኩ ተሸበርኩ። ቢቸግረኝ ከድምጹ ልገላገል በማለት ጆሮዎቼን ያዝኩ። ከአምስት ደቂቃ በኋላ እጆቼን ከጆሮዎቼ ላይ ሳላቅቅ ግን የረባሹ ድምጽ ግዝፈት ከበፊቱ ብሶ አገኘሁት። “ያ አላህ! የዛሬን ብቻ በሰላም አውጣን” አልኩ!!!

ሁላችንም ከቤቱ ወለል ላይ ነበር የተኛነው። እኔ የነበርኩበት ደግሞ ከቤቱ ዋነኛ ክፍል ወደ ጓዳ የሚያስገባው በር ካለበት ስፍራ ነው። ታዲያ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለን አንዲት ጥይት አክስቴ እንጀራ ከምትጋግርበት ቦታ ከፍ ብሎ ያለውን የጭስ መውጫ ቀዳዳ የታችኛውን አፍ በጥርቃ ወደቤቱ ገባች። ሁላችንም ደንግጠን መሬት ለመሬት በመንፏቀቅ ከቤቱ ዋነኛ ክፍል ውስጥ ተሰባሰብን።

በዚያች ጊዜ ውስጥ መሬት ላይ ያልተኛችው አክስቴ ብቻ ነበረች። በቤቱ ዋነኛ በር ቀዳዳ ወደ ውጪ እያየች “ወይኔ ከብቶቼ! አለቁብኝ እኮ?!! ለነርሱስ ማን ነው የሚያዝነው! እነርሱ የት ይደበቁ እስቲ!! ወይ በሃኢም! እነርሱም እንደኛ ነፍስ አላቸው አይደለም እንዴ? እነዚህ ባለጠመንዣዎች የአላህ ፍጥረት አያሳዝናቸውም” ትል ነበር። “እባክሽ መሬት ላይ ተኚ” ብለን ስንለምናት “እሺ” ትልና ወደኛ ትመጣለች። እንደገና ደግሞ “ከብቶቼ!” ትልና ወደ በሩ ትሄዳለች። “እባክሽ! አክስቴ! ቅድሚያ ለነፍስ ነው!! እባክሽን ተኚ” ብዬ ስለምናት “እሺ” ብላ ትተኛለች። እንደገና ትነሳና “ከብቶቼ” ትላለች። አክስቴን በፍጹም ማስተኛት አልቻልንም።

ከውጪ የሚንፈቀፈቀው የተኩስ ድምጽ እንደቀጠለ ነው። የሰዎች ንግግርና ሁካታም ቀጥሏል። “ግደፉ! ግደፉ! እስመአንዶ… ማንጁስ… ንሽተይ… ….ቁሩብ..ቁሩብ…” የሚሉ ቃላት ይሰሙኛል። ሰዎቹ የሚሉትን ለመረዳት ቢከብደኝም ኢህአዴጎች መሆናቸውን አውቀናል። አክስቴ “ቡራቡሬ ለባሾች” ያለቻቸው እነርሱን ነው።

በግምት ከጧቱ አንድ ሰዓት ተኩል ሲሆን ተኩሱ መቀነስ ጀመረ። የሰዎች ንግግርና የሁካታ ድምጽም ራቅ እያለ ሄደ። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ በዚያ አካባቢ የሚተኮሰው ነገር በሙሉ ጸጥ ረጭ አለ። በምትኩ “Akkana Leenca Oromoo! Nuti ilmaan Oromoo eenyu nu seete” የሚል የፉከራ ድምጽ ቀስ እያለ መሰማት ጀመረ። ይህም ድምጽ እየቀረበ መጥቶ በቤቱ ጀርባ አለፈ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እርሱም እንደ መጀመሪያው ድምጽ ጠፋ።

በኦሮምኛ የሚፎክሩት የኦነግ ወታደሮች መሆናቸውንም አውቀናል። ኢህአዴጎቹን ገፍተው ወደ ኋላ እየመለሷቸው እንደነበርም ተረድተናል። በመሆኑም በአካባቢው ሰላም የሰፈነ ስለመሰለን ከቤት መውጣት ጀመርን። ታዲያ በቤቱ የጓሮ በር ወጥቼ ወደ ታች (ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ) ሳይ በርቀት ክላሽ ይዞ ከቆመ የኦነግ ወታደር ጋር ዐይን ለዐይን ተጋጨን። ወታደሩ እኔን ሲያይ በቅጽበት አንድ እግሩን ወደ ኋላ በርከክ አደረገ። ከዚያም መሳሪያውን ወደኔ አዙሮ “Eenyu Aboo?” (ማን ነህ አንተ?) በማለት ጠየቀኝ። እኔም ድምጼን ከፍ አድርጌ “Warra Biyyaati” (የሀገሬው ሰው ነኝ) የሚል መልስ ሰጠሁት። ወታደሩም “Ol deebi’aa gara manaa” (ወደቤት ተመለሱ) የሚል ትዕዛዝ ሰጠኝ። እኔም እሺታዬን ገልጬ ወደቤቱ ገባሁ።
*****

(ይቀጥላል)

መስከረም 14/2007
—–

ኦነግና ኢህአዴግ በአንድ ቀን ጦርነት (ክፍል አምስት)

 

Afendi Muteki is a researcher and author of the ethnography and history of the peoples of East Ethiopia

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...