ኦሮማይ ከልቡ መጽሐፍ ነው። በአማርኛ ልብ-ወለድ መጻሕፍት (Novel) ታሪክ በጣም አነጋጋሪውና አከራካሪው መጽሐፍ ነው። እስከ አሁን ድረስ የህዝብ ፍቅር ካልተነፈጋቸው ጥቂት መጻሕፍት አንዱም ነው። በህይወቴ ብዙ ጊዜ እየደጋገምኩ ካነበብኳቸው መጻሕፍት መካከልም በመጀመሪያው ረድፍ ይሰለፋል። ይሁንና ሰዎች ለዚህ መጽሐፍ ያላቸው አድናቆት እንደየ አመለካከታቸው ይለያያል።
መጽሐፉ የብዙዎቹን አትኩሮት የሳበው ታሪኩ እውነት ነው ስለተባለ እና በመጽሐፉ ሳቢያም የደራሲው ህይወት ለአደጋ በመጋለጡ ይመስለኛል። ከመጽሐፉ ዐቢይ ገጸ-ባህሪያት አንዱ የሆኑት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ “የደም እምባ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ተመሳሳይ እይታ አንጸባርቀዋል፤ እንደ ሻለቃ ዳዊት አባባል ኦሮማይ ባይታገድ ኖሮ ተወዳጅነቱ ይሄን ያህል አይገዝፍ ነበር። ሆኖም እኔ በዚህ አባባል አልስማማም። ደራሲው ባይሞት እና ታሪኩ እውነተኛ ባይሆን እንኳ “ኦሮማይ” ተደናቂ የመሆንን እድል አያጣም ነበር ብዬ አምናለሁ። ለዚህም በርካታ አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል።
“ኦሮማይ” በቅድሚያ ቀልብን የሚስበው በአጻጻፍ ብሂሉ ነው። ደራሲው ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው አጫጭር ዐረፍተ ነገሮችን ይጠቀማል። ይህም አንባቢው የመጽሐፉን የትረካ ቅደም ተከተል ሳይስት ድርሰቱን ያለድካም እንዲያጣጥም ያግዘዋል። ደራሲው ጠጣር ሃሳቦችን በቀላሉ ይዘረዝራል። የዘመኑ መንግሥት አሰራርን ለተደራሲው በሚገባው ቋንቋ ቀለል አድርጎ ያስረዳዋል። በሌላ በኩል መጽሐፉ ኪናዊ ውበቱን እንዳይስት ደራሲው በእጅጉ ተጠቧል። ዘይቤአዊ አባባሎችን ከዘመኑ የአነጋገር ፋሽን ጋር እየቀላቀለ አንባቢውን ያዝናናዋል። በተለይም “ኦሮማይ” ፈጠራ እየነጠፈ በዘመቻ ግርግር እና በንድፈ-ሓሳብ ዝብዘባ የሚፈበረኩ ቃላት የድርሰቱን ጎራ እያጠለሹ በመጡበት ዘመን አንባቢው በማይሰለቸው የቋንቋ ጥበብ የተጻፈ በመሆኑ የደራሲውን ልዩ ተሰጥኦ በጉልህ ያስረዳል። ሆኖም ኦሮማይ የዚያ ዘመን ድርሰት ብቻ አይደለም። በዚህ ዘመንም እንኳ ተደግመው ሊጻፉ ከማይችሉ ድርሰቶች መካከል ሊመደብ ይችላል።
ይበልጥ አስደናቂው ነገር ደግሞ ወዲህ ነው። ደራሲው ያንን ውብ መጽሐፍ የጻፈው በጥቂት ወራት ውስጥ ነው። ይገርማል! ሰውዬው በወቅቱ ምክትል የማስታወቂያ ሚኒስትር ነበር (በደንበኛ ስሙ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ ይባል ነበረ)። የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሆኖም ይሰራ ነበር። በአዲስ ዘመን እና በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጦች ዝግጅትም ይሳተፋል፤ ዝግጅታቸውን በበላይነት ይቆጣጠራል። ቱባ ባለስልጣን በመሆኑ የብዙ ኮሚቴዎች አባል መሆኑም ይታመናል። በርካታ የቢሮክራሲ ስራዎችም ነበሩት። እና ከነዚህ ሁሉ የስራ ጋጋታዎች ጋር የሚታገል ሰው ያንን የመሰለ ውብ መጽሐፍ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዴት ብሎ ነው የጻፈው? ይህንን በቀላሉ ማመን ይቻላል? በትርፍ ጊዜው መጻፉ ይቅርና የሙሉ ጊዜ ደራሲ ቢሆን እንኳ አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርለትም። ሰውዬው ግን በዓሉ ነውና ቻለው! የስራ መደራረብ “ሳይበግረው” ኦሮማይን ከዘጠኝ ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲያ ከሽኖ አቀረበው (የቀይ ኮከብ ዘመቻ ያበቃው በየካቲት ወር 1974 ነው፤ ኦሮማይ የታተመው በታህሳስ ወር 1975 ነው)። ችሎታ ማለት እንዲህ ነው!!
ለኦሮማይ ዘመን አይሽሬነት ሁለተኛ አብነት ሆኖ የሚጠቀሰው ደግሞ የመጽሐፉ ጭብጥ ነው። በዚህ ላይ በርካታ ሰዎች የተለያየ አስተያየት ነው ያላቸው። አንዳንዶች በዓሉ ኦሮማይን የጻፈው የቀይ ኮከብ ዘመቻ ውጥረትና ውድቀትን ለመግለጽ ስለፈለገ ነው ይላሉ። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “የመጽሐፉ ጭብጥ በርዕሱና በመጨረሻው ዐረፍተ ነገር ላይ ነው የሚገኘው” ብለው ነገር። አቶ መለስ ንግግራቸውን ሲያሰፉም “በዓሉ በመጽሐፉ “እናንተ ደርጎች በኤርትራ ላይ ሙዝዝ ካላችሁ በአዲስ አበባ ያላችሁንም ስልጣን ታጣላችሁ” የሚል መልዕክት ነው ያስተላለፈው” ብለዋል። አቶ መለስ ይህንን ትንተና የሰጡት ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የአልጀርሱን ስምምነት ፈርማ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ በምትጠባበቅበት ወቅት “የስምምነቱ አካሄድ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነው” የሚል ሃሳብ ለሰነዘሩ ተቃዋሚዎች መልስ በሚሰጡበት ጊዜ ነው (ባልሳሳት ጊዜው የካቲት 1994 ይመስለኛል)። ሆኖም የኦሮማይ ጭብጥ በእንዲህ ዓይነቱ የፖለቲካ ዘውግ ብቻ የታጠረ አይደለም። ኦሮማይ በዘመኑ “አይነኬ” (taboo) የነበሩ በርካታ ጉዳዮችን ይነካካል። ለማስረዳት ይፈቀድልኝ።
የደርግ መንግሥት በወቅቱ የሀገሪቱን ህዝብ ከአቅሙ በላይ እያሯሯጠው ነበር። ህዝቡ በየዓመቱ ከሚመጣበት የዘመቻ መአት ሳያገግም በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም የማያውቀው ግዙፉ የቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ በጫንቃው ላይ ወረደ (ዘመቻው የጠየቀው የሰው ሀይልና ማቴሪያል ሳይደመር ሁለት ቢሊዮን ብር ወጥቶበታል፤ ይህም በወቅቱ ከሀገሪቷ በጀት ግማሽ ያህሉን ይሸፍናል)። ሆኖም በዘመኑ ወታደራዊው መንግሥት ያሻውን ቢያቅድና ቢፈጽም አይደፈሬ ነውና ማንም ሰው አፍ አውጥቶ አልተቃወመውም። በዓሉ ግርማ ግን ለመጪውም ዘመን ትምህርት በሚሆን መልኩ የቀይ ኮከብ ዘመቻን በግልጽ ቋንቋ ሄሶታል። ለምሳሌ በመጽሐፉ ውስጥ የጋዜጠኛ ጸጋዬ ኃይለማሪያም እጮኛ እንዲህ ትላለች።
“ኤጭ እቴ! ለሁሉም ነገር ቸኩሎ መሞት! ነጋ ጠባ ዘመቻ! እድገት በህብረት ብሎ ዘመቻ! ለጦርነት ዘመቻ። የኢኮኖሚ ግንባታ ዘመቻ። ማይምነትን ለማጥፋት ዘመቻ። የቁጥጥር ዘመቻ። አሁን ደግሞ የኤርትራን ችግር ለመፍታት ዘመቻ። የዘመቻ ባህል ፈጥረናል። ያለዘመቻ ኖረን የምንሞትበት ቀን መቼ ይሆን?” (ኦሮማይ ፤ ገጽ 9)
ጋዜጠኛው የመንግሥት ባለስልጣን ሆኖ ለእጮኛው ንግግር የሰጠው ምላሽ ይበልጥ የሚደንቅ ነው። “ጊዜ ያጥረናል፤ እብዶች ነን፤ ችኩል ትውልድ፤ ያበደ ትውልድ…” ወዘተ.. ይላታል (ኦሮማይ፤ ገጽ 10)
በአንድ በኩል ጸሓፊው የዘመኑ ባለስልጣናት ለቀይ ኮከብ ዘመቻ መሳካት አኩሪ ገድል ሲፈጽሙ ያሳየናል። ወዲያው ዞር ይልና ደግሞ የመንግሥቱ የቀን ቅዠትና ሀገር አጥፊ ፖሊሲ ያስከተለውን ቀውስ በራሳቸው በባለስልጣናቱ አንደበት ይገልጽልናል። ለምሳሌ ከመጽሐፉ ዐቢይ ገጸ-ባህሪያት አንዱ የሆነው ኢኮኖሚስቱ መጽሐፈ ዳንኤል ዘመቻው በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ጫና በማስረዳት የዘመኑን አመራር እንዲህ ይሸረድደዋል።
“ይህንን የቆየ ችግር በዘመቻ እንፈታለን ብለን ስንረባረብ ከአሁኑ ሌላ ችግር እየፈጠርን ነው፤ 450 ከባድ የጭነት መኪናዎች፤ 250 ሼልቶ፣ 200 ከነተሳቢያቸው ወደ ሰሜን ማዞር ምን ማለት ነው? ባጭሩ ኢኮኖሚው ተናግቷል ማለት ነው፤ ደሞ አሁን የመኸር ጊዜ መሆኑን አትርሳ” (ኦሮማይ፤ ገጽ 75)
ጋዜጠኛው በዚህ አባባል ተናዶ “ስብሰባው ላይ ምን ዘጋህ? ቅድም እንዲህ ብለህ አትናገርም ነበር። መድረኩ ለማንም ክፍት ነበር።ማን ከለከለህ?” ሲለው መጽሐፈ ዳንኤል “ትቀልዳለህ ልበል?” በማለት በአጭሩ መልሶለታል። መጽሐፈ ልክ ነው። አንድ ሰው በሚፈልገው መንገድ ብቻ መደስኮር በሚፈቀድበት ስብሰባ ሐቁን እናገራለሁ ቢል የሚደርስበትን ቅጣት በደንብ ያውቀዋል። ለዚህም ነው በስብሰባና በጉባኤ ፊት እያስመሰሉ መለፍለፍ እና ለክፉ አሳልፎ የማይሰጥ ወዳጅ ሲገኝ ሐቁን መናገር የዘመኑ ወግ ሆኖ የቆየው።
በተመሳሳይ መልኩ ሰለሞን በትረ-ጊዮርጊስ የተባለው ገጸ-ባህሪ የያኔውን የፕሮፓጋንዳ አካሄድ እስኪበቃው ድረስ ሲወርፍ ይታያል። “እናንተ ጋዜጠኞች ጭንቀታችሁ ሁሉ ስታቲስቲክስ ነው፤ ይህን ያህል ሄክታር መሬት ታረሰ፤ ይህንን ያህል ህዝብ ተደራጀ፤ ይህን ያህል ሰዎች ከመሀይምነት ተላቀቁ፤ ነው የምትሉት። እንዲያው ወሬአችሁ ሁሉ ስታቲክቲክስ ነው፤ ዘገባችሁ ሰው ሰው አይሸትም፤ ስለ አሐዝ ስትጨነቁ ሰው ትረሳላችሁ” ይላል (ኦሮማይ ገጽ፤ 67)። እነኝህን የመሳሰሉ የስርዓቱን ጉድፍ የሚያሳዩ በርካታ አንቀጾችን መልቀም ይቻላል።
የቀይ ኮከብ ዘመቻ የመጨረሻ ግብ ናቅፋ የሚገኘውን የሻዕቢያ ዋና የዕዝ ማዕከል መቆጣጠር ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ሆኖም ናቅፋ በቀላሉ የምትደፈር ሆና አልተገኘችም። ሺዎች እንደ ቅጠል ረግፈዋል። ሺዎች ቁስለኛና ምርኮኛ ሆነዋል። ሁኔታውን በቅርበት የታዘበው ጋዜጠኛ ጸጋዬ ኃይለማሪያም ጦርነቱ ከኪሳራ ውጪ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ተገንዝቧል። ከናቅፋ ወደ አፍአበት ሲመለስ “አይዞን! ገና ሺህ ናቅፋዎች ይጠብቁናል” ብሎ ለተናገረው ባለስልጣን “እኔ አንድ ናቅፋ ከወዲሁ በቅቶኛል፤ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ ከአሁን በኋላ ላለማየት ቆርጫለሁ” በማለት ተቃውሞውን ገልጿል (በዓሉ ጦርነቱን ከተቃወመባቸው ዐረፍተ ነገሮች መካከል ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ይህኛው ነው)።
*****
“ኦሮማይ” ፈርጀ ብዙ የዕውቀት ድርሳን ነው። ረጅምና ውስብስብ የሆኑ እውነተኛ ታሪኮችን እጥር ምጥን አድርጎ በቀላሉ ያስነብበናል። ለምሳሌ የኤርትራ ችግር መሰረታዊ ምንጭ ምን እንደሆነ መረዳት የሚፈልግ ሰው ከሰለሞን በትረጊዮርጊስ ታሪካዊ ትንተና ብዙ ቁምነገሮችን ይጨብጣል (ኦሮማይ፡ ገጽ 78-86)። እንግሊዝ በኤርትራ ምድር የቀበረችው ፈንጂ፤ የኤርትራ ክፍለ ሀገርን ከኢትዮጵያ ጋር ለመቀላቀል የተደረገው ጥረት፤ የጀብሃና ሻዕቢያ አነሳስና በመካከላቸው የተፈጠረው ፍጭት፣ አብዮታዊ ሰራዊት ኤርትራን ከአማጺያን ለማጽዳት ያደረገው ዘመቻ ወዘተ… በሰለሞን አንደበት በሰፊው ተተንትነዋል (እርግጥ ትንተናው ሙሉ በሙሉ ትክክል ነው ለማለት አይቻልም፤ ግማሽ ያህሉ የደርግ መንግሥት በሚፈልገው መልክ የተቀናበረ ነው)።
የጎሪላ እና መደበኛ የውጊያ ስልትን በተነጻጻሪ ማወቅ የሚፈልግ ሰው ከኦሮማዩ ኮሎኔል ታሪኩ ወልዳይ ትንታኔ ብዙ ነገሮችን ይማራል። ኮሎኔል በትሩ ተሰማ እና አጋዥ ቡድኑ (እነ ተክላይ ዘድንግል ያሉበት) የዘመኑ የኢንተሊጀንስ ጥበብና ስልት ምን ይመስል እንደነበር በቃልና በድርጊት ያሳዩናል። ጋዜጠኛው ጸጋዬ ኃይለማሪያም አስቸጋሪውን የናቅፋ ተራሮች የመሬት አቀማመጥ ለዓይናችን ወለል ብሎ እስኪታየን ድረስ በማይሰለቸው ብዕሩ እያጣፈጠ ይተርክልናል። ስዕላይ ባራኺ እና ጓዶቹ ደግሞ የሚያስገርሙ ጀብዶችን እየተገበሩ ሻዕቢያ በሰርጎ ገቦቹ አማካኝነት አስመራን እንዴት ያሸብራት እንደነበር ያሳዩናል። የአስመራ ነዋሪዎች የአኗኗር ወግና ማሕበራዊ ህይወት፣ የከተማዋ ታዋቂ ሰፈሮችና ሆቴሎች፤ የመንገዶቹ ውበትና አቀማመጥ ወዘተ… በመጽሐፉ ዘርዘር ብለው ተጽፈዋል። በኔ እይታ አንድ ሰው ልብ ወለድ ተብሎ የተጻፈውን “ኦሮማይ”ን ቢያነብ ከአስር መጻሕፍት የሚያገኘውን ዕውቀት ሊገበይ ይችላል።
*****
እንደዚያም ሆኖ ግን “ኦሮማይ” ሙሉ በሙሉ እውነተኛ ታሪክ አይደለም። ደራሲው የመጽሐፉን ተነባቢነት ለማጉላት ምናባዊ ገጸ-ባህሪዎችንና ታሪኮችን ጨማምሯል። ለምሳሌ ደራሲው የሁለት ሰዎችን ታሪክ አዳብሎ “ስዕላይ በራኺ” የተባለ ገጸ-ባህሪ ፈጥሮልናል። እንደዚሁ ደግሞ በመጽሐፉ ውስጥ የሻዕቢያ ሰዎች በዚሁ ስዕላይ በራኺ በተባለ ገጸ-ባህሪ መሪነት የሚያካሄዱት “ኦሮማይ” የተሰኘ ስውር ኦፕሬሽን የደራሲው ፈጠራ ነው (“ቢሮክራሲ” የተባለው የስለላ ኔትወርክ ግን ትክክለኛ ነው)።
ከኦሮማይ ገጸ-ባህሪያት መካከል ኮሎኔል መንግሥቱ ሀይለማሪያምና ኢሳያስ አፈወርቂን የመሳሰሉት በእውነተኛ ስማቸው ተጠቅሰዋል። አንዳንዶቹ ግን ስም የለሽ ሆነው በድርጊታቸው ብቻ ተገልጸዋል (ለምሳሌ “የቀይ ኮከብ ሁለገብ ዘመቻ ዋና ጸሐፊ” ተብለው በስራ መደባቸው ብቻ የተጠቀሱት ባለስልጣን አቶ አማኑኤል አምደሚካኤል ናቸው)። ከፊሎቹ ገጸ-ባህሪያት በእውነታው ዓለም የሚታወቁበት ስም በመጽሐፉ ውስጥ ተቀይሯል። ከነርሱ መካከል የጥቂቶቹ ትክክለኛ ስም እንደሚከተለው ቀርቧል።
1. ኮሎኔል በትሩ ተሰማ= ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ (በደርግ መንግሥት የህዝብ ደህንነት ጥበቃ ሚኒስትር፤ ሆኖም ኮሎኔሉ “የኔ ምክትል ነው እንጂ እኔ አይደለሁም፤ እኔ በቀይ ኮከብ ዘመቻ አስመራ አልሄድኩም” በማለት አስተባብሏል)።
2. ኮሎኔል ታሪኩ ወልዳይ= ጄኔራል መስፍን ገበረቃል (በኤርትራ የተወለዱ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ጄኔራል፣ በደርግ የመጨረሻ ዘመናት ም/ኤታማዦር ሹም የነበሩ)
3. መጽሐፈ ዳንኤል= ዶ/ር ዳንኤል ክንዴ (ታዋቂ ኢኮኖሚስት፣ አሁን በአሜሪካ ሀገር የዩኒቨርሲቲ መምህር)
4. የሺጥላ ማስረሻ= አቶ ሽመልስ ማዘንጊያ (የኢሠፓ የፖሊት ቢሮ አባልና የርዕዮተ ዓለም ጉዳዮች ሃላፊ የነበሩ)
5. ጸጋዬ ሀይለማሪያም= የበዓሉ ግርማ ግርማ እና የቴሌቪዥን ጋዜጠኛው የጌታቸው ኃይለማሪያም ቅልቅል ይመስላል።
6. ተድላ ረጋሳ= ሻለቃ ፍሰሓ ገዳ (የኢሠፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደርግ መንግሥት የፕሮቶኮል ሹም)
7. ሰለሞን በትረ ጊዮርጊስ= ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ (በቀይ ኮከብ ዘመን የኤርትራ ክፍለ ሀገር ኢሠፓአኮ ተጠሪ እና የክፍለ ሀገሩ የበላይ አስተዳዳሪ፣ በኋላም የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ በ1978 ከደርግ መንግሥት ተነጥለው ወደ ውጪ ሀገር የሄዱ)
8. ስዕላይ ባራኺ= የሁለት ሰዎችን ታሪክ በመቀላቀል የተፈጠረ ነው። አንደኛው ተስፋሚካኤል ጆርጆ ነው (አቶ ተስፋሚካኤል በሀይለስላሴ ዘመን የደቀምሐረ ወረዳ ገዥ ነበሩ)። ሁለተኛው ሰው ተክላይ አደን ይባላል (ተክላይ አደን የህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የድርጅቱ የፖለቲካ ትምህርት ቤት ሃላፊ ነበር፤ በኋላ እጁን ሰጥቶ በሀገር ውስጥ ሲኖር ከቆየ በኋላ የደርግ መንግስት ሲወድቅ ወደ አውሮጳ ሄዷል)።
9. “ቢሮክራሲ”= አፈወርቂ ተወልደ መድሕን (ደሴ የተማረ የሻዕቢያ የውስጥ አርበኛና ሰላይ፣ “ቢሮክራሲ” በሚል ስም የሚታወቀውን የስለላ ኔትወርክ የሚመራው እርሱ ነው ይባላል። የህግሓኤ ምንጮች ግን ከኦሮማይ በስተቀር “ቢሮክራሲ” የሚባል ኔትወርክ አልነበረም” ይላሉ)።
*****
ስለኦሮማይ ይህንን ብያለሁ። ወደፊት አዲስ ነገር ከተገኘ መመለሴ አይቀርም። እስከዚያው ሌሎቻችሁ የምታውቁትን ጨምሩበት።
ሰላም!
—-
አፈንዲ ሙተቂ
ሸገር-አዲስ አበባ
ጥቅምት 13/2006
——
Major Dawit Wolde-Giorgis wrote a beautiful essay on Oromay after he read my treatise. So you have to search that article from the Internet and compare it with my presentation.
2 Comments
ሸገር ብሎግ እሰከ አሁን የት ነበርኩኝ ይህን የመሰለ የጥበብ ገበታ ዓይነቱ ብዛቱ ውበቱ ጥራቱ ይደንቃል ለማንኛውም ስላገኘዋቹ ደስ ብሎኛል
እጅግ በጣም ክብር ይገባችኋል ።ኦሮማይን እንደ ብርቱካን ልጣችሁ ነው ያጎረሳችሁኝ።የየምእራፍ ሽግግር የገፀ ባህርያት አሣሣል ምን ይመሥላል?አሥተማማማኝ የሆነ ሃሣብ የሚለውን መረጃ ካለ ጣል አድርጉበት