በዚህ አለም ላይ ፤እንደ ወንድ ልጅ ጨካኝ ፍጡር አለ? ወንድ ልጅ በወንድ ልጅ ሲጨክን ለከት የለውም፤ባለፈው ከስንት ጊዜ በሗላ ፎቶ ለመለጠፍ ወሰንኩ። የሃይሌ ገብረስላሴን ያክል እንኳ ያክል ባይሆን፤ የሃይሌ ገሪማን ያክል ሮጨ፤ እምብርቴን የወጠረውን የጮማ አሎሎ አቅልጨ፤ ሰው ፊት የሚቀርብ ፎቶ ተነሳሁ፤
ጢሜን ሳላሳድግ፤ አንገቴ ላይ ድግ እሚያህል ስካርፍ ሳልደገድግ፤ ዝንጥጥ ብየ ፤ ‘ጠይም አጠር ያለ አይፎን ታጣቂ’ ሆኘ፤ ተነሳሁ፤ ተነስቼም አልቀረሁ፤ ለጠፍኩትና ሎግ አውት አደረግሁ።
ትንሽ ቆይቼ አዝመራ ለመሰብሰብ ተመለስኩ ፤ሴቶች ከፎቶየ ስር የላይክ እና የልብ ምልክት ጎዝጉዘውልኛል፤ ወንዶች በበኩላቸው፤ የሳቅ ምልክት አስቀምጠውልኛል፤
ሴቶች በምህረት አይን አይተውኝ:
” አምሮብካል”
” አልተቻልክም!”
” አይን በዝቶብሃል ሽሽግ በልልኝ”
የሚሉና የመሳሰሉ ኮመንቶች ስላልነፈጉኝ ደስ አለኝ፤
ደስታየ ብዙ አልቆየም። የመጀመርያው የወንድ አስተያየት ተወረወረ:-
“በውቄ ምነው ወደ ግራ ጎን ዘመም አልህ ?፤ ውሃ ልክህ ላይ ችግር አለ እንዴ?”
ታድያ ፤እንደ ወንድ ልጅ ያለ ጨካኝ ፍጡር አለ?
ትናንት ማታ ዩቲውብ ላይ የሙዚቃ ቪድዮ ስኮመኩም ነበር፤ በመጀመርያ የገባልኝ ሰማኸኝ በለው ነው፤ ሰማኸኝ ጨምሯል!! ክብደት ማለቴ ነው! እረ ምኑን ሰጠሽ እያለ ከሚዘፍንላትን ልጅ ቂጥ ሁለት እጥፍ የሚልቅ ቦርጭ አብቅሏል ፤ ያንን ቦርጭ ይዞ “ዲስካው” እያለ እስክስታውን ሲያስነካው ፤ ዲስኩ እንዳይንሸራተት ፈራሁለት።
ብዙ ሳይቆይ፤ የዩቲውብ ባለቤት : ብቻየን መሆኔን እንዴት እንዳወቀ እንጃ “ የባይተዋር ጎጆ የሚል ዘፈን “ ሬኮመንድ አደረገኝ ፤ዘፈኑ ምንም አይወጣለትም፤ዘፋኙ በሚያባባ ዜማ” አልቋል ሰውነቴ በሞቴ “ እያለ ያንጎራጉራል፤ የሙዚቃ ቪድዮው ላይ ያለው አክተር ግን “አልቋል ሰውነቴ” ሊል የማይችል ጠረንገሎ ነው፤ ሰውነቱ የምግብ ቤት ቧንቧ ላይ ፤የሚታሰር ሳሙና ቢሆን ፤ መቶ ሰው ታጥቦበት አያልቅም ፤ደረቱ ብቻ የዘበኛ ቤት ያክላል ፤ አልታጠረም እንጂ እሱ ራሱ የባይተዋር ጎጆ ነው!
እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ያማርኛ ዘፈን ቪድዮዎች የሚታወቁባቸው ተመሳሳይ ባህርይ አላቸው፤ መጀመርያ፤ የሆኑ ዳንሰኞች ብቅ ይሉና በፈራረሰ ህንፃ ፊትለፊት ይወዛወዛሉ፤ ሁለት ፍቅረኛሞች ቁጭ ብለው ወይን ይጠጣሉ፤ ከዛ ምኝታ ቤት ገብተው በትራስ ይደባደባሉ፤ ከዛ ሴቲቱ ተነስታ ሻንጣዋን ይዛ ልትመርሽ ስትል ወንዱ ሊያስቀራት ይታገላል ፤ ገፍትራው፤ በሩን አናግታ ዘግታበት ስትሄድ ቪድዮው ይጠናቀቃል፤
እኛ ወንዶች ይህንን ስናይ ፍቅረኛችን ላይ የሰራነውን በደል አስበን እተክዛለን ፤ሴቶች ደሞ ፤ብሽቅ ፍቅረኛቸው የሰራባቸውን ግፍ እያሰቡ ይተክዛሉ፤
፤አሁን ያ ቀረ! አሁን ጊዜው የመቀመጫ ነው፤ እዚህ ግባ የማትለው ዘፋኝ ፤ እዚህ ውጣ በማይባል ድምፁ ይዘፍንብሃል ፤ ዘፋኙ በቆንጆ ሴቶች ስለተከበበ አልባሌ ድምፁን ያረሳሳሃል ፤ ማቄጥ የተሳካላቸው ቆነጃጅት የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ሲርመሰመሱ ይታያል ፤ እኛ ወንዶች ስክሪኑ ውስጥ የሚወዛወዘው ቂጥ “ የሚታይ እንጂ የማይበላ ፍሬ ‘ ሆኖብን እንተክዛለን ፤ሴቶች ደሞ ራሳቸውን ቪድዮ ውስጥ ከሚያይዋቸው ቺኮች ጋር እያወዳደሩ ይተክዛሉ፡
በመጨረሻ፤ የዩቲውቡ ሰውየ “አላሳዝንም ወይ ” የሚለውን ያስናቀ ገብረየስን የሙዚቃ ቪድዪ ለሰባተኛ ጊዜ መረጠልኝ ፤ አስኔ ፤ አላሳዝንም ወይ እያለ ፤ ሴቶች በእብሪትና በድሎት የተሞላ ዳንስ ይደንሳሉ ፤ በርግጥ ያንን እሚያክል ቦርጭ ይዘህ ሴቶችን ማሳዘን ይከብዳል ፤(ዩቲውብ ግ ን ምን ሆኖ ነው ዛሬ ቦርጭ እየመረጠ ሪኮመንድ የሚያረግልኝ)
የማሳዘን ነገር ሲነሳ ፤ሱራፌል ወንድሙ የነገረኝ ታሪክ ትዝ አለኝ፤
ጥላሁን ጉግሳ የተባለ ፀሀፌ ተውኔት ነበር ፤ በጣም ዝነኛ የሆነ፤ አሳዛኝ ተውኔት ነበረው፤ በተውኔቱ መሀል፤ የሆነ ቲንሽየ ልጅ ከመጋረጃው ብቅ ይልና “አባቴን ገደሉት እናቴን ደሞ ድፈርዋት ” ብሎ ሲናገር ድፍን ሸዋ በንባ ይታጠባል፤ጥላሁን ጉግሳ ይሄንን ተውኔት ይዞት ወደ ድሬዳዋ ወረደ፤ የድሬ ሰው ደሞ ፤ ብትንን ብሎ ቅሞ መርቅኖ ነው ትያትር ቤት እሚገባው፤ ድሬ ለመዝናናት እንጂ ለማዘን አልመጣም፤ ጥላሁን በህዝቡ መሀል ተቀምጦ ቢጠብቅ ቢጠብቅ ህዝቡ አያለቅስም፤ በመጨረሻ ጥልየ፤ አንጀት መብላት እንዳልሆለለት ሲገነዘብ ባካባቢው ከሚገኝ ቄራ ጎራ ብሎ፤ የበሬ አንጀት ገዝቶ መብላት ጀመረ፤
ባስናቀ ገብረየስ ዘፈን ስር “በርታ” የሚል ኮመንት አደረግሁና ላይክ መጠበቅ ጀመርሁ፤ወፍ የለም፤
ያንን አጠፋሁና ሌላ ኮመንት አስቀመጥኩ፤ከጥቂት ደቂቃ በሁዋላ ስመለስ ኮመንቴን አምስት መቶ ሰው ወዶታል፤ ኮመንቴ እንዲህ የሚል ነበር፤
I’m from Eritrea I love Ethiopian music !
One Comment
ያምራል