Tidarfelagi.com

እውነትን ፍለጋ

እኔ 
እኔ ከገንፎ ውስጥ ስንጥር ስጠረጥር
ስንጥር ውስጥ አገኘሁ ገንፎን ያህል ሚስጥር
ሽንፈቴን ልቀበል ስህተቴን ገጠምኩኝ 
ካንቺ ጋር ስጣላ ከራሴ ታረ‘ኩኝ

አንቺ 
ከተኩላ መንጋ ውስጥ በግ ስለተመኘሽ
ከበጎችሽ መሀል ተኩላሽን አገኘሽ
እውነትሽን ስትሸሺ ግራ ስለገባሽ
ከራስሽ ተፋተሽ ከባዳ ተጋባሽ

ያገባሽው ባዳ
ማስመሰል ለመደ ማስመሰል አወቀ
ከት ብሎ አልቅሶ ስቅስቅ ብሎ ሳቀ
ስትገቢ እያነባ ስትወጪ ይፈግጋል
ቀዳዳው ላይ ቆሞ ሽንቁር ይፈልጋል

አሰስን
እኔ ባለፈ እጄ ነገዬን ለመግለጥ
ከኔ ሊየሳንስሽ እሱ አንቺን ለመብለጥ
ሀቅን ማሰሳችን በራሳችን አለም
እውነት ቢሆን እንጂ ትክክል አይደለም
ምክንያቱም
ጥርጣሬ ዘርቶት ምክንያት ያበቀለው
ውሸትም እራሱ የራሱ እውነት አለው

እናም አልን 
በሀሰት መነፅር ውሸትን ልናሳይ
ትክክል ነው አልን የእውነት ተመሳሳይ
ለሰራነው እውነት አምሳያ ብናጣም
በእውነት መስፈሪያ ልክነት አይመጣም

ሰውነት እንዲህ ነው
መጠርጠር ስንጀምር እምነታች‘ን ገድለን
“ክትትላችን” ነው “ትክክል” ሚመስለን

ከራስ ፀብ እንዲህ ነው
ሞጋች ህሊናችን ጥፋተኛ ሲለን
“መወቀስ” ነው ለኛ “መቀወስ” ሚመስለን

እብደት ይመስለናል 
እያወሩ መሄድ እየሄዱ ማውራት
የሄደን መሸኘት የመጣውን መጥራት
ጆሯችንን ደፍነን ላንሰማ እያወራን
የደሀ አደጉን ግፍ ማድመጥ እየፈራን
ሰሚ አልባውን ጩኸት እብደት ብለን ጠራን
በወለቀ ካድሬ ሆጌሻ እያሳሸን
ሀኪም አዋረድን ፈውስ እያበላሸን
በንክ አስተሳሰብ እብደት እየለካን
የተሻልን መስሎን በቀውሳችን ረካን

እና እንደሰማነው
ስለ አባቶቻችን እንደተነገረ
ላመኑበት እውነት ይሞቱ ነበረ
እኛም ልጆቻቸው ዛሬ ታሪክ ሰራን
ላመንበት እውነት መኖር እየፈራን
መፍራት ብቻ !
መሸሽ ብቻ !
“ወደ ኃላም መሸሽ ወደ ፊትም መሸሽ” !
“እውነትንም መፍራት ውሸትንም መፍራት” !
“ውስጣችንን መሸሽ ውጪውንም መሸሽ” !

ሽሽት እና ፍርሀት
ፍርሀት እና ሽሽት እያፈራረቅን
ከእውነት ለማምለጥ
የውሸት ስንሮጥ ከትክክል ራቅን

አቅጣጫው አይለይም የሩጫችን ዳና
ፈሪ መንገድ ሰርተን በጀግና ጎዳና
=======||========

One Comment

  • mohammeddulla4142@gmail.com'
    መሀመድ ዱላ commented on June 17, 2019 Reply

    የ አፕሊኬሽን መተግበርያቹ ስልካችን ላይ እየሰራ አይደለም
    ማሰወተካከል ያለባቹ ነገር አለ
    ኮኔክሽን እያገኘ የለም እያለ ተቸገርኩኝ

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...