Tidarfelagi.com

እኛ ነን እኛ!

መግደልና መናድ እንጂ!
ተስማምቶ መኖርና ማኖር ያቃተን፣
በሃሳብ መሸናነፍ እጅግ የከበደን፣
ከመካብ ይልቅ ማፍረስ የሚቀለን፣
የሃሳብ ልዩነት ሁሌም የሚገለን።

በመጠፋፋት ታሪካችን!
ዓለሙ የሚያውቀን፣
በዚህም የሚንቀን፤
የመገዳደል አዚም የተጋተን!
ክፉ አዙሪት የሚነቀንቀን።

የውጪ ጠላት ሲመጣ የምንስማማ፣
የውጪ ጠላት ሲጠፋ…
እርስበርስ ተጠላልተን፣
ተገፋፍተን፣
እርስበርስ የምንጠፋፋ።

እኛ ነን እኛ!
በመገዳደል አንደኛ!
መለወጥ ያልቻልን፣
ዘመን ያላደሰን፣
ክፉ ትናንትን ያልቀየርን፣
በጎ ማሰብ የተሳነን፣
ኅሊናችን የማይወቅሰን፣
አዎ እኛ ነን እኛ!
ትንሽ ማሰብ! ያሳነሰን።

ከመስፋትና አንድ ከመሆን ይልቅ!
ጠብበን፣ ጠብበን ልናልቅ፣
አንድ ሐሙስ የቀረን፣
መልካሙን ሁሉ ፈጅተን፣
መጥፎውን ብቻ አስቀርተን፣
በሙጣጩ ያለን።

ታሪክ እያለን ያልተስተማርንበት፣
እምነት ቢኖረንም አንዳች ያልኖርንበት፣
እንደእኛ ማን አለ?
እንደኛ!
አንደኛ!

ሰውነታችን ላይ የሸፈትንበት፣
ሕሊናችን ላይ የሸፈጥንበት፣
ጥበባችን ላይ ያላገጥንበት፣
ታሪካችን ላይ የከሸፍንበት።

እህ!
እርስበርሳችን ላይ መጠቋቆም እንጂ!
ለሐገር የሚበጅ፣
ልማት ማምጣት የታከተን፣
ኖሮ ማኖር ያቃተን፣
ለሕዝብ የማይበጅ….
የሴራ ፖለቲካ መጎንጎን እንጂ!
ዕድገትና ብልጽግና የተራቆተን፣
እንደኛ ማን አለ?
እንደኛ!
አንደኛ!

ኋላቀርነት የማረከን፣
መጥፎ ታሪክ የጎተተን፣
ዘመናዊነት የፎተተን።

አዎ! እኛ ነን እኛ!
አንደኛ!
ተፈጥሮ ያልለወጠን፣
አዲስ ሃሳብ ያልናጠን፣
ክፉ አስተሳሰብ ያገጠጠን፣
የዘረኝነት ዋሻ የዋጠን፣
“እኔ ብቻ ልኑር!” ያናወጠን፣
የደም ፖለቲካ….
አድምቶ አክስቶ ያደቀቀን፣
ሕሊናችንን ያስወለቀን፣
እርስበርስ ያሯሯጠን፣
እልፍ መልካም ቀን ያመለጠን፣
አዙሪት ወድዶ የመረጠን።

ዘመናችንን ያልቀየርን፣
ጊዜም ያልቀየረን፣
በእጃችን ያለ መልካም ነገር፣
ሊያስማማን የሚችል ቁምነገር፣
አንድም ያላስቀረን፣
ምንም የለም በእጃችን!
ለምልክት እንኳን የቀረን።

አዎ! እኛ ነን እኛ!
አንደኛ!
ዲስኩረኛ፣
ምግባርና ተግባር የጎደለን፣
የሚጨበጥና የሚያዝ የሌለን፣
ወደረኛ!
ሕሊና ያላደሰን፣
ሰውነት ያልመለሰን፣
ሃይማኖት ያልፈወሰን፣
ሳይንስ ያልቀየሰን፣
ለሐገር ማሰብ ያልቀመሰን፣
ታላቅና ሠፊ ሐገር ኖሮን ሳለ…
ለምለም ምድር ተችሮን እያለ፣
መልካም ማሰብ ቸግሮን፣
ድንበሩ ያነሰን፣
መገዳደል የጨረሰን፣
ሥራችን ያሳነሰን።

እንደእኛ ማን አለ?
እንደኛ!
በመገዳደል አንደኛ!
አፈናቃይ ዘረኛ፣
ጦርነት አዋቂ ጦረኛ፣
የዴሞክራሲ ጥማተኛ፣
የፍትህ እጦተኛ፣
የእኩልነት ረሃብተኛ፣
አድሏዊ አድሎኛ፣
በመጠፋፋት ወደረኛ!
የራስ ሐገር ባላንጣ!
የጠላት አርበኛ፣
ማንም የለም ያለእኛ።

___________________________

እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)

ቅዳሜ ሰኔ ፳፪ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.

2 Comments

  • Se Humed Aafar commented on October 8, 2019 Reply

    wow batam harif new

  • www.info@seidhumedafar.com'
    Se Humed Aafar commented on October 8, 2019 Reply

    wow batam harif new

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...