አውቀን የተኛን ነን፡፡ ቢቀሰቅሱን የማንሰማ! ከከተሳካልን ቀስቃሾቻችንንም አሰልችተን የምናስተኛ! …ሰውነታችን ጣምኖ ጮማ ከምንቆርጥ ይልቅ፣ ያለምንም ልፋት የምናገኛትን ጎመን እየላፍን፣ “ጎመን በጤና” የምንል ዘመናዮች ነን፡፡ ታሪክ ዳቦ አይሆንም ብለን፣ ታሪክ የማይሆን ዳቦ እየገመጥን ያለን በልቶ አደሮች ነን፡፡ ነፃታችንን ከባርነት እግር ስር የደፋን አርበኞች ነን፡፡ በአንድ ባለራዕይ ስንገዛ የነበርን፣ እሱ ሲሞት “ራዕዮን” ተከትለን መቃብር የወረድን ራዕየ-ቢሶች ነን፡፡
ባህል የሚያቀነቅነን፣ ምክንያት የሚቀናቀነን ነን!! ሁለ ነገራችን ሆሆሆ… ነው፡፡ በምክንያት መቃብር ላይ የምንጨፍር ዳንኪረኞች ነን፡፡ ጭፈራችን፤
“ሆያ ሆዬ…. ሆሆሆሆሆ…” ነው፡፡
“ሆሆ… ብለን መጣን ሆሆ… ብለን” ነው፡፡
“ያ ሆሆ….” እያልን ነው የምናደምቀው፡፡
“ሻሞ፤ ሆ… ሻሞ ሆ…” እያልን ነው ያደግነው፡፡ ስንጫወት ብቻ ሳይሆን ስናስብም ስናስብም “ሆሆሆ…” ብለን፡፡ እኛ ጋር ሃሳብ ልክ የሚሆነው በሃሳቡ የልክነት መጠን ሳይሆን፣ በተካታዩ ብዛት ነው፡፡ ሆ ብለን ያነሳነውን ሆ ብለን እንጥላለን፡፡ “የኢትዮጵያ ብሄር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች” እያሉ ስማችንን ከሚያንዛዙት ለምን የ”ሆ” ህዝቦች ብለው በአንድ ፊደል አይገላገሉንም? “ሆ” ከሚለው በላይ የሚገልፀን ቃ ከወዴት ይገኛል?
በእንግሊዘኛ የሚያነጥሱ፣ በእንግሊዘኛ የሚያለቅሱ፣ እንግሊዘኛ የሚተነፍሱ በእንግሊዘኛ ስቅ የሚላቸው፤ አማርኛ እንቅ የሚያደርጋቸው ልጆች ያፈራን ኢንተርናሽናል ዜጎች ነን! ማንም እኛን ለመሆን ባይፈቅድም፣ ማንንም ለመሆን የፈቀድን የዓለም ዜጎች ነን!! Can ya c that guys? Don’t fuck with us then! We are what we are, you cant escape it, Neither we!
ስህተታችንን ዘንግቶ በጩኸት የሚያደንቀንን እንጂ፣ ተሳስታችኋል የሚለው ቃልም ሰውም ጠላታችን ነው፡፡ ከመደነቅ አልፈን መወደድ ነው የምንፈልገው፡፡ ሂስ የሚሉት ክፉ ዘፈን አይገባንም፡፡ ከኛ የሚበልጡ የመጡ የመሰለን ጊዜ ግን ይሄን ክፉ ዘፈን ድብልቅ አርገን እንከፍተዋለን፡፡ ጀማርያንን በማበረታታ ሰበብ እራሳችንን የማጥፋት ትልቅ ወንጀል ሆኖ ነው የሚታየን፡፡
“ማሰብ ክልክል ነው” የሚል የማይታይ ግን በጉልህ የሚነበብ ትዕዛዝ በየቦታው ሰቅለናል፡፡ ከአንዳንድ አጓጉሎች በስተቀር ይመስገነው ሰፊው ሕዝብ አላሳፈረንም- ባለማሰብ ተባብሮናል፡፡
መጠየቅ የሚሉትን ነገር በጥፊ እያላጋን፣ በካልቾ እየቆጋን አባረን፣ ካለማሰብ የተሰራ ምቹ አልጋችን ላይ ፍልስስ ብለን እንቅልፋንን በምቾት የምንለጥጥ “ባለጊዜዎች” ነን፡፡ ማሰብ የሚሏት ሹክሹክታ የመጣች ለታ፣ “ደንስ ጎበዝ” እየተባባልን ታምቡር በሚበጥስ ዜማ ድምፅ እንነሳታለን፡፡ ብዙዎች የሚሄዱበት እንጂ፣ ጥቂቶች የሚሄዲቦት መንገድ ጥራት ይጎድለዋል ለኛ፡፡ መንገዳቹህ እሾሃማ ነው ቢሉን አንሰማም- እንዴት ይሄ ሁላ ሰው ይሳሳታል ይሉናል? ደፋሮች!!
እንዲህ ነን እኛ! ብዙ ነን እኛ!! ረቂቅ ነን፡፡ አንጨበጠጥም፣ ቀድመን ተጨባብጠናላ! … ምን ያልሆነው አለ? ምንም! ምንም ሆነናል!!