(መነሻ ሃሳብ፡ የሰርክ አለም መጋቢያው ‹‹አሮጌው ገንዘብ›› እና የሐና ሃይሌ ‹‹ሀው ወዝ ማይ ደይ›› አጭር ፊልሞች)
ሥራ ውዬ እና የማታ ትምህርት አምሽቼ ሶስት ሰአት ከአስር ገደማ ቤቴ ገባሁ።
ብቻዬን ከምኖርባት ሚጢጢ ቤቴ ገብቼ ከፍታ ካለው ጫማዬ ላይ ከመውረዴ ታላቅ ወንድሜ ደወለ እና
‹‹ እህስ…እንዴት ዋልሽ?›› ብሎ ጠየቀኝ።
እንዴት ዋልኩ?
ከወትሮው በጣም አርፍጄ ነበር ከጠዋቱ አንድ ሰአት ላይ ከእንቅልፌ የነቃሁት። አለቃዬ ‹‹ማንም እንዳያረፍድ›› ብሎ ሲያስጠነቅቀን ለነበረው ከባድ ስብሰባ ማርፈዴ መሆኑ ሲታወቀኝ ከአልጋዬ ውስጥ ተስፈንጥሬ ተነሳሁ።
ዘወትር እንደማደርገው ልብሴን ከጌጣጌጤ፣ የከንፈር ቀለሜን ከጫማዬ የማቀናጃ ጊዜ አልነበረኝም። ፊት ለፊት ያገኘሁትን አጭር ጉርድ ቀሚስ በጠባብ ሹራብ እየለበስኩ ፌቴን እንደነገሩ ታጠብኩ።
ፀገሬ! ፀጉሬ ተንጨባሯል።
ይሄን የሚያህል ስብሰባ በዚህ ፀጉር ብገባ የአለቃዬን ኩርፊያ የዛሬው የግንቦት ፀሃይ እንኳን እንደማያሞቀው ስለማውቅ ሙልጭ አድርጌ በጨዋኛ አስያዝኩት።
ኩሌን ኳል ኳል፣ ቻፒስቲኬን ቀባ ቀባ አድርጌ ሁሌ የማደርጋትን የስብሰባ ጫማዬን አጠለቅኩ እና እየተደናበርኩ ወጣሁ።
በሬን ቆልፌ ከመውጣቴ ሞረሞረኝ።
ርቦኛል።
ጊዜ ሲኖረኝ በቅንጬ እና በጨጨብሳ የምደለድለው የጠዋት ሆዴ ሲጮህ፣ አንጀቴ ሲታጠፍ ተሰማኝ።
ጫማዬን ከትልልቅ ድንጋይ እየጠበቅኩ በምችለው ፍጥነት በመጀመሪያው ቅያስ ላይ ወዳለው የብርሃኑ ሱቅ በሩጫ ቀረሽ አረማመድ ሄድኩ።
ብርሽ ሬዲዮውን እየሰማ ገበያተኛውን ያስተናግዳል።
‹‹ብርሽ አቡ ወለድ ስጠኝ?›› አልኩት አስር ብር ከቦርሳዬ እየጎተትኩ።
አቀበለኝ እና ‹‹አንቺ ግን ሴት ሆነሽ ቁርስ መስራት ይከብድሻል? ሆይ!›› ሲለኝ ዝም ብዬ ትንሽዋን የብስኩቴን ካርቶን ነጥቄው፣ ሁለት ብር መልሴን ተቀበልኩና የፍጥነት ጉዞዬን ቀጠልኩ።
ታክሲ ያለበት ዋና መንገድ ጋር ለመድረስ ትንሽ ሲቀረኝ ‹‹ ሴት ሆነሽ መንገድ ላይ ስትበይ ሼም አይቆነጥጥሽም?››የሚል ሻካራ ድምፅ ስስማ ዞር አልኩኝ።
ፀጉሩን እንደ ቀንድ ያሾለ ከሃያ የማይዘለው ጎረምሳ ነው።
ግንብ ስር እየሸና ነው የሚያወራኝ። ጭንቅላቴን ግራና ቀኝ ነቅንቄ መንገዴን ቀጠልኩ።
የታክሲው ሰልፍ ተስፋ ያስቆርጣል።
ዛሬ አለቀልኝ በቃ።
እዩት ይሄ ደግሞ በ‹‹ሰዎች ሰልፉን እየሰበሩ ገፉኝ›› ሰበብ አስሬ ሲተሻሸኝ!
የምችለውን ያህል እየሸሸሁት ተራዬ ደርሶ ልገባ ስል ወያላው ደግፎ በማስገባት ሰበብ ቂጤንን ሲነካኝ ስቅጥጥ ብሎኝ ‹‹ልቀቀኝ አንተ!›› አልኩኝ። ‹‹አቦ አታካብጂኣ! ከገባሽ ግቢ!›› ብሎ ቆሞ ያየኝ ጀመር።
ምርጫ አልነበረኝም። ገባሁ።
ጉዞ ስንጀምር አንዴ እያለቀ ያለ ሰአቴን፣ አንዴ ደግሞ ታክሲው ውስጥ የተለጠፉ ‹ጥቅሶችን›› እያቀያየርኩ ማየት ጀመርኩ።
‹‹ሴት ደሃን የምትወደው ፊልም ላይ ብቻ ነው››
‹‹የቤትሽን አመል እዛው!››
‹‹ወንድ ልጅ አይጣ!››
‹‹ሴት እና ታክሲ ትርፍ መጫን ልማዳቸው ነው››
ሰውነቴ ሲግም ተሰማኝ።
እንደምንም ደረስኩ።
አስር ደቂቃ አርፍጄ እያለከለክኩ ስገባ አለቃዬ የቢሮዬ በር ላይ ቆሞ ሳገኘው ውሃ ሆንኩ።
‹‹አጅሪት!›› አለኝ በዚያ ሹል እና ቀጭን ድምፁ።
‹‹እንደምን አደርክ አቶ ታሪኩ?›› አልኩት በሙሉ አይኔ ላላየው እየሞከርኩ።
‹‹በመጨረሻ መጣሽ…?መኳኳሉ ቀርቶብሽ ሥራ በጊዜ ብትገቢ ምን ይመስልሻል…? የማትችይ ከሆነ እንደ አንቺ አይነቷን ለማግኘት አስር ደቂቃ አይፈጅብኝም…አሁን እዚህ ህንፃ ስር ያለው ካልዲስ ብሄድ ሰባት ያንቺ አይነት በአስር ደቂቃ ይዤ መምጣት እችላለሁ እሺ….ገባሽ…?››
ዝም አልኩ።
‹‹ገባሽ ወይ…?››
‹‹ገብቶኛል››
‹‹ሹራብሽ ደግሞ መንችኳል። በዚህ ሁኔታሽ የሴልስ ሚቲንግ አትገቢም። ማህሌትን ቢሮዬ ጥሪያት!››
ድምፁ እንደ መርፌ ይወጋኛል። ቃላቱ እንደ ቢላዋ ይከትፉኛል።
ዘንጬ እና ተኳኩዬ እንድመጣ ይፈልጋል። ከሚሸጣቸው መኪኖች እኩል ተወልውዬ እንዳብረቀርቅ ይፈልጋል። እንደዛ ሳደርግ ደግሞ ሁሉን ትተሸ ስራሽ መኳኳል ብቻ ሆኗል ይለኛል። የሚፈልገው አይገባኝም።
ከረጅም እና አድካሚ የስራ ቀን እና የትምህርት ምሽት በኋላ ወደ ቤቴ የሚያደርሰኝ ታክሲ ውስጥ ተቀምጫለሁ።
ታክሲው ሊሞላ ሁለት ሰው ቀርቶታል። ዞር ብዬ አየሁ። ሴት የሚባል የለም።
ውስጤ በፍርሃት ሲርድ ተሰማኝ። ‹‹ልውረድ ልቅር›› በሚል ሙግት ተወጥሬ ሳለሁ አንዲት ሴት ልክ እንደኔ ባለ ሁኔታ የታክሲውን የፃታ ተዋፅኦ ፈጥና ካጣራች በኋላ ስትገባ እፎይ አልኩኝ።
ወንዶች ማታ ማታ ታክሲ ውስጥ ሲገቡ ይሄን አይነት ትንሽ ጥናት ሊያደርጉ ይገደዱ ይሆን?
መንቀሳቀስ ስንጀምር የአነዳዱ ፍጥነት እና የሙዚቃው ምት ታክሲዋን ይንጣት ጀመር።
‹‹ትብላው ብሬን›› ይላል ዘፈኑ።
ሹፌሩ እና ወያላው አብረውት ይዘፍናሉ።
ሁለት ከፊቴ የተቀመጡት ወጣቶች ራሳቸውን በስሜትም በስምምነትም ይነቀንቃሉ።
‹‹ትብላው ብሬን›› ይላል ዘፋኙ።
ደርሼ ተገላገልኩ።
ሶስት ሰአት ለመሙላት ጥቂት ሲቀረው መብራት በሌለበት የሰፈሬ ኮረኮንች መንገድ ወደ ቤቴ እራመዳለሁ።
ከወትሮው ትንሽ ስላረፈድኩ ‹‹ምን እና ማን ይገጥመኝ ይሆን›› እያልኩ አጭር ቀሚሴን በጉተታ ለማስረዘም እሞክራለሁ።
እየሮጥኩ እራመዳለሁ።
ሊደርስብኝ ስለሚችለው ክፉ ነገር እያሰብኩ፣ ቀሚሴን እየጎተትኩ፣ ሃሳቤን እየገሰፅኩ፣ አለቃዬን እየተራገምኩ፣ ጨለማ በወረሰው ቀጭን ኮረኮንች መንገድ እሮጣለሁም። እራመዳለሁም።
ደረስኩ።
ታድዬ! ምንም ሳልሆን ደረስኩ።
‹‹ስሚ እንጂ›› አለኝ ወንድሜ
‹‹ወዬ…?››
‹‹መልስ ስጪኝ እንጂ…!››
‹‹ምን ነበር ያልከኝ?››
‹‹እንዴ…እንዴት ዋልሽ…ቀንሽ እንዴት ነበር ነው ያልኩሽ›› አለኝ ግራ ገብቶት።
‹እ…ቀኔ…ቀኔ እንደተለመደው ነበር››