ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት፣ በባልንጀራየ በሲራክ ገፅ በኩል ሳልፍ ፣ ካንድ ዜና አይሉት መርዶ ጋር ተገጣጠምኩ።
እነ ወተት ፣እነ በርበሬ ፣እነ ለውዝ ፣ለካንሰር የሚያጋልጥ ንጥረ ነገር መያዛቸው ተረጋገጠ ይላል ዜናው።
– እንዲህ ተሆነማ ምኑን በላነው?! ምኑን ኖርነው?! ማሊን ጂራ ?!
ወተት ካልጠጣህ የካልስየም እጥረት በጠረባ ይጥልሃል፤ ወተት ከጠጣህ ደግሞ ካንሰር ይገድልሃል፤ የትኛው ሞት ይሻልሃል?! እና መኖር ማለት ከዘጠኝ ሞት አንዱን የመምረጥ ሂደት ነው?
ዘመናዩ ሰው ፣ ፈርዶበት ፣ካንዱ ስጋት ጣቢያ ወደ ሌላው የስጋት ጣቢያ ሲዘል የሚኖር ፍጡር ነው።
በመጀመርያ በራብ ላለመሞት ይፍጨረጨራል፤ ይቀጥልና እስኪጠግብ ለመብላት ሌት ተቀን ይሠራል። ከዚያ፣ጠንክሮ ሠርቶ ወይም ጠንክሮ ሰርቆ ደና ጥሪት ያኖራል። ከዚያ፣ ሪሁን ሳይቀሰቅስ ፣የሚወደውን ጥሬ ስጋ መብላት እንዴት እንደሚችል በማሰብ ይጠመዳል። ክልኩልቱን ለማቅለል ፣ቦርጩን ለማርገፍ ይወጣል ይወርዳል።
አለማችንን መቅጨት እንፈልጋለን። በጤና መኖርም እንፈልጋለን። ሁለቱ ፣ብዙ ጊዜ አብረው አይመጡም።
ተፈጥሮ ደስታን በብላሽ(በነፃ) አትሰጥም። አንድ እፍኝ ደስታ ትሰጥህና ‘ላንዳንድ ነገር ይሁንህ ‘ብላ አንድ ቁና ስቃይ ትጨምርልሃለች።
ስለ መብላት ካነሳን ዘንዳ፣ ስለጥሬ ስጋ እናውጋ።
ከባንዲራው ቀጥሎ ያገሬ ሰው መለዮ ብርንዶው ነው። ጥሬ ስጋ ዝምብሎ ምግብ ብቻ አይደለም። የክብር መገለጫ ሆኖ ቆይቷል። በማህበረሰብ ርከን ውስጥ ፣ የፒራሚዱ ጉልልት ላይ ከደረስክ ብቻ ጥሬ ስጋ ትበላለህ።
ከጥሬ ስጋ የሚገኘው ርካታና ደስታ ፣ ዋጋ ያስከፍላል። ባያቶቻችን ጊዜ፣ ላቅመ ጥሬ ስጋ የደረሰ ሰው በወር ቢያንስ ሁለቴ ኮሶ ሊታየው ይችላል። እናም ኮሶ ከተባለ ውብ ዛፍ የተቀመመ መዳኒት እንዲጠጣ ይደረጋል። የኮሶ መጠጥ የምሬት አልፋና ኦሜጋ ነው ማለት ይቻላል። ያንን የጠጣ ሰው ለሁለት ሰአት ያህል መላ ሰውነቱ ይርዳል። ለጥቂት ቀናት ባደባባይ አይታይም። ለጥቂት ጊዜ ያገለገለ እቃ መስሎ ፣ ከለት ተለት ተግባሩ ተገልሎ ይቆያል። ከዚህ ሁሉ ስቃይ በሁዋላ” ባይበላስ ቢቀር” ብሎ እጁን አይሰበስብም። ሲሻለው እንደገና ቢላዋውን ታጥቆ ይሰማራል።
አንዳንዴ ከዚህ የባሰም ይገጥማል።
ግራዝማች ዮሴፍ ንጉሴ የውጫሌ ውል አስተርጏሚና ለዛ ያለው ፀሀፊ ነበር። ባድዋ ጦርነት ፣ ጥይት ሳይነካቸው ወደ ሸገር ከተመለሱት እድለኞች አንዱ ነበር። ከጥቂት ወራት በሁዋላ ግን መጠኑን የዘለለ የኮሶ መዳኒት ወስዶ ተኛ። ከተኛበት አልነቃም። እንዴት ያለው ጅግና ከጦር ሜዳ ተረፈ፤ በሞተ በሬ ተሸነፈ።
የፅሁፉ አላማ ጤነኛ አመጋገብ ባህል እንዴት እናዳብር?! ምናምን የሚል አይደለም። እየኖርኩ ስሄድ የገባኝ አንድ ነገር ቢኖር ጤነኛ አመጋገብ የሚባል ነገር አለመኖሩን ነው። ቬጂተርያን መሆንም የህይወት ቤዛ አይሆንም። የሽንት ገባር ወንዝ ያበቀለውን ያዲሳባ ሰላጣ የሚበላ ሰው ፣ ከጥሬ ስጋ አፍቃሪው የተሻለ የጤና ዋስትና ሊኖረው አይችልም።
ባጠቃላይ፣
ስለ መብል ስለ መጠጥ ፣ስለ ሲጃራ ፣ስለ ሌላም ጥቅምና ጉዳት ምክር ሊመክረኝ የሚቃጣ ሰው ሲገጥመኝ ፣ እንደ ተቀደመ እነግረዋለሁ። ወዳጄ ራሴን ከመከርኩት ቆየሁ እለዋለሁ። ራሴን ምን ብየ መከርኩት፤
“በዚም አለ በዚያ ፣
የማይቀር ከሆነ፤ ወደ ሞት መሻገር
እንዲገድልህ ተመኝ፤የምትወደው ነገር
(የግጥም መነሻ: ቻርለስ ቡኮውስኪ)
3 Comments
abo yimechachu…….
በጣም ሚገርም ነገር ነው በርቱልኝ
በጣም ወደድኩት