Tidarfelagi.com

‹‹እኔም የናፈቅኩት ጨዋታሽን ነበር››

እንደ ወትሮው የማያቋርጥ የቢሮ ስራ ሲያዝለኝ ነው የዋለው፡፡
ጨዋታ ናፈቀኝ፡፡ ሙዚቃ አማረኝ፡፡ መደነስ ውል አለኝ፡፡ እንደለመድኩት ልክ እንዲህ ስሆን ነዳጅ የሚሆኑኝ የድሮ ሙዚቃዎችን ፍለጋ በተቀመጥኩበት ኮምፒውተሬ ላይ ዩቱዮብን ማሰስ ላይ ነበርኩ፡፡

ያው በኮሮና ምክንያት እስካሁን ስራዬን ከቤት አይደል የምሰራው? ልክ ቢሮ እንዳለሁ ዴስኬ ላይ ቁጭ ብዬ በኮምፒውተር ከምሰማ…ምን አሳቀቀኝ…? ማን ያየኛል? ለምንድነው ዩቱብን ከቲቪዬ አገናኝቼ …ሙዚቃዬን ከጣሪያ በላይ ከፍቼ… ሳሎኔ ሄጄ ዳንኪራዬን የማላስነካው? ብዬ ሳሎን ሄድኩ፡፡

ቴሌቪዥኔ ላይ ዩቱዩብን ከፍቼ እንደለመድኩት ሪሞት ኮንትሮሌ ላይ እየተንቀራፈፍኩ የምፈልገውን ቪዲዮ ስም ልጽፍ፣ ስል በድምፅ ትእዛዝ ብቻ የምፈልገውን ርእስ ሰጥቼ ውጤቱን ማየት እንደምችል መልእክት አይቼተረዳሁ፡፡ ጎሽ! ቲቪው በተገዛ በስንት ጊዜዬ ነው ይሄን ያወቅኩት ግን ምን ገዶኝ?

እንዳልኳችሁ የሚያጫውትም፣ የሚያስደንሰኝም የድሮ ዘፈን ነበር የፈለግኩት፡፡
ድንገት ከየት እንደመጣ ሳላውቀው ምን አማረኝ? ምን ውል አለኝ? የአረጋኸኝ ወራሽ እንሻገር ጎንደር፡፡

እስቲ የዚህን የድምፅ ትእዛዝ ጉድ ልይ ብዬ፣ ሰፍ ብዬ፣ የሚነካውን ነክቼ ለመጀመሪያ ጊዜ ቲቪዬን በድምፄ ለማዘዝ ተዘጋጅቼ ምን አልኩት?
‹‹አረጋኸኝ ወራሽ ኦልድ ሶንግስ››
….በእንግሊዝኛ የሚያስበውን ቴሌቪዥኔን ‹‹አረጋኸኝ ወራሽ እንሻገር ጎንደር››ብለው ይማታበታል ብዬ ማሰቤ ነው፡፡
እሱስ ምን አመጣልኝ?
ሽፍታ በሽፍታ- ብጉር በብጉር የሆኑ መአት የአዛውንት ገላዎች!

አማርኛ ለማያውቀው፣ ከአረጋኸኝ ወራሽ ለማይዛመደው፣ ጎጃምን አልፎ ጎንደር መሻገር ምን ማለት እንደሆነ ለማያውቀው ባእድ ቴሌቭዠኔ የአረጋኸኝ ወራሽ የድሮ ሙዘቃዎች አይገቡትም፡፡
ሰለዚህ የሰማ የመሰለውን አጠጋግቶ የምን ውጤትን አመጣልኝ? ‹‹ኦልድ ፒፕል ኤንድ ራሽ…›› ….

ክትክት ብዬ ታይፕ ወደ ማድረጌ ተመለስኩ፡፡
ከታሪኬ የተጋመደ ፣ከኢትዮጵያዊነት የተሳሰረ፣ አማርኛ የሚሰማ ቴሌቭዥን በሀገሬ ልጆች እስኪሰራ …
የምፈልገውን በትክክል ተይቤ ‹‹አረጋኸኝ ወራሽ እንሻገር ጎንደር›› ብዬ፣ በአረጋኸኝ ተዝናናሁ…

አንዱን የዘፈን ክፍል በዚያ እርጎ ድምጹ ረጋ ብሎ ሲዘፍነው አብሬው አንጎራጎርኩ፣…ያንኑ ዘፈን ቆይቶ ሲያፈጥነው ደግሞ አብሬው ዘለልኩ፡፡
ጨዋታ የናፈቀውን ገላዬን
‹‹ተይ ጓጓሁ ተይ ሳሳሁ እባክሽ ተጫወች-
ዘፈኑን አድምቀው ባረጉት እንዲመች
አትደክምም ይሉሻል አንዴ ከገጠመች
እስቲ እምቧ ሲሉ ምቺው ትከሻሽን
ትመኪበት እንደው ጎጃሜነትሽን
እንግዲህ ወገብሽ ይበል ሰበር ሰበር
እኔም የናፈቅኩት ጨዋታሽ ነበር›› ብሎ ሲያበረታኝ ደግሞ በሰከንድ ጎጃሜ ሆኜ እስክስታዬን ያለ አጃቢ፣ ያለ ተመልካች አቀለጥኩ….እጅጉን ተዝናናሁ፡፡

እንዴት ናችሁ ጃል?

 

Aregahegn Werash – Abay Yabeqelesh/Enshager Gonder (አባይ ያበቀለሽ /እንሻገር ጎንደር) 1985 E.C. – YouTube

 

ሕይወት የአድቮኬሲና የኮሚውኒኬሽን ባለሙያ ስትሆን የትርፍ ጊዜ ፀሃፊ ናት፡፡

One Comment

  • ኮዲኒ commented on June 5, 2021 Reply

    ደህና አንቺ እንዴት ነሽ ?

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...