Tidarfelagi.com

የእቴጌ ጣይቱና የዳግማዊ ምኒሊክ ባንክን/ኢኮኖሚን “ከቅኝ ግዛት” ነፃ የማድረግ ታሪክ

‹‹ያልተዘመረው… የእቴጌ ጣይቱና የዳግማዊ ምኒሊክ… ባንክን/ኢኮኖሚን “ከቅኝ ግዛት” ነፃ የማድረግ ታሪክ…››

አንድ ቀን ምሽት የሴት አንበሳዋ እቴጌ ጣይቱ የቁጣ ፊቷን በምኒልክ ዙፋን ፊት አነደደችው።
‹‹ተደፍረናል…! ተንቀና…! በገዛ ሀገራችን የራሳችን ዜጎች በእንግሊዞች እየታሰሩ መሆኑን ሰምተህልኛል?››…
‹‹ምን አልሽኝ ጣይቱ? መታሰር አልሽኝ?›› ንጉሠ ነገሥቱ የሰማውን ማመን አቅቶት ጥያቄዋን በጥያቄ መለሰ።
‹‹አዎ መታሰር! እንግሊዞች ዜጎቻችንን በሐበሻ ባንክ ዕዳ እያሰሩ ነው። ይህ ትልቅ ድፍረትና ንቀት ነው። ለዚህ ዋጋ ይከፍሉበታል!›› …እትጌ የበለጠ እየተቆጣች ተናገረች።
‹‹ይህማ አይደረግም! ተራ ወሬ መሆን አለበት። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል…? ለመሆኑ አጣርተሻል ጣይቱ?›› …ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ለማመን ከበደው።
‹‹እኔ ጣይቱ…! ሳላረጋጥ ተራ ወሬ ይጄ ነው እንዴ ካንተ ፊት የምቀርበው? ነገሩ እርግጥ ነው››።
‹‹እኔ የዳኛው ጌታ! …ይህማ አይደረግም።›› ኑጉሡ እንደ አንበሳ ተቆጣ።
‹‹አሁኑኑ ባንካቸውን ዘግተው እንዲወጡ ትዕዛዝ ይሰጥ። ዛሬውኑ!!!›› እቴጌ በመደፈር ስሜት ተናገረች።
ዳግማዊ ምኒልክ ትንሽ ዝም አለ። ቀና ብሎ ጣሪያ ጣሪያውን አየ። ከዙፋ ወርዶ ከወዲያ ወዲህ ተንጎራደደ። ከዚያም ወደ እቴጌ ዘወር አለና……
‹‹እየውልሽ ጣይቱ… ነገሩ እጅግ ያበሳጫል። የሕይወት ዋጋ ተከፍሎላቸው ነፃነታቸውን በደማቸው ያወጁ ሕዝቦች በመዲናቸው ሲታሰሩ እንደማየት የሚያም ምንም ነገር የለም። የባንኩ ኃላፊዎች አሁኑኑ መጥተው ጉዳዩን እንዲያስረዱ ይደረጋል። ለዚህ ድፍረታቸው መቀጣታቸውና ባንኩም መዘጋቱ አይቀርም። ነገር ግን ጣይቱ….. አንድ ነገር መዘንጋት የለብንም። ይህንን ባንክ ስንዘጋ… ለሕዝባችን አማራጭ ባንክ መክፈት አለብን። ሕዝባችን የለመደውን ተበድሮ የማደግ አማራጭ እንዲሁ መዝጋት አይገባምና በዚህ ጉዳይ እንድንመክርበት…ለፊታራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ፣ ለበጅሮንድ ሙሉጌታ፣ ለራስ ቢትወደድ ተሰማ፣ ለራስ ወልደጊዮርጊስና ለነጋድራስ ኃይለጊዮርጊስ ይነገራቸው። ሁሉንም በምክር ብናደርገው መልካም ነው።›› አላት በፍቅር የተቆጣ ዓይኗን እየተመለከተ።
‹‹ይህ መልካም ሐሳብ ነው ይሁን። ግን የእስረኞችስ ጉዳይ?›› ጣይቱ ባልተቤቷን ጠየቀች።
‹‹እስረኞችማ አሁኑኑ ይፈታሉ። አሁኑኑ ለፊታራሪ ቴሌግራም ይደረግና ያስፈታቸው።›› ምኒልክ በቁጣ ትዕዛዛ አሰተላለፈ። እትጌም ተስማምታ ትዕዛዙን አስተላለፈች። እስረኞችም ተፈቱ። ሕዝቡም አቤቱታውን በይፋ እንዲያቀርብ ተደረገ።

በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው ባንክ እኤአ በ1905 በግብጽ ብሔራዊ ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ስምምነት የተመሠረተው ‹‹የሀበሻ ባንክ – Bank of Abyssinia›› ነው። ይህ ባንክ ግን ባለንብረትነቱ የእንግሊዝ መንግሥት ነበር። (እንግሊዝ በግብጽ በኩል የኢትዮጵያን ባንኮች/ኢኮኖሚውን በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት የመያዝ ተግባራዊ ሙከራ መሆኑን ልብ ይሏል)። እናም እንግሊዞች ለኢትዮጵያውያን ብድር ከሰጡ በኋላ ብድሩን ለመመለስ የማይችሉትንም ከመመለሻ ቀኑ የሚያዘገይቱንም ማሰር ጀመሩ። በጣም የሚገርመውና ጉዳዩን የቅኝ ግዛት ሙከራ የሚያደርገው ደግሞ… እንግሊዞች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የራሳቸውን እስር ቤት ከፍተው ያለ ኢትዮጵያ መንግሥት ዕውቅና ነበር ብድር ኢትዮጵያውያንን የሚያስሩት።
እቴጌ ጣይቱ ይህንን በሰማች ጊዜ እንደ ነብር ተቆጥታ ለአንበሣው ባሏ ለንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ነገረችው። (ይህ የእንግሊዞች ባንክ በመክፈት ስም የሚያደርጉት ነውረኛ ተግባር ዘግየት ብሎም ቢሆን ከእትዬ ጣይቱ ጆሮ በደረሰና ለንጉሡም በነገረችው ጊዜ የነበረውን የቃላት ልውውጥ ነው ‹‹በምዕናብ›› ለላስታውሳችሁ የሞከርሁት።)

እቴጌ ጣይቱ እና ዳግማዊ ምኒልክ ጉዳዩን በሰሙ ጊዜ… እስረኞችን ከማስፈታትና የእንግሊዞችን ባንክ ከመዝጋት ባለፈ አማራጭ ባንክ ስለመክፈት መከሩ። ከምክክር በኋላም በኢትዮጵያውያን ሲመሠረት የመጀመሪያውና በልማት ባንክ ታሪክ ፈር ቀዳጅ የሆነው ‹‹የርሻና የንግድ ማስፊያ የኢትዮጵያ ማኅበር›› ተመሠረተ። ይህ ‹‹የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ታሪካዊ ጅማሮን›› ያበሰረ ማኅበር የተቋቋመው በዚህ (ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ የ100 ዓመት ታሪክ ዘካሪ መጽሔት አግኝቼው እዚሁ ላይ በፎቶ ባስቀመጥሁት) አዋጅ ነበር።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ታሪካዊ ጅማሮን

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ታሪካዊ ጅማሮን

ማኀበሩን የመሰረቱት ሰባት የወቅቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ውላቸውን አቅርበው በጠየቁት መሠረት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በአክስዮን መልክ የተቋቋመው ይኸው ማኅበር አቋሙ የታመነና ጠንካራ ይሆን ዘንድ… ዳግማዊ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ መሥራች ማኅበርተኛ/አባል ሆነው እንዲገቡ ተደርገ።

በመጨረሻም ‹‹እኛ (ዳግማዊ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው፣ ራስ ወልደጊዮርጊስ፣ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ በጅሮንድ ሙሉጌታ ይገዙና ነጋድራስ ኃይለጊዮርጊስ ወልደሚካኤል) በዚሁ ወረቀት ግርጌ የእጅ ፊርማችንን ያደረግን የኢትዮጵያ ማኅበር አቁመን ስሙን ‹የርሻና የንግድ ማስፊያ የኢትዮጵያ ማኅበር› ተብሎ እንዲጠራ ተስማምተናል።›› በማለት በማለት ተፈራመው አጸደቁት። አዋጁም ግንቦት 23 ቀን 19ዐ1 ዓ.ም (እኤአ 1909) በይፋ ታውጆ ባንኩ/ማኅበሩ ተመሠረተ። በኋላም ሌሎች ሰዎችና ነጋዴዎች አክሲዮን በመግዛት በማኀበሩ ውስጥ ተሳታፊ ሆኑ።

ይህንን ነፍሴ የተደሰተችበትንና ካሁን በፊት ሰምቼው/አንብቤው የማላውቅን ታሪክ በምዕናባዊ ወግ አላዝቤ አጋራኋችሁ። በንጉሡና ንግሥቷ የተወሰደ… ከዐድዋ ቀጥሎ ሊዘመርለት የሚገባ ታሪካዊ የነፃነት እርምጃ ነው። እቴጌ ጣይቱ እና ዳግማዊ ምኒልክ… የሀገር ድንበርን ብቻ ሳይሆን… የባንክን/የኢኮኖሚንም ነፃነት ያረጋገጡ ንግሥትና ንጉሥ መሆናቸውን የማወቅና የማሳወቅ ኢትዮጵያዊ ግዴታ አለብን።

የግርጌ ማስታወሻ፡-
(የመጀመሪያው ባንክ ከአሁኑ የአቢሲኒያ ባንክ ጋር የታሪክም ሆነ ሌላ ግንኙነት የለውም)።

melakual@shegerblog.com'
ለሀገር መለኛ ሐሳቦችን እናዋጣለን!

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...