Tidarfelagi.com

እርዳታ እና እኔ

ግኑኝነታችን የሚጀምረው፣ በልጅነቴ ከበላሁት የእርዳታ “ፋፋ” እና “ዘይት” ነው። የሆነ ጊዜ ወተትም ነበር። የሆድ በሽታ ለቀቀብኝና ለሳምንታት ላይና ታይ በሌ ስል ኖሬ ይቺን ዓለም በጨቅላነት ሳልገላገላት ለትንሽ አመለጥኩ።

ኑሮን በድህነት ስትገፋ በወር የሚሰጥህ 5 እና 10 ኪሎግራም ምጽወታ ነፍስህን ለማቆየት ትረዳ ይሆናል። የተመረዘ በልተህ እስከወዲያኛው ካልተሸኘህ። ያኔ ችግሩ ከኔ ወይም ከቤተሰቦቼ ይመስለኝ ነበር። ወላጆቻችን በቀን ከሚገባው በላይ ላባቸውን አንጠፍጥፈው ይሰራሉ። ያ ሁላ ላብ ፈስሶ ለለት ጉርስ የሚበቃ ነገር እንኳን አያገኙም። በአንጻሩ ደግሞ ቅንጣት ሳይሰራ የሰው ደም የሚመጥ ተባይ፣ የሰው አጥንት የሚግጥ አውሬ በተዋረድ ከላይ እስከታች አገሪቱን ወሯታል። ምድሪቱ ለሁላችንም የሚበቃ ነገር አታመርትም ነበር? ግብር የሚሰበስብ፣ በህዝብ ስም ምጽዋት የሚቀበል፣ ብድር የሚዝቅ መንግስት የለም ነበር? ከተረፋቸው ወደ ሌላቸው የሚበትን የገበያ ስርዓት አልነበረም? እዛ የሚበላው አጥቶ እህል ሲነቅዝ፣ እዚህ በርሃብ የሚረግፈው ወገን ለምንድን ነው?

ያኔ እነዚህን ጥያቄ መጠየቅ አልችልም ነበር። አልተማርኩም። ድሀ መሆኔ፣ ከድሀ ቤተሰብ መወለዴ፣ የኔ ስህተት ይመስለኝ ነበር።

ትምህርቴን እንደምንም ጥርሴን ነክሼ ጨረስኩ። በአንድ ፕሮጀክት (ጎልጎል ራያ ይባል ነበር ያኔ) ስራ ጀመርኩ። የፕሮጀክቱ ገንዘብ እንዴት እንደሚዘርፍ ገና 20 ሳይሞላኝ አየሁ። ተጣልተው ፕሮጀክቱን አፈረሱትና ለግብርና አስረክበውኝ ሄዱ፣ በቤት ላይ ቤት፣ በንብረት ላይ ንብረት እንዴት በዘረፋ እንደሚያካብቱ አየሁ። የገበሬ ልጆች የሚበሉት ምሳ ስሌላቸው ትምህርት መሄድ በማይችሉበት ቦታ በነዚህ ልጆች ስም የመጣ እርዳታ ከላይ እስከታች ድረስ ያለው መዥገር እንዴት እንደሚመጠምጠው አየሁ። ባይነት ባይነቱ ይግጡታል። እርዳታውን በከፍተኛ ወለድ ብድር ሰጥተው ከነወለዱ ይቀረጣጥፉታል። ያ አልበቃ ብሏቸው በመዋጮም ይግጡታል።

ይህን ሁሉ በለጋነቴ አየሁ። ከልጅነቴ ጋር አቆራኘሁት። እልህ ያዘኝ። ደሜ ፈላ!

የናቹራል ሳይንስ ተማሪ ነበርኩ። ያውም በጣም ከፍተኛ ውጤት አርማዬ። ግን የኔ A በዚህ ሲስተም ውስጥ ዋጋ የላትም። ለኔም አትበጅ ለማህበረሰቤም አትበጅ። እኔ በህይወታቸው ቅንጣት ለውጥ በማያመጣ ነገር አፈርና ውሃ ሳስከትራቸው፣ እነሱ ዶላሩን ይከትሩታል። ገና ለገና የገረጣው ተራራ ነፍስ ዘርቶ ሆዳቸውን መሙላት ይችላሉ ተብሎ ሲፈጉ፣ እዚህ ያለቀውን ዳቦ የሚሻማ አሳማ አለ። መፍትሔው ያለው የአፈር ኬምስትሪ ና ፊዚክስ መከካት ላይ ሳይሆን ማህበራዊ ሳይንስን ላይ ነው፣ የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ። እናም ከልጅነቴ ጀምሮ እመኝ የነበረውንና ሃይስኩል ላይ የጀመርኩትን ኢኮኖሚክስ በጎን ማጥናት ጀመርኩ። ረዥሙን ታሪክ ሳሳጥረው፣ ኢኮኖሚክስ ዓይኔን ገለጠው። መዥገርነቱ የታችኛው የመንግስት መዋቅር ብቻ ሳይሆን ከላይ ከዋናው እንደሚነሳ ተረዳሁ። በይበልጥ ለማጥናት ወሰንኩ፡፡

ለከፍተኛ ትምህርት ወደዚህ አገር ስመጣ ቀዳሚ ትኩረቴ እርዳታና ፖለቲካ ላይ ሆነ። አስታውሳለሁ የመጀመሪያ ሰሚስተር ላይ የጻፍኩት ተርም ፔፐር እንዴት እንደተወደደልኝ። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ስለጉዳዩ ባለማቋራጥ ሁሌም አነባለሁ። ባነበብኩ ቁጥር ውስብስብነቱ እየጎላ ሲሄድ ይታየኛል። ነጮች ስለ እርዳታ እንዲወራ እንኳን አይፈልጉም። ወይም ከተወራም በጥቁር መሆን የለበትም። እርዳታ ጥሩ ነው የሚለውም መጥፎ ነው የሚለውም ጥቁሩን ወክሎ ሁሌም ነጭ ነው። የአምባገነኖች ተቀጣሪ ካልሆኑ በስተቀር አንድም ጥቁር ምሁር እርዳታ ጥሩ ሊበረታታ ይገባል ብሎ ሲከራከር አታዩም። ለምን?

ዘመናዊ ቢዝነስ ነው። ለብዙዎቹ ደሞዝ ነው። የስራ ዕድል ነው። የሀብት ምንጭ ነው። ህዩጅ፣ እጅግ በጣም ህዩጅ ኢንዱስትሪ ነው። ከUN እስከ WB እስከ WFP እስከ Action aid እና ምናምን ከ90% በላይ ተቀጣሪው ነጭ ነው።የት ይግባ ይህ ሁሉ ሰራዊት?

ለእርዳታ ከሚለገሰው ከ50% በላይ ከለጋሽ አገሩ ሳይወጣ እዛው ነው የሚቀረው። ከወጣ ብኋላ ስራ አስከያጆቹ እነሱ፣ ለስራ ማስኬጃ የሚቦድሱት እነሱ፣ ለመኪና ለነዳጅ ለአበል እየተባለ ተቦድሶ ታች የሚደርሰው፣ ከ10% አይበልጥም። ያቺም ከቦታዋ ስትደርስ ካድሬ ይናጠቃታል። ባለስልጣን ይናጠቃታል። በመጨረሻ የሚቀርህ፣ ሰርቶ ማሳያ (ሰሪሕኻ መርአይ) ሳይት ብቻ ነው። ይህን ያህል ነው ክራይሙ።

ከብዙ ጥናት ብኋላ (አንድ ቀን በደንብ እንደምጽፈው አምናለሁ!) የደረስኩበት ድምዳሜ፣ “ድሀ የሚጠቀመው እርዳታ ሲቆም ብቻ ነው” የሚል ነው። በተወሰነ ደረጃ ዛሬ በቆሼ አይታችሁታል!

ይቀጥላል

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...