Tidarfelagi.com

የታላቁ ንጉስ እምዬ ምኒልክ የመጨረሻ ስንብት

“ያገሬ የኢትዮጵያ ሰዎች ልጆች ወዳጆች እግዚአብሔር የገለፀልኝን ምክር ልምከራችሁ። ምክሬንም እግዚአብሔር በልባችሁ እንዲያሳድርባችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።

አፄ ቴዎድሮስ የሞቱ ጊዜ ከሳቸው ጋር የነበረው ሰው ሁሉ ያንዱን አገር አንዱ እደርባለሁ፤ አንዱን ገድዬ እኔ ጌታ እሆናለሁ፤ እያለ ሁሉም ላይረባ ተላልቆ ቀረ።

አሁንም ልጆቼ ወዳጆቼ አንዱ ባንዱ ምቀኝነት ይቅር ያንዱን አገር አንዱ እኔ እደርባሉ እንዳትባባሉ። እኔ እስካሁን በፍቅር እንዳኖርኳችሁ እናንተም ተስማምታችሁ በፍቅር እንድትኖሩ እለምናችኋለሁ።

እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታቹሁ ካላለቃችሁ በቀር አገራችንን ኢትዮጵያን ለሌላ በዕድ አትሰጧትም። ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም።

ንፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ። ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተድንበር መልሱ።

የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ድንበር ቢጋፋ በኔ ወገን ካልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ሁላችሁም ሄዳችሁ በአንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ። እየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ።

ከብዙ ዘመን ጀምራ ተከፋፍላ የነበረችውን አገራችን ኢትዮጵያን ማስኜ ተጣጥሬ ይሄው አስፍቻታለሁ። እናንተም ከልጄ ጋር ሆናችሁ ተስማምታችሁ የኢትዮጵያን ድንበር እንዲሰፋ እንጂ አንድም ጋት መሬት እንዳይጠብ አድረጉ። ጠብቁ አልሙ። የደጊቱ አገራችን የኢትዮጵያ አምላክ ያግዛችሁ። ይጠብቃችሁ።

ከዚህ ቃል የወጣ በሰማይም ነብሱ በምድርም ስጋው ከልጅ እሰከ ልጅ የተረገመ ይሁን፤ የኢትዮጵያ ወቃቢ ያጥፋው፤ እኔም ሳለሁ ከፍቃዴ የወጣውን ረግረሜያለሁ።”

******
እምዬ ምኒልክ ፀሐዩ ንጉስ ልክ በዛሬው እለት ታህሳስ 3 ቀን 1906 ዓ.ም ይህችን አለም ተለዩ።
ነገር ግን ዛሬም ከኛው ጋር አሉ።

አስተያየትዎን እዚህ ይስጡ

የኢሜል አድራሻዎ አይወጣም

Loading...