ላለፉት ጥቂት ቀናት ያገኘኋቸውን ወንዶች በሙሉ አንድ ጥያቄ ስጠይቅ ነበር፡፡
‹‹የቤት እመቤት ምን ማለት ነው?››
ከአንድ ወይም ሁለት መልሶች ውጪ የተሰጡኝ ፍቺዎች በሚከተሉት ሀረጎች ሊጠቃለል ይችላል፡፡
‹‹የማትሰራ ሴት››
‹‹ስራ የሌላት ሴት››
‹‹ገቢ የሌላት ሴት››
‹‹ስራ አጥ ሴት››
‹‹ስራ ፈት ሴት››
እነዚህን መልሶች የሰጡኝን ወንዶች መልሼ ይሄንን ጥያቄ ጠየቅኳቸው።
ነጋ ጠባ አልጋ ማነጠፍ፣
ቆሻሻ ልብስ ማጠብ፣
የታጠበ ልብስ ማጠፍ፣
የታጠፈ ልብስ በየቦታው ማስቀመጥ፣
ከሻይ ማንኪያ እስከ በርሜል ሙልጭ አድርጎ ማጠብ፣
ከሻይ ማንኪያ እስከ በርሜል ሙልጭ አድረጎ የታጠበ እቃን ማድረቅ፣
ከሻይ ማንኪያ አስከ በርሜል ሙልጭ ተደርጎ የታጠበና የተደረቀ እቃን በየቦታው ማስቀመጥ ስራ አይደለም?
በየቀኑ ከኩሽና እስከ ሳሎን፣ ከሽንት ቤት እስከ ግቢ መጥረግና መወልወል፣
ከሳሎን ጠረጴዛ እስከ ቁምሳጥን ጀርባ እና አልጋ ስር ድረስ መጥረግና መወልወል፣
የቤቱን ሁሉ የተጠረገና የተወለወለ ቆሻሻን ሰብስቦ መጣልስ ስራ አይደለም?
ቀን ቆጥሮ አንሶላ፣ ትራስ ልብስ እና አልጋ ልብስ መቀየር፣
ጊዜን አስልቶ የኩሽና እቃ ገልብጦ አውጥቶ ማፅዳት፣
ጊዜን ወስኖ የመስኮትና የበር መስታወትን በጋዜጣ ሲያፀዱ እና ሲያስውቡ መዋል፣
የአደፈ መጋረጃን መለወጥ ስራ አይደለም?
‹‹ምን አለቀ?›› ብሎ ቀለብ መሸመት ፣
የተሸመተውን አመጣጥኖ ማዘጋጀት፣
የተዘጋጀውን ማቅረብ እና ቤተሰብን መመገብ ስራ አይደለም?
ደግሞ ከሁሉ በላይ ፣
ልጅ ማርገዝ፣
ልጅ አምጦ መውለድ፣
ልጅ አጥብቶ ማሳደግ፣
ልጅ ማነፅ፣
ልጅን ለወግ ማብቃት ስራ አይደለም?
እናም ወንድሞቼ ..
አገልግሎት እና ምርታማነትን በጥሬ ገንዘብ በሚተምን የኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ በመኖራችን ብቻ፣
በቀጥታ የገንዘብ ክፍያ የማያስገኝ ስራ እንደ ስራ በማይቆጠርበት አለም በመኖራችን ብቻ፣
ይሄን እና ሌላም ልዘረዝረው ያቃተኝን ስራ ሁሉ የምትሰራን ሴት ‹‹ስራ የላትም‹‹ አትበሉኝ፡፡
ይልቁንስ፤ በእኛ ሀገር የቤት እመቤት መሆን ከእመቤትነቱ ሸክሙ ይበልጣል እና፤
ሚዛናችሁን አስተካክላችሁ… ‹‹የቤት እመቤት ማለት ‹በአለም ላይ ከባዱን ግን ክፍያ የሌለውን ስራ የምትሰራ ሴት ማለት ናት›› በሉኝ!
(Happy International Women’s Day!)